እግር ኳሱን ከወደቀበት ለማንሳት…

ከዓመት ዓመት ከትልልቅ የአሕጉሪቱ የውድድር መድረኮች እየራቀ የመጣው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከመሻሻል ይልቅ እየተዳከመ እንደመጣ የአደባባይ ምስጢር ነው። ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሱ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ። ከነዚህም መካከል ጠንካራ አመራር ማጣት፣ ስፖርቱ ከባለሙያዎች እጅ ወጥቶ ጥቅም በሚያሳድዱ ግለሰቦች እጅ መውደቅ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ችግር፣ የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክቶች ውጤት አልባ መሆን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። እነዚህ ምክንያቶች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ማነቆ ሆነው የቁልቁለት ጉዞውን የሚያፋጥኑ ጉዳዮች እንደሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ችግር ሰፊ እና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም በመንግሥት ደረጃ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ይኖርበታል። በተለይም በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ጥያቄ እንደማቅረቧ ከወዲሁ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የእግር ኳሱን ተረካቢና ተተኪዎች ለማፍራት ታዳጊዎች ላይ መሠራት እንደሚገባ ብዙ ጊዜ ሲነሳ ቆይቷል። ከክለቦች ውጤት አልባ አሕጉራዊ ተሳትፎ አልፎ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለሚታየው የውጤት ማሽቆልቆል፣ በተሰጥዖ፣ ቴክኒክና ታክቲክ እንዲሁም በአካል ብቃት የዳበሩ ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ማፍራት አለመቻሉ ዋነኛው ችግር በመሆኑ ሊጤን ይገባል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁት አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ የእግር ኳሱን እድገት የጎተቱትን ችግሮች ለመቅረፍ ሰፊ ጥናትና ምርምር እንደሚያስፈልግና ታዳጊዎች ላይ መሠራት እንዳለበት ተናግረው ነበር። አሠልጣኙ በብሔራዊ ቡድን የሠሩትን ታሪክ ለመድገም እና የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማከም፣ የታዳጊ እግር ኳስ ፕሮጀክት ከፍተው እየሠሩም ይገኛሉ፡፡

በፕሮጀክቶች አልፈው በማሠልጠኛ ማዕከላት እና አካዳሚዎች ሠልጥነው በትክክለኛው እድሜ የሚወጡ ስፖርተኞች ለዘመናዊ እግር ኳስ የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች የመያዝ ዕድል አላቸው። በሀገራችን ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። ከክለብ አልፈው በብሔራዊ ቡድንም ጭምር የሚጫወቱት አብዛኞቹ ተጫዋቾች እግር ኳስን የሚጫወቱት በራሳቸው ተነሳሽነት እና በልምድ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው ከታዳጊነት እድሜ ጀምረው፣ በእውቀት የተደገፈ እንዲሁም ሳይንሳዊና መሠረታዊ የእግር ኳስ ሥልጠናዎችን ማግኘት ባለመቻላቸው ነው። በሳይንሳዊ መንገድ የተደገፈ ሥልጠናን በተገቢው እድሜ የሚያገኙ ቢሆን እግር ኳሱን አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግና ኢትዮጵያን በዓለም ተፎካካሪ ማድረግ የሚችል አቅም እንዳለ ግን የሚካድ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከልማዳዊ አሠራር ወጥቶ ዘመኑ የሚፈልገውን አሠራር መዘርጋትና የእግር ኳሱን እድገት የሚያፋጥኑ መንገዶችን መከተል ይኖርበታል። ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች በሙሉ እንደየደረጃቸው ለውጤት ማሽቆልቆል ሚና ቢኖራቸውም ትልቁን ስፍራ የሚይዘው የአሠራር ሥርዓት ነውና በቶሎ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል። የተበላሸና የትም የማያደርስ የእግር ኳስ ሥርዓት ይዞ የተቀሩት ችግሮች ላይ መሥራት ፈታኝ በመሆኑ ከመዋቅር ጀምሮ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን መፈተሽ ለነገ የሚባል አይደለም።

አሁን ላይ በዓለም ስመ ጥር የሆኑት የእግር ኳስ ከዋክብቶች ከታዳጊነታቸው አንስቶ በጥሩ የእግር ኳስ ሥርዓት ውስጥ አልፈው ውጤታማ መሆናቸው እውን ነው። እኛም ታዳጊዎች ላይ ስር ነቀል የሆነ ሥራን በመሥራት የስፖርት ቤተሰቡ የሚናፍቀውን የእግር ኳስ ውጤት ለመመለስ መሥራት ይኖርብናል፡፡

የዓለም እግር ኳስ አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰው ሀገራት በዘረጉት ምቹ አሠራር እና ታዳጊዎች ላይ ሰፊና ቀጣይነት ያለው ሥራ በመሠራቱ እንደሆነ የሚታይ ሐቅ ነው። የእግር ኳስ ተሰጥዖ ያላቸው ታዳጊዎችን በሳይንሳዊ እውቀት አስደግፎና ያላቸውን ክህሎት የሚያጎለብቱ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶችን ለመፍጠር መረባረብ ይኖርብናል።

እግር ኳስ ክለቦች የራሳቸው የሆነ የታዳጊ ልማትን በተገቢው ሁኔታ አለመያዛቸውና ቢይዙም በክትትል ችሎታቸው ላቅ ያሉ ተጫዋቾችን ለማፍራት ሲቸገሩ እየታየ ነው። በመንግሥትም በኩል የተከፈቱ ፕሮጀክቶች የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አልቻሉም። በየእድሜ ደረጃው ታዳጊዎች ላይ የሚሠሩ ጥቂት ክለቦች ቢኖሩም ደፍረው ዕድል በመስጠትና በማሳደግ ረገድ ግን ብዙ ርቀት አይጓዙም።

በኢትዮጵያም በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ባሉት ታዳጊዎች ላይ ምልመላ በማድረግ የሚያሠለጥኑ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና ድንቅ ጊዜን ማሳለፍ የቻለው የመሐል ሜዳ ተጫዋቹ ዳዊት እስጢፋኖስ እድሜያቸው ከአምስት እስከ አስራ አምስት የሆኑ ታዳጊዎችን እና በስሩ አራት የሚሆኑ አሠልጣኞችን ይዞ ለመጪው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ግብዓት የሚሆኑ ታዳጊዎችን ለማፍራት ከሚንቀሳቀሱት ውስጥ ተጠቃሽ ነው።

ልክ እንደ ዳዊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከወደቀበት ተነስቶ እንዲያድግ ዝቅ ብለው ታዳጊዎች ላይ መሥራት ያለባቸው ብዙ ባለሙያዎች አሉ። ያም ሆኖ ይህ የቤት ሥራ በግለሰቦች ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም።ከፌዴሬሽን በተጨማሪ መንግሥትም ለችግሩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በቅርብ ክትትል መሥራት አለበት።

በታዳጊዎች ትክክለኛ እድሜ ላይ በንቃት በመሥራት ረገድ ክለቦች ያሉባቸውን በርካታ ችግሮች ቀርፈው በትክክለኛው ሐዲድ ላይ ሊጓዙ ይገባል። ክለቦች የሚታየውን ችግር መቅረፍ ብቻ ሳይሆን ያለፉባቸው ታዳጊዎች ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። በዚህ ረገድ በጣት የሚቆጠሩ ክለቦች በየጊዜው ታዳጊዎችን ወደ ዋናው ቡድን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት ሊደነቅ ይገባል። ሌሎችም በርካታ ክለቦች ረብጣ ገንዘብ እያወጡ ተጫዋቾች ከመግዛት ይልቅ ፊታቸውን ወደ ታዳጊዎች ሊመልሱ ይገባል።

ሌላው የእግር ኳሱ ዋነኛ ችግር የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት መሆኑ ይታወቃል። ይህ ችግር በተለይም ለታዳጊዎች ሥልጠና ፈተና መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። በዚህ ምክንያት በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ታዳጊዎችን ለይቶ ለማሠልጠን እንዳልቻሉም ባለሙያዎች ዘወትር ቅሬታ ያቀርባሉ። እንደ ችግሩ ስፋት እና ግዝፈትም ሊሰጠው የሚገባው ትኩረት አልተሰጠውም።

በቅርብ ጊዜ ይሄን ችግር ለመፍታት በመዲናዋ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት፣ የተሠሩ ትናንሽ የእግር ኳስ ሜዳዎች ቢኖሩም፣ ከከተማው ነዋሪ ቁጥር አንፃር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ስለዚህም ከመንግሥት በተጨማሪ ባለሀብቶችም በየአካባቢያቸው የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመገንባት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ለእግር ካሱ ትንሳዔ የራሳቸውን ዐሻራ ሊያሳርፉ ይገባል፡፡

ማሕሌት ጋሻው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You