ዶክተር አምባቸው መኮንን በ1962 ዓ.ም ጎንደር ክፍለ ሀገር ጋይንት አውራጃ ታች ጋይንት ወረዳ ልዩ ስሙ አተቶ ኪዳነማርያም ተወለዱ።
የትምህርት ሁኔታ
• አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአተቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
• መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በታጠቅ ለሥራ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
• የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በንፋስ መውጫ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
• የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት ሳይንስ ፤
• የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከሁለት የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም ከደቡብ ኮሪያ በፐብሊክ ፖሊሲ እና ማኔጅመንት፣ በእንግሊዝ ኬንት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የፋናንስና ኢኮኖሚ ልማት አግኝተዋል።
• ፒ.ኤች.ዲ በእንግሊዝ ሀገር ኬንት ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት ሳይንስ በእጅግ ከፍተኛ መዓርግ አጠናቀዋል። በትምህርታቸውም ተፎካካሪና ተወዳዳሪ ተማሪ ነበሩ።
የትግል ጊዜ
• የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው ደርግን ለመጣል የተደረገውን ትግል ኢሕዴንን በ1982 ዓ.ም በመቀላቀል ብርቱ ኃላፊነትን ተወጥተዋል።
• ከትግሉ ማብቃት በኋላ በሽግግሩ ጊዜ የተሰጣቸውን ልዩ ልዩ ተልእኮዎች ተወጥተዋል።
የአመራርነት ጊዜያት
• ከ1982-88 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ታች ጋይንትና ፋርጣ ወረዳዎች፣ በሰሜን ሸዋ ጣርማበርና ሀገረማርያም ከሰም ወረዳዎች በክፍለ ሕዝብነት፣
• ከ1991 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በአማራ ክልል ሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር፣
• በ1993 የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት/ አ.ብ.ክ.መ/ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣
• ከ1994-95 ዓ.ም የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም የጥረት ኮርፖሬት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ፣
• ከ1996-97 ዓ.ም የአ.ብ.ክ.መ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣
• 2003-2005 ዓ.ም የአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት/አ.መ.ል.ድ/ ዋና ዳይሬክተር፣
• ከ2006-2008 ዓ.ም በምክትል ርዕሰ መስተዳዳር ደረጃ የአ.ብ.ክ.መ የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፣
• ከ2009-2011/ጥር/ ዓ.ም ጀምሮ የኢ.ፊ.ዴ.ሪ የከተማ ልማትና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ በሚኒስትር መዓርግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ፣
• ከ2011 /የካቲት / ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ የአ.ብ.ክ.መ ፕሬዚዳንት ነበሩ።
ሌሎች ኃላፊነቶች
• ዶክተር አምባቸው ከመንግሥት ኃላፊነታቸው በተጨማሪ የታች ጋይንትን ሕዝብ በመወከል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት አባል፣ የአማራን ሕዝብን በመወከል የኢ.ፊ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ነበሩ።
• የአ.ዴ.ፓ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና አባል የኢህአዴግ ምክር ቤት እና ሥራ አስፈጻሚ አባል፣ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር ነበሩ።
• በቦርድ ሰብሳቢነት ደግሞ የአ.መ.ል.ድ፣ የቤቶች ልማት፣ የአማራ ቧንቧና ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የደብረ ታቦር ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ነበሩ።
• የኢትዮጵያ ምድር ባቡር፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የመብራት ኃይልን በቦርድ አባልነት ከማገልገላቸውም በላይ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተፈጽሞ የነበረውን ምዝበራና ብልሹ አሠራር በማጋለጥ በኩል ጉልህ ድርሻ ነበራቸው።
የጠባይና የአኗኗር ሁኔታ
• ሁሉን ያለልዩነት የሚወዱ፣ ሀገራቸውን ከልብ የሚወዱ፣ ደስተኛና ተጫዋች፣ የሰመረ ማህበራዊ ኑሮ ያላቸው፣ ለትዳራቸው ታማኝ፣ ብልሹ አሠራርን የሚጠየፉ፣ በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ከታገሉ ወሳኝ የኢሕአዴግ አመራሮች አንዱ ነበሩ። ዶክተር አምባቸው ባለትዳርና የአራት ሴቶች እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ።
በመጨረሻም
ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የአማራ ክልልንን እንደ ክልል ወደ ትርምስ ለመክተት በተቀናበረውና ሙሉ በሙሉ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ/ሤራ ከሁለት ሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ጥቃት ደርሶባቸው ሰኔ 15/2011 ዓ.ም ተሰውተዋል።
ዘመን መጽሔት፤ ለሰጡን ቃለ ምል ልስ እናመሰግናለን!
ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011