የኃይል አማራጭን የሚፀየፍ ትውልድና አገር ለመገንባት

የሕዝብ እንደራሴዎች በተወካዮች ምከር ቤት ተሰይመዋል። ስለ አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እያነሱ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። በምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገኝተዋል። ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ማስታወሻ ይይዛሉ። በዚህ መሃል ነው ሰላምን የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች መንሸራሸር የጀመሩት።

አንድ ከደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የቁጫ ብሔረሰብ የወከሉ የምክር ቤቱ አባል ጥያቄዎቻቸውን ማቅረብ ጀመሩ። ዜጎች መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው፣ ባህል ወጋቸውን በመከተላቸው፤ እራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር በመፈለጋቸው ምክንያት በምላሹ ድምፃቸው እንደታፈነ፣ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች እንደተገደሉ የተለያዩ ወከባ እንደሚደርስባቸው አና ሌሎችም ጉዳዮችን በማጣቀስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት አሉ።

በመቀጠል የዘይሴ ብሔረሰብ የወከሉ የምክር ቤት አባል እንዲሁ ተመሳሳይ ጥያቄ አስከተሉ። የወከሉት ሕዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርብም በምላሹ ግጭት፣ መፈናቀል፣ ግድያ እና ሌሎችም መሰል ችግሮች እየገጠሙት እንደሆነ አነሱ። በአካባቢው ሰላም አለመኖሩን የፀጥታ ኃይሎች በሕዝቡ ላይ በደል እያደረሱ መሆኑን ጠቁመው የፌደራል መንግስት እልባት እንዲሰጣቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን አቀረቡ።

የሁለቱ ብሔረሰቦች ተወካዮች ያነሱትን ቅሬታ ተቃውመው ግጭቱን ከማርገብ ይልቅ በእሳት ላይ ጋዝ እየጨመሩ ነው የሚል ሌላ ተቃውሞ ከአንድ የምክር ቤት አባል ተነስቶ ነበር። የቀረቡት አሳሳች መረጃዎች ለሰላም መፍትሄ ሳይሆኑ ግጭትን ይበልጥ የሚያባብሱና በውስጣቸው ሴራ የያዙ መሆኑንም በመግለፅ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ተወካዮቹ ሕዝብን አወያይቶ ሰላም ለማምጣት ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸውና የወከላቸውን ማህበረሰብ ኃላፊነት እንዳልተወጡ በመጥቀስ በቸልተኝነት ክስ ቀርቦባቸዋል።

በሌላ በኩል ከአማራ ከልል የተወከሉ የምክር ቤቱ አንድ አባል በበኩላቸው የመጡበትን ክልል ጨምሮ በልዩ ልዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት፣ ጦርነት፣ መፈናቀል እና ሞት፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የአገሪቱን ሰላም ማደፍረሱን፣ ኢኮኖሚውን ማድቀቁን፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመስራት እንዳይችሉ መገደቡን በማንሳት መንግስት የሰላም ባንዲራን በማውለብለብ ሆደ ሰፊነቱን እንዲያሳይ፣ ከታጣቂዎች ጋር ለመደራደር ለምን አይሞክርም የሚል ጥያቄን አስከተሉ። መንግስት የኃይል አማራጭን ወደጎን ትቶ ትጥቅ ካነገቡ ኃይሎች ጋር ለመደራደር ያለው ቁርጠኝነትን ጠየቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በቂ ማብራሪያ መስጠታቸውን በወቅቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተላለፈውን የምክር ቤቱ ስብሰባ ስንከታተል ሰምተናል። መንግስታቸው በአገሪቱ የሰላም አየር እንዲሰፍን ፍፁም ቁርጠኛ መሆናቸውን ያሳዩ ምላሾችና መሬት የተከሰተውን እውነታ ገላልጠው ሲያስረዱ አድምጠናል። የሰላም እጦት የአገሪቱን እድገት አንዴት አንደጎዳው፣ ግጭት፣ የትጥቅ ትግል ምን ያህል ወደ ኋላ እንዳስቀረን በዝርዝር ተናግረዋል።

መንግስታቸው ዛሬም ነገም የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ አማራጭን እንደሚከተልና በዚያም ፍፁም እንደሚያምን አብራርተዋል። ረዘም ያሉ ዘመናትን በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሳለፉ ኃይሎች እራሳቸውንም፣ ሕዝቡንም አገሪቱንም ከመጉዳት ያለፈ የፈየዱት አንዳች እንኳን አለመኖሩን በማንሳት ወደ ሰላሙ መንገድ እንዲመጡና በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንዲመክሩ ገልፀዋል።

የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ እነዚህ ጉዳዮችን በወቅቱ በጥሞና ሲከታተል ነበር። ለዚህም ነው ከዚህ የሚከተሉትን ጉዳዮች በቅንነትና ፍፁም መፍትሄን በሚሻ አንደበት በዝርዝር ምልከታውን ለማስቀመጥ የወደደው። እርግጥ ነው አባቶቻችን ‹‹እሳት በሌለበት ጭስ አይታይም›› ይላሉ። በምክር ቤት የተነሱ የሰላም እጦት ችግር በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሉም፤ ጥያቄዎቹም መሰረት የላቸውም ብሎ መካድ አይቻልም። ግችሩ መሬት ላይ አለ። በተለያዩ ግዜያት ከሰላማዊ መንገድ የተለየ እሳቤን የያዙ ኃይሎች ስርዓትን ለማፍረስ፣ ማህበረሰብን እረፍት ለመንሳት ነፍጣቸውን መዝዘዋል። በውጤቱ ሰዎች ሞተዋል አሁንም እየሞቱ ነው። ሀብት ንብረት ወድሟል፤ አሁንም እየወደመ ነው። ዜጎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ይታገታሉ፤ አሁንም ይህ ስጋት እንዳለ ነው። ዜጎችን በማንነት፣ በክልል፣ ወረዳ፣ ልዩ ወረዳ አደረጃጀት ስም በመቀስቀስ ወደ ግጭት የሚከቱ አካሄዶችን የሚከተሉ በርካቶች ናቸው።

ሕዝብን እንወክላለን ያሉና ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚሰጥ አጀንዳ እንዳላቸው የሚናገሩ አካላት፤ ከሰላም ይልቅ ግጭትን፤ ከጠረጴዛ ይልቅ ምሽግን ምርጫቸው አድርገዋል። ለመሆኑ ይህ አካሄድ ምን ያህል ያዋጣል? ለሕዝቡ ወጥቶ መግባት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጠንከር ምን ያህል ጠቃሚ ነው? እኛ በጎጥ፣ ዘር እና በሌሎች በቀላል ውይይት ሊፈቱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ እሳት ስንጭር ዓለም በስልጣኔ፣ በእድገትና በዘመናዊነት እሩቅ ጥሎን እንደሄደ እንዴት ማወቅ ተሳነን? በቂ ችግር፣ በቂ ጠላት እያለን ነግቶ በመሸ ቁጥር እርስ በእርስ የሚያጋጩና የሚያባሉ ችግሮችን እየፈለፈልን የምናድረው ለምን ይሆን?

እነዚህ ጠያቄዎች ፍፁም ቅን ምላሽ ይፈልጋሉ። የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ግን ጥያቄዎቹ ከቅንነት የተለየ የረቀቀ ሳይንሳዊ ምርምር የሚፈልጉ ከባድ ችግሮች አለመሆናቸውን ያምናል። ፖለቲከኞች የትኛውንም አይነት የፍትሀዊነት፣ የዲሞክራሲ፣ የኢኮኖሚ የፖለቲካ ውክልና ጥያቄዎችን በተመለከተ መፍትሄ ለመስጠት የሰላሙን መንገድ መከተል ይኖርበታል።

እነዚህ አጀንዳዎች የግለሰቦችን፣ የማህበረሰብን በጥቅሉ የአገርን ሰላም ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። ከነፍጥ ይልቅ፣ ጠረጴዛን ምርጫ ማድረግ ይገባናል። በመንግስት በኩል የሰላም ፍላጎት መኖሩን እየተመለከትን ነው። ነፍጥ ያነገቡትን ብቻ ሳይሆን፣ የማንነትና የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ከሚያነሱ አካላት ጋር ሕጋዊና ሰላማዊ አካሄድን ለመከተል መንግስት እረጅም እርቀት እየተጓዘ ነው። ይህ ሆደ ሰፊነትን ያሳያል። በምክር ቤት ውስጥ የሰላምን ፍፁም አስፈላጊነትና የመንግስታቸውን ቀና ሀሳብ መሰረት አድርገው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ ሀሳብ ነው አበክረው ሲያነሱ ያደመጥነው።

‹‹መንግስት ለሰላም ምን ያህል ቁርጠኛ ነው። ለድርድርና ለመነጋገርስ ምን ያህል ተዘጋጅቷል›› በሚል ለተነሳው ቅን ጥያቄ በጎ ምላሽ አድምጠናል። ‹‹ከቻላችሁ እናንተም ቢሆን የማደራደር ኃላፊነቱን መውሰድ ትችላላችሁ እኛ ዝግጁ ነን›› የሚል ምላሽ እስከመስጠት የደረሰ ዝግጁነት መኖሩን ተመልክተናል። በመንግስት በኩል ይህንን ያህል ዝግጁነት ካለ፣ ማንኛውንም ጥያቄ ከኃይል ይልቅ በሰላም ለመፈታት የሚያስችል ሆደሰፊነት ከታየ ነፍጥን፣ ግጭትን ምርጫቸው ያደረጉ አካላት ምን ምክንያት ኖሯቸው ነው ወደ ሰላሙ መድረክ ለመምጣት ያልደፈሩት?

ዜጎች ይህንን ጥያቄ ደጋግመው ማንሳት ይኖርባቸዋል። ኃይልን ምርጫ ያደረጉ ኃይሎች (በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ) ወደ ሰላም መድረክ እንዲመጡ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል። ምከንያቱም ከዚህ የባሱ በርካታ የቤት ስራዎች አሉብን። አገራችንን ከኋላ ቀርነት የሚያላቅቁ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፍ ይኖርብናል። ከዓለም አገራት ጭራ ሳይሆን ፊት መቀመጥ ይኖርብናል። በቃጣናው እድገታችንን የሚፃረሩ፣ አንድነታችንን የሚጠሉ ኃይሎች እየተፈጠሩ ነው። የውስጥ ችግራችን ላይ ጋዝ የሚያርከፈክፉና በፍርስራሻችን ላይ የበላይነታቸውን ለመገንባት የሚታትሩ ዙሪያችንን ከበውናል። ለዚህ በራችን ክፍት መሆን አይጠበቅበትም።

ሰላምን ምርጫ ማድረግ ያለብን ጠላቶቻችን ሰለከበቡንም ብቻ አይደለም። የሰላም መንገድ፣ የውይይትና የምክክር አማራጭ ለፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች አያሌ ችግሮቻችን መከተል የሚኖርብን ሕዝባችን ይህ ስለሚገባው ነው። ኑሮውን ለማሻሻል ከሰላም በላይ ሌላ ምንም ስለማያስፈልግው ነው። አርሶ፣ ነግዶና ሸምቶ ኑሮውን ለመምራት ቅድሚያ ሰላምን ይሻል።

እርግጥ ነው ዲሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ ማህበረሰቡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እኩልነት ተጠቃሚ መሆን አለበት። ሰብዓዊ መብቶቹ መጠበቅ ይኖርበታል። እራሱን በራሱ በመረጠውና በድምፁ በወከለው አካል ሊተዳደር ይገባል። እነዚህን መበቶቹን እናስጠብቃለን የሚሉ ፖለቲከኞች እና ግለሰቦች ግን ውይይትን፣ ድርድርን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን መከተል ይኖርባቸዋል።

በዚህ ምክንያት ነው መንግስት በከፈተው የፖለቲካና የድርድር ምህዳሮች ውስጥ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ ያሉ ልዩነት ያላቸው ኃይሎች መሳተፍ የሚኖርባቸው። ጥያቄዎችን አጀንዳ ለማድረግ እና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በዲሞክራሲያዊ መንገድ፣ በድርድር (በሰጥቶ መቀበል መርህ) ዘላቂ እልባት እንዲያገኙ ዝግጁ መሆን አለባቸው።

የሕዝብ እንደራሴዎች በምክር ቤቱ ውስጥ የወከሉትን ማህበረሰብን ድምፅ ማሰማታቸውና ቅሬታቸውን ለመንግስት ማቅረባቸው አንዳች ስህተት የለበትም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በያዙበት ወቅት ሁሉም ድምፆች እና የልዩነት ሀሳቦች በምክር ቤቱ ውስጥ በዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ ሊሰሙ እንደሚገባ ቃል ገብተዋል። እነዚህ ድምፆች በእርግጥም እየተሰሙ ነው። ይሁን እንጂ ይህንን መንገድ ለቅቀው ነፍጥን ያነገቡ ኃይሎች አሉ። መንግስት አሁንም እነዚህ ኃይሎች ወደ መሰል የሰላም መድረኮች መጥተው ጥያቄዎቻቸውን በሰላምና በድርድር እንዲፈቱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀጥታ በሚተላለፍ መልእክት ጭምር ጥሪ እያስተላለፉ ነው። ለዚህ ነው የተከፈተውን ምህዳር መጠቀሙ ለሁሉም ወገን የሚበጅ እንደሆነ ለመግለፅ የምወደው።

እዚህ ጋር አንድ ጉዳይ ትኩረት ማግኘት እንዳለበት አምናለሁ። እርሱም ሕዝባቸውን ወከልው በምክር ቤቱ ውስጥ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ጥያቀዎችን የሚያቀርቡ፣ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የሚሞግቱ አካላት ተጨማሪ ኃላፊነት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። የመጡበት ማህበረሰብ አካባቢ ለሚኖር ማንኛውም ከሰላም ያፈነገጠ፣ ግጭትን ምርጫው ያደረገ ኃይል ወደ ዲሞክራሲያዊ የሰላም አማራጮች እንዲመጣ ግፊት የማድረግ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል። የወከሉትን ሕዝብ በማወያየት ግጭትን አማራጭ ያደረጉ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር እና ውይይት እንዲመጡ መስራት አለባቸው።

ከሰሞኑ በተካሄደው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የሰማናቸው ልዩ ልዩ ድምፆች የሚያመለክቱት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በመንገድ ላይ መሆናችንን ነው። ይህ ሙሉ የሚሆነው ግን ሁሉም አካላት ሰላማዊ መንገድ ሲከተሉ ብቻ ነው። ‹‹በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል›› እንዲሉ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚነሱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የፍትህ ጥያቄዎች ሁሉም አካላት ሰለማዊ መድረኮችን የመጠቀም ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ከሌላቸው እየታየ ያለው የዲሞክራሲ ጭላንጭሉ መክሰሙ የማይቀር ነው። በዚህ ምክንያት የአገሪቱን ሰላም ለማስፈን፣ ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ፣ በቀጠናው ታላቅ ኃይል ሆኖ ለመውጣት፣ በዓለም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ላይ ከልዕለ ኃያላኖቹ ጋር ለመስተካከል የውስጥ ሰላማችንን እና የቤት ስራችንን በአግባቡ እልባት መስጠት እንዳለብን አምናለሁ። ሰላም !!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You