ዓለማችንን እየተፈታተኑ ካሉ ችግሮች በዋንኛነት የሚጠቀሰው የአየር ሙቀት መጨመር ነው። ችግሩ ዓለምን በብዙ መልኩ እየተፈታተነ ቢገኝም ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ አሁንም ዓለም አቀፍ ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል። በተለይም የችግሩ ዋነኛ ተጠቂ የሆኑት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ሕዝቦች ዛሬም ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየጮኹ ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ዓለማችን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን በ1.2 ዲግሪ ሴልሺዬስ፤ ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠንም 50 በመቶ ጨም ሯል። በችግሩ ዙሪያ የተጠናከረ ርምጃ መውሰድ ካልተቻለ የምድራችን ሙቀት መጠን በያዝነው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ወደ 2 ዲግሪ ሴልሺዬስ ከፍ ሊል ይችላል።
ችግሩ አሁን ላይ የሰዎችንና የተፈጥሮ ሃብትን ሕልውና እየተገዳደረ ይገኛል። ከዕለት ተዕለት እያደገ ያለው የአየር ሙቀት መጨመር አንዳንድ ሥፍራዎችን ወደ በረሃነት እየቀየረ ነው። እየተከሰተ ካለው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ጋር በተያያዘም የተለያዩ የዓለም አካባቢዎች በጎርፍ እየተጠቁ ነው።
የአየር ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ፤ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በድርቅ እንደሚጠቁ በዓለም ላይ በጣም ለም በሆኑ የግብርና አካባቢዎች የሰብል ምርት እንደሚቀንስ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘም በዓለም አቀፍ ደረጃ ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሊያስከትል እንደሚችልም በዘርፉ እየተደረጉ ጥናቶች እያመላከቱ ነው።
በችግሩ ምክንያት አዳዲስ ገዳይ በሽታዎችን እንደሚከሰቱ፣ ሚሊዮኖች በውሃ መጠን መጨመር ምክንያት ከመኖሪያቸው ቀያቸው ሊፈናቀሉ፤ እፅዋትና እንስሳት ከምድራችን ሊጠፉ እንደሚችሉ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የሚ ገኙ የእርሻ ቦታዎች ወደ በረ ሃማነት እንደሚቀየሩ እያስጠነቀቁ ነው።
ችግሩ አሁን ላይ “ከረሀብ ነፃ የሆነች ዓለም” ለመፍጠር ለተጀመረው ዓለም አቀፍ መነቃቃት ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ይታመናል። በተለይ በግብርናው ዘርፍ ላይ እየፈጠረ ካለው ስጋት አኳያ፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በኃላፊነት መንፈስ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ካልቻለ ጥረቱ “ላም አለኝ በሰማይ….” አይነት መሆኑ የማይቀር ነው።
በተለይም የበለፀጉ ሀገራት የችግሩ ዋነኛ ፈጣሪዎች/ባለቤቶች ከመሆናቸው አንጻር፣ ከቋንቋ ባለፈ በተጨባጭ ለችግሩ ዋነኛ መፍትሔ መሆን፤ ችግሩን ለመከላከል በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ውስጥ በታማኝነት ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ መገኘት ይኖርባቸዋል።
ችግሩ አሁን ላይ በተጨባጭ እያስከተለ ካለው አደጋ አኳያ፣ እነዚህ ሀገራት የችግሩን ግዝፈት ከመተረክ ባለፈ፣ ለችግሩ አዳዲስ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማቅረብ፣ ቀደም ሲል በተለያዩ ወቅቶች ችግሩን አስመልክቶ ለተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ።
ይህንን ግዴታቸውን መወጣት ባልቻሉበት ሁኔታ፣ ከረሀብ ነፃ የሆነች ዓለም ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት “ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ” አይነት መሆኑ ስለማይቀር፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሆነ፣ የጉዳዩ በአሳሳቢነት የሚመለከታቸው አካላት ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን በኃላፊነት መንፈስ እንዲወጡ ጫና ሊያሳድሩ ይገባል ።
ከረሃብ ነፃ የሆነች ዓለም ለመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጀመረው መነሳሳት፤ በቅድሚያ ዓለምን ከተደቀነባት ሁለንተናዊ ስጋት ከመታደግ የሚጀምር ሊሆን ይገባል። ለዚህም መላው ዓለም ድምፁን ከፍ አድርጎ መጮኸ፤ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ይኖርበታል።
ችግሩን ባላቸው አቅም ለመከላከል ለሚሞክሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ዓለም አቀፍ እውቅና እና ተገቢውን ድጋፍ መስጠት፤ ተጨባጭ ተሞክሯቸውን በማስፋት ችግሩን ለዘለቄታው መቋቋሚያ ስትራቴጂክ አቅም አድርጎ መውሰድም ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ እና መላውን ሕዝብ በማንቀሳቀስ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር 40 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን በመትከል፤ ችግሩን ባላት አቅም ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት በተጨባጭ አሳይታለች።
በዚህም የአየር ሙቀት መጨመር የታመመ የአየር ንብረቷን ከማከም ባለፈ፤ ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሠራች ነው። በዓለም አቀፉ ደረጃም የችግሩ የመፍትሔ አካል በመሆን ጎልታ ወጥታለች ።
ይህ ተጨባጭ ተሞክሮዋ በምግብ እህል እራስን በመቻል ከረሃብ ነፃ የሆነ ሀገር ለመፍጠር እያደረገችው ላለው ጥረትም ትልቅ ጉልበት፣ ዘላቂ የግብርና ልማት እውን ለማድረግም ስትራቴጂክ አቅም እየሆናት ነው። በዚህም ተስፋ ሰጭ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።
ይህ የሀገሪቱ ተሞክሮ፤ በአየር ሙቀት መጨመር የታመመ የአየር ንብረትን በማከም የግብርና ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ከረሃብ ነፃ የሆነች ዓለም መፍጠር እንደሚቻል በተጨባጭ ያመላከተ እና ተገቢ ዓለም አቀፍ እውቅና እና ድጋፍ ሊቸረው የሚገባው ግሩም ስኬት ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም