የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ በመጋቢት ወር መጨረሻ 2011 ዓ.ም ሥነ ጽሑፍ ለሰላም በሚል አገር አቀፍ ዐውደ ጥናት አካሂዶ ነበር። በዶክተር ደመቀ ጣሰው የማኅበረሰብ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ምርምር አስተባባሪነት በተካሄደው ውይይት ላይ በዶክተር ተስፋዬ ዳኘው፤ በወይዘሮ ሜሪ ጃዕፋር፤ በዶክተር ታደለ ፋንታው፤ በዶክተር ጥላሁን በጅቷል፤ በዶክተር አንተነህ ደመቀ፤ በዶክተር አብርሃም መልኬ፤ በዶክተር ሃይማኖት ዋሴ፤ በተለያዩ የጥናት ርእሶች ዙሪያ የመወያያ ሐሳቦች ቀርበዋል። በውውይቱ ጣልቃም ስለ ሀገር ፍቅርና ስለ ሰላም የሚያስገነዝቡ የግጥም ሥራዎች ተደምጠዋል።
የሰላም ሥነ ጽሑፍ ዘውጉ፤ ምንነቱና ዓላማው በሚል ዶክተር ጥላሁን በጅቷል ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጽሑፍ ለሰላም ያለው አሉታዊና አዎንታዊ ሚና ላይ ጥናት አቅርበዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ድርሰት ርኅራኄ ኀዘኔታ፤ ራስን በሌላው ቦታ ላይ አድርጎ የማሰብ ጉዳይ፤ የዓለማቀፋዊነትና የሰብአዊነት ይዘት አለው። ሥነ ጽሑፍ የሰላም መንገድ ጠራጊ ነው። በተመሳሳይ በየዕለት ሰላምታችንና ጸሎታችን (በክርስትናውም በእስልምናውም) ሰላም የሚል ቃል እናዘወትራለን። በሰላም ሥነ ጽሑፍ ልቦለድ ድርሰት፤ ሥነ ግጥምና ፊልም፤ ዐጭር ልቦለድና በትረካ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ፤ ኖቬላ ታላቅ ሚና ይጫወታሉ።
ዶክተር አንተነህ አወቀ እንዲሁ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጽሑፍ ለሰላምና ወይም ለግጭት ያበረከተው አስተዋጽኦ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚል ርእስ ጥናታቸውን አቅርበዋል። በእርሳቸው ገለጻ ረገድ ሥነ ጽሑፍ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ማናቸውንም ሀገራዊ ጉዳዮች ለማንጸባረቅና በጉዳዮቹ ላይ የሚፈጠሩ የተለያዩ ስሜቶችን፤ አስተሳሰቦችን ለመግለጽ የሚችል መሣሪያ ነው። ለምሳሌም በ1976 ዓ.ም የታተሙ ድርሰቶች ሕዝብን በማስተባበር ሰላምን ለማስፈን የቻለ መሆኑን ይገልጽልናል። ዶክተር አንተነህ አወቀ እንደሚሉት በጣምራ ጦር ሀገርን የመከላከል ተግባር የተሠራው በሕዝቡ ጥምረት ነው። የኢትዮጵያ ሶማሌዎች፣ ከኦሮሞ፣ ከአማራና መሰል ኢትዮጵያውያን ጋር ኅብረት በመፍጠር ሀገርን የመከላከል ሥራ ተሠርቶ ሰላምን ለማስፈን ተችሏል። ልቦለዱም ስልታዊ መንገድ በሆነ መልኩ የሕዝብን አንድነት የሚገልጽ ነው። ምክንያቱም ኃላፊነት በተመላበት መንገድ በተቆርቋሪነት ስለተጻፈ ነው።
የሕዝብን አንድነት፤ ሰላምና ፍቅርን የሚያጠናክሩ ድርሰቶች እንዳሉ ሁሉ የተለየ ተልእኮን (ግላዊም ሆነ ተቋማዊ) ለማስፈጸምና ጥላቻን በሕዝቦች መካከል የሚዘሩ ድርሰቶች አሉ። በዚህ ረገድ በዘመነ ኢሕአዴግ ከተቀነባበሩ ድርሰቶች ውስጥ አንዱ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመምሪያ ኃላፊ ሆኖ ሲሠራ የነበረው የተስፋዬ ገብረ አብ መጽሐፍ ነው። ተስፋየ የቡርቃ ዝምታ በሚል በሸረበው ሥራው በተለይም በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠርና ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት ሲል ያቀነባበረው የሴራ ድርሰት ነው። በዚህም አቀናባሪው ለሕዝብ ፍቅርና ለእውነት ያለው አስተሳሰብ ዝቅተኛ ስለሆነ ጥያቄ ላይ ወድቋል።
ድርሰት ከፖለቲካና ከርእዮተ ዓለም ነጻ እንደማይሆንና የተለያዩ ቡድኖች በተለይም መንግሥትና የፖለቲካ ተቋማት በሕዝብ ውስጥ ማስረጽ ለሚፈልጉት ጉዳይ መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት እንደሚሹ መረዳት ተገቢ ነው። በዚህ ዓይነት ጥናት አቅራቢው እንደጠቀሱት ተስፋዬ ገብረ አብ የቡርቃ ዝምታ (1992) ብሎ በሸረበው ድርሰቱ በአማራ ላይ ያለውን የከረረ ጥላቻ በኦሮሞነት በኩል ተጠግቶ ማስተጋባቱ ነው።
ተስፋዬ ገብረ አብ የልቦለዱ አቀንቃኞች በሆኑት አኖሌና ሐዊ አንደበት እንደሚናገረው የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዓመት ብቻ ነው። ይህም የኦሮሞን መሬት ከወሰደው፤ የተቃወሙትን ጥፍር ከነቀለው፤ ብልትና ጡት ከቆረጠው፤ የገዳ ሥርዓትን ከአጠፋው ከምኒልክ ጋር የተያያዘ ነው (ገጽ 93)። ቡርቃ የተባለው ወንዝም የኦሮሞ ሕዝብ ተምሳሌት ሲሆን ከምኒልክ በፊት በመሬት ላይ ይፈስስ ነበር። ምኒልክ ከመጣ በኋላ ግን በኦሮሞ ሕዝብ ድርጊት አፍሮ በመሬት ውስጥ እየሄደ ነው። « እናም ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ በኢሕአዴግ ትግል አማካይነት ነጻነት ስላገኘህ አማራን ውጋው፤ አጥፋው፤ ደምስሰው፤ አኖሌ ሆይ አንተም በበኩልህ የአክራሪ ነፍጠኛ ልጅ የሆነቺውን አማራዋን ዮዲትን ፍታት፤ ዘርህ አይደለችምና »ይለናል። ልቦለዱም የሚጠናቀቀው የዘር ፖለቲካን በማቀንቀን፤ እንኳን ምድሩ ሰማዩም የኦሮሞ ነው በሚል የሰላም ፀር የሆነውን ግጭት በመቀስቀስና ኦሮሞን ለበቀልና ለጥላቻ በማነሣሣት ነው።
ተስፋዬ በድርሰቱ ፊታውራሪነት ዐመፁን ያስጀምረዋል። ኦሮሞው ነፍጠኛ ብሎ በፈረጀው የአማራ ሕዝብ ላይ ይዘምታል፤ ይገድላል፤ ቤት ንብረቱን ያፈራርሳል። በዚህ ድልም ተስፋዬ በሳለው ገጸ ባሕርይ ደስታን ይጎናጸፋል። በአማራ ሕዝብ ሥቃይ፤ ሞትና ስደት፤ ውርደት ይደሰታል፤ ተስፋዬ።
በዚህ ዓይነት የዘር ፖለቲካን በሚያኝከው፤ አማራን በሚያጠቁረው፤የኢትዮጵያን ታሪክ በ100 ዓመት በገደበው፤ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክን ጨምሮ የቀድሞ ነገሥታትን ጥላሸት በሚቀባው የዘመናችን የጥፋት መልእክተኛ በሆነው የቡርቃ ዝምታ ትርክት ሕዝቡ አብሮ እንዳይኖር፤ ሰላሙ እንዲደፈርስ፤ በራስ የመቆም ተስፋው እንዲያከትም፤ እምነቱ እንዲቀጭጭ፤ በዘረኝነትና ጎጠኝነት ሕልሙ እንዲጨልምና እርስ በእርሱ እንዲታመስ፤ ግጭት እንዲፈጠር፤ የሰብአዊ መብቱ እንዲረገጥና ነጻነት እንዲጠፋ፤ ጊዜ በሰጣቸው ፖለቲከኞች እንዲዋረድና ግፍና መከራ እንዲደርስበት ሲደረግ ቆይቷል።
እናም ባለፉት 27 ዓመታት ሥነ ጽሑፍ ኢሕአዴግን ኮቴ ከኋላው ተከትላ ትንፋሹን እያዳመጠች ወደ ፊት ከመሄድና ለሥርዓቱ አሽቃባጮች የገንዘብ ማግኛ ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራትም። የሥርዓቱ አሽቃባጮች ጥበበኛ ሳይሆኑ እንደ ጥበበኛ መስለው በጥበብ ስም ነግደዋል። ጥበብ ከማኅበረ ሰብ ፊት ቀድማ መምራት እንጂ በኋላ እየተከተለች ለባለጊዜ ማሽቃበጥና ሕዝብን እርስ በርሱ ማፋጀት የለባትም። ዶክተር አንተነህ አወቀ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ከበኩር ጋዜጣ ጋር ያደረገውን ውይይት ዋቢ በማድረግ እንደጠቀሱት ጥበብ ወይንም ሥነ ጽሑፍ ማኅበረ ሰብን ሊከተል ወይም ሊመራው ይችላል። ከማኅበረሰብ ፊት ቀድሞ መንገድ ያሳያል። ጉድፍ ያነሣል።
ኅብረተሰቡ ያላየውን እያየ ምዕናባዊ እርካታን ለማስገኘት ይጥራል።
በኢጣሊያ ወረራ ወቅት እነ ዮፍታሔ ንጉሤ ነጻነት እንዲመለስ፤ ሰንደቅ ዓላማ እንዲቆም ሱዳን ውስጥ ሆነው በጽሑፎቻቸው ለዐርበኞች የሠሩት ሥራ ጥበብ ማኅበረ ሰቡን የምትመራ ምልክት ተደርጋ እንድትታይ ያደርጋታል። በደርግ ጊዜ ጥበብ የአብዮቱ መቀስቀሻና ማታገያ ሆናለች። ይህ ልምድ ሕዝብን በብሔር ልዩነት ወደሚከፋፍለውና በተበድለሃል መንፈስ እርስ በርሱ ወደሚያላትመው ወደ ኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ስለመጣ ሥነ ጽሑፍም ላለፉት 27 ዓመታት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆና ቀጥላለች። እናም እንደነ ተስፋዬ ገብረ አብ በመሳሰሉት ፕሮፓጋንዲስቶች ጥበብ ከጥንተ ተፈጥሮዋ ከውበትና ከነጻነት ተገልላ፤ የሕዝብ ሰላምን፤ አንድነትንና ልማትን ችላ ብላ፤ ከከፍተኛው የክብር ማማዋ ላይ ወርዳ ወደ ተራ ቀስቃሽነት፤ ወደ ገንዘብ ቃራሚነት፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ወደሚያጋጨውና ወደሚለያየው ወደ ዘረኝነት እድታመራ ስትደረግ ቆይታለች። ተስፋዬ ገብረ አብን የወሰደው የጥላቻ ማዕበልም በጥርጣሬ ዓይን ያየው የነበረውን ኢሕዴግን ለማስደሰት፤ ለመሾምና ለመሸለም ነበር።
በሀገራችን በዘር ፖለቲካ ላይ በተመሠረተ ቅኝት በግፍ ታስረው የነበሩት፤ አካላዊ ቅጣት የተፈጸመባቸው፤ አካላዊ ጉድለት የደረሰባቸውና የሞት ፍርድ የተወሰነባቸው ወገኖቻችን ክቡር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ በየ እስር ቤቶች የመከራውን ገፈት ሲቀምሱና ሲሰቃዩ ኖረዋል። የፖለቲካ እሥረኞችን ቢፈቱም እነ ተስፋዬ ገብረ አብ በዘሩት የዘረኝነቱ ጥቃት ግን እስከ አሁን ሕዝቡ በመሰቃየት ላይ ነው፤ የግጭት እና ጦርነት አፋፍ ለማድረስ ሞክሯል፤ የመከራው ዘመን ገና የቆመ አይመስልም።
ዶክተር አንተነህ አወቀ እንዳሉት ለ ተስፋዬ ገብረ አብ አጻፋዊ መልስ ሊሰጡ በሚችል መልኩም የተቃኙ ሌሎች በፀረ ብሔርተኝነትና በፀረ ዘር ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ ሥላቃዊ የፖለቲካ ድርሰቶችን እናገኛለን። ለምሳሌ የበድሉ ዋቅጅራ « ኑ ሐውልት እንሥራ (የተስፋ ክትባት 2008.85) » የኤፍሬም ሥዩም «ኑ ግድግዳ እናፍርስ» ን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል። በ ተስፋዬ ገብረ አብ በተቃራኒ በዴርቶ ጋዳና ራማቶሐራ ዓፄ ቴዎድሮስና ዓፄ ምኒልክ ጀግናና የሕዝብ ተምሳሌት ሆነው ቀርበዋል። ሀገሪቱም ከ3000 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ እንዳላት ይገልጻሉ።
ዶክተር ተስፋየ ዳኘው ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በበኩላቸው በጉባኤው ላይ በአቀረቡት ምክረ ሐሳብ ሰዎች ስለ ሥነ ጽሑፍ መነጋገርና መከራከር ከጀመሩ ረጅም ዘመናት አልፈዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ሥነ ጽሑፍን በተመለከተ በቅጅ፤ በውበትና በእውነት መካከል ስለአለው ግንኙነት በአንድ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ውስጥ ስለሚገኙ አካላት አንድነት፤ ስለ ሥነ ጽሑፍ ማኅበራዊ፤ ፖለቲካዊና ሥነ ምግባራዊ ፋይዳዎች፤ ስለ ፍልስፍናና ንግግር ግንኙነት፤ድራማ በአንባቢዎች ዘንድ ስለሚኖረው ተጽዕኖ፤ ስለ ንግግር ዘይቤዎች ምንነት፤ ስለ ካኖንስ (ምስሎች)፤ ስለ ትራጄዲና ኮሜዲ ልዩነት መሠረታቸው የተጣለው በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ክላሲካል ወይም ዘመን አይሽሬ ተብሎ በሚጠራው ዘመን በነበሩ የግሪክ ፈላስፋዎች ነው።
ዶክተር ተስፋየ ዳኘው እንዳብራሩት በግሪኩ ፈላስፋ ፕሌቶ አመለካከት እውነት (ሐቅ) እንደ ሒሳብ/ጆኦሜትሪ ስሌት በምክንያት ላይ የተመሠረተ ነው። በፕሌቶ ሐሳባዊ ዓለም ሥነ ጥበብ የተፈጥሮ የቅጂ ቅጂ ስለሆነ ከእውነት ፈጽሞ የራቀ ነው። ሥነ ጥበብ ከምክንያታዊነት ይልቅ በስሜት ላይ ስለሚያተኩር ተቀባይነት የለውም ብሎ ያምናል። እንዲያውም በዘመኑ ደራሲዎችና ገጣሚዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት ሰዎች የተረጋጋ ማኅበራዊ ሥርዓትን ለማፍረስ ይችሉ ስለነበር ፕሌቶ ከእብዶች ጋር ያመሳስላቸዋል። ስለዚህ በግሪክ ሪፐብሊኮች ውስጥ ገጣሚዎች ቦታ እንዲኖራቸው አይፈቀድም ነበር። ፕሌቶም ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል ብሎ ያምን ነበር።
ይህ የፕሌቶ አስተሳሰብ ሥነ ጽሑፍ በማኅበረ ሰብ ላይ በሚኖረው ሚና ትኩረት እንዲደረግ በር ከፋች ሆነ። «ገጣሚዎች » በሚለው ሥራው የፕሌቶን ሐሳብ የተቃወመው የገዛ ተማሪው አሪስቶትል ነው። አሪስቶትል ሥነ ጥበብ ቅጂ ሳይሆን በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም እውነታ የሚያሳይ ጥበብ ነው ብሎ ያምን ነበር። በእርሱ አመለካከት የጥበብ ሰዎች የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም ተፈጥሮ የተሟላች እንድትሆን ሊያደርጓት ይችላሉ። አሪስቶትል ሥነጽሑፍን በመጠቀም በግማሽ ስሜታዊ የሆነውን የሰው የተፈጥሮ ባሕርይ የሠለጠነ እንዲሆን ለማድረግና ስሜትን በስሜት ለመግራት ይቻላል ብሎ ያምን ነበር። ዶክተር ዳኘው ይህንኑ በምሳሌ እንዳስረዱት አሪስቶትል ከፍተኛ የድራማ ዓይነት አድርጎ በሚተነትነው ትራጀዲ ውስጥ ካታርሲስ ወይም ፑርጌሽን የሚባል ጽንሰ ሐሳብ ያገኛል።
ይህም ጥልቅ ከሆነ ስሜት ተላቅቆ ከጭንቀት መውጣትና መገላገል እንደማለት ነው። ለአብነት ኦቴሎ በተባለው የዊልያም ሼክስፒር ትራጀዲ ውስጥ ኦቴሎ ሚስቱን ዴዝዲሞናን
በኢያጎ መሰሪነት መግደሉን ያየ ተመልካች በድንጋጤና በፍርሐት ይዋጣል። መጨረሻ ላይ ግን ተመልካቹ በትራጀዲው ይፈወሳል። እንደ ኦቴሎ በስሜት ተነድቶ ተመሳሳይ ድርጊት የመፈጸም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ይጠነቀቃል። ይህም ከላይ እንደተጠቆመው ካታርሲስ ወይም ፑርጌሽን ይባላል። ስለዚህ አሪስቶትል ትራጀዲ ማኅበረሰብን የመፈወስ ሚና አለው ብሎ በማስረዳት የመምህሩን የፕሌቶን ሐሳብ ይቃወማል።
የአፍሪካን ሥነጽሑፍ ታሪክ ስንመለከት በዐመፅ ላይ የተቃኘ ነው። ይኸውም አፍሪካውያን በባርነት ወደ ካሪቢያን ደሴቶች ከተጋዙበት ጊዜ ጋር ይያያዛል። እንደነ ኦላውዳህ እና ኢግናቲየስ ሳምቾ የመሳሰሉና በባርነት የተሸጡ አፍሪካውያን ግለ ታሪካቸውን ሥነ ጽሑፋዊ በሆነ መንገድ ጽፈው የነበረውን ኢ-ሰብአዊ ሁኔታ በማሳየት አውሮፓውያን በሕግ የተደነገገውን የባሪያ ንግድ ሥርዓት እንዲሰርዙ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርገዋል።
በቅኝ አገዛዝ ዘመን በፈረንሳይ ኔግሪቲዩድ በመባል በሚታወቀው የጥቁሮች እንቅስቃሴ እንደነ ሴዳር ሴንጎርና ኦስማን ሶሴ የመሳሰሉ ገጣሚዎች በፀረ ዘረኝነት ግጥሞቻቸው ለአፍሪካውያን ክብርና ለሀገሪቱ ነጻነት በብርቱ ታግለዋል። የማኅበረ ሰቡን ዶክተር ተስፋየ ዳኘ የልቦለድን ሥራ አስመልክተው እንዳወሱት የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ልቦለዶች በሚጻፉበት ወቅት ፖለቲካው የሥነ ጽሑፉን ሥራ መጫንና ማደብዘዝ የለበትም። የአንድ ልቦለድ ሥራ ሥነ ጽሑፋዊና ፖለቲካዊ ሚዛኑ ተጠብቆ እንዲሄድ ደራሲው ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ድርሰቱ የፖለቲካ መሣሪያ ከመሆንና ሕዝብን ከመከፋፈል ወጥቶ የተጨቆነው ማኅበረሰብ አጋር፤ መሪና መንገድ ጠራጊ መሆን አለበት። ምክንያቱም አንድ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ፕሮፓጋንዳ ከሆነ ጥበባዊ ባሕርይ ይለየዋልና ነው። እናም በትላንትናዋና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጨቋኝ ሥርዓትን ለመፋለምና ፍትሕንና ሰላምን በሕዝቡ መካከል ለማስፈን የሞከሩ ድርሰቶች የመኖራቸውን ያህል ሥነ ጽሑፍን በአፍራሽ መንገድ ቀይሰው ለአፍራሽ ተልእኮ ለማዋል የሚሞክሩ ደራሲዎች ከጥበብ የተፋቱና በዘረኝነት የዛር መንፈስ የተያዙ፤ ለሰው ልጅ ሰላም፤ እድገትና ብልጽግና የማያስቡ የአእምሮ ሕሙማን ናቸው።
በእርሳቸው እምነት በሀገራችን የአማርኛ ሥነ ጽሑፍም እንደዘመኑ ሁኔታ የተለየ ሚና ተጫውቷል። ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ እስከ 1950ዎቹ የነበረውን ሥነ ጽሑፍ አወዳሽ ነበር ብለውታል። ነገር ግን እንደ አርዓያና አደፍርስ በመሳሰሉ ልቦለዶችና በከበደ ሚካኤል ግጥሞች ለውጥን የሚደግፉና ዘመናዊነትን በሀገሪቱ የማስፋፋት አስፈላጊነትን የሚያመለክቱ ሥራዎችንም እናገኛለን። ከ1950 እስከ 1966 ሥነ ጽሑፍ ከነበረበት የአወዳሽነት መንፈስ ተላቅቆ የጊዜውን የለውጥ ፍላጎት በተለየ መንገድ አሳይቷል።
ዶክተር ተስፋየ የቴዎድሮስ ገብሬን ጥናታዊ ጽሑፍና ትንታኔ (2013) ጠቅሰው እንደተናገሩት በዚያ ወርቃማ የሥነ ጽሑፍ ዘመን ከተጻፉት ልቦለዶች ውስጥ ፍቅር እስከ መቃብር፤ የቴዎድሮስ ዕንባ፤ አደፍርስ፤ ከአድማስ ባሻገር እና ሌቱም አይነጋልኝ የተሰኙት ድርሰቶች በጊዜው የነበረው ትውልድ ስለ ሀገሩ ወቅታዊ ሁኔታና ስለመጭው ዘመን አደጋ እንዲያስብ አስችለዋል። እነዚህ ልቦለዶች ፖለቲካዊ ይዘት ቢኖራቸውም ጎልቶ የወጣው ግን ሥነ ጽሑፋዊ ይዘታቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ይዘታቸው ጎልቶ የወጣ እንደ አልወለድም ያሉ ድርሰቶችም እንደነበሩ አይዘነጋም።
ዘመን ሰኔ 2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር