ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከአባታቸው ፲ አለቃ መኮንን ይመር እና ከእናታቸው ወ/ሮ ሕይወት ይሕደጎ በትግራይ ክልል ምዕራብ ዞን አስገደ ፅምብላ ወረዳ በ1954 ዓ.ም ተወለዱ።
የትምህርት ሁኔታ
• በእንዳ አባ ጉና ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፣
• በሽረ ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፣
• የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሎንዶን ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በማኔጅሜንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በኢንፎርሜሽን እና ሊደርሺፕ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተምረዋል።
የትግል ጊዜ
• በ1969 ዓ.ምወደ ትግል ሜዳ በመቀላቀል በግንቦት የሥልጠና ማዕከል ሠልጥነዋል፤
• ከ1969 እስከ ታኅሣሥ 1971 ዓ.ም የ91ኛ እና 73ኛ ተራ ተዋጊ እና በጓድ አመራርነት፤
• ከታኅሣሥ 1971 እስከ 1972 ዓ.ም የሕውሓት የተሀድሶ አሃዱ ጋንታ አመራር፤
• ከታኅሣሥ 1972 እስከ 1973 ዓ. ምየ 573 እና 753 ቦጦሎኒዎች (ሻለቆች) ውስጥ የሻምበል መሪ፤
• ከ1974 እስከ 1975 ዓ.ም በብርጌድ 43 ውስጥ የሻለቃ አመራር በመሆን የኤርትራ የቀይ ኮከብ ዘመቻ አመራርነት፤
• ከጥር 1974 እስከ 1977 ዓ.ም በብርጌድ 43 እና 45 የሻለቃ አዛዥ፤
• በ1978 ዓ.ም የብርጌድ 78 ምክትል አዛዥ፤
• በጥር 1979 እስከ 1981 ዓ.ም የብርጌድ 70 አዛዥ፤
• ከመስከረም 1981 እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም የአውራአሮ ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን ትግሉን ለድል አብቅተዋል።
ከሽግግር ወቅት ጀምሮ
• በሽግግር ወቅት የምሥራቅ ዕዝ የዘመቻ ኃላፊ፤
• ከየካቲት 1987 ዓ.ም የኢፌዴሪ የምሥራቅ ዕዝ ም/ አዛዥ፤
• በግንቦት 1990 ዓ.ም የኤርትራ መንግሥት ሀገራችንን ሲወር የቡሬ ግንባር አዛዥ፤
• በየካቲት 1991 ዓ.ም በባድመ የዘመቻ ፀሐይ ግብዓት የግራ ክንፍ አዛዥ፤
• ከ1992 እስከ 1994 ዓ.ም 107ኛ ኮር ዋና አዛዥ፤
• ከ1994 እስከ 1997 ዓ.ም የሰሜን ግንባር ሀ እና አንድ አዛዥ፤
• ከ1997 እስከ 2006 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ፤
• ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም የመከላከያ የትምህርት እና የሥልጠና መምሪያ ኃላፊ፤
• ከመጋቢት 2010 እስከ ግንቦት 2010 ዓ.ም የጦር ኃይሎችም/ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም፤
• ከግንቦት 2010 እስከ ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በመሆን ሀገራቸውን አገልግለዋል።
የቤተሰብ ሁኔታ
• ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ባለትዳር ሲሆኑ፤ ከባለቤታቸው ኮለኔል ፅጌ አለማየሁ አንድ ሴት እና አንድ ወንድ ልጆች አፍርተዋል።
• ጄኔራል ሰዓረ መኮንን በነበራቸው ከፍተኛ የትግል ተሳትፎ እና በተጫወቱት የላቀ የአመራር ሚና የኢፌዴሪ መንግሥት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚም ነበሩ።
በመጨረሻም
ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ወደ ትርምስ ለመክተት በተቀናበረውና ሙሉ በሙሉ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ/ሤራ ጥቃት ደርሶባቸው ሰኔ 15/2011 ዓ.ም ተሰውተዋል።
ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011