ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነቶች፣ የፖለቲካ ቀውስና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ መግባባትን ለመፍጠር የሚደረግበት ሂደት ነው። ውጤታማ የሆነ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች መለየትና በአጀንዳዎች ላይ ከመግባባት ላይ መድረስ እንደሆነ ይነገራል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በሐረር፣ በአፋር፣ በሱማሌ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን መቻሉን አስታውቋል።
ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኅብረተሰብ ተወካዮችና የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አስጀምሯል። እስከ ጥቅምት 30 በሚከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ፤ በክልሉ ከሚገኙ 57 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮችን የተመረጡ ከ2ሺ 200 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ወኪሎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ከካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ የንግድ ማኅበረሰቡን ወክለው በመድረኩ የተገኙት አቶ ሳሕሌ ገብረሥላሴ እንደሚገልጹት፤ በንግግር፣ በምክክርና ቀርቦ በመወያየት የማይፈታ ችግር የለም። ኢትዮጵያ ብዙ የግጭትና የአለመግባባት ጊዜያትን አሳልፋለች ነገር ግን ይህ አይገባትም። የዚህ ምክንያትም ታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ቀርቦ ስላለበት ሁኔታና ስለአኗኗሩ መነጋገር ባለመቻሉ ነው።
ለዚህም መንግሥት የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈታው በምክክር እንደሆነ በማመን ዜጎችን ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በማሰባሰብ ይህንን የምክክር መድረክ በማዘጋጀቱ ምስጋናቸውን የቸሩት አቶ ሳሕሌ፤ በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ማኅበረሰባቸውን ወክለው በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ሳሕሌ ገለጻ፤ ኅብረተሰቡ በውስጡ የሚስተዋሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የተለያዩ ችግሮችን እንዲፈቱለት ከፍተኛ ፍላጎት አለው። በቀጣይም የክልሉ ማኅበረሰብ በችግሮቹ ዙሪያ በጋራ የሚመካከርበት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትስስሮች የሚፈጠሩበት ይሆናል ብለው ይጠብቃሉ።
የካፋ ማኅበረሰብ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር እኩል የመልማት ጥያቄዎችን ያነሳል። ለአብነትም ካፋና አከባቢው በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ቢሆንም ዜጎች ከዚህ ሀብት ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም። በዚህ የምክክር ሂደትም በአካባቢ የሚስተዋሉ ሁሉም ችግሮች ተፈተው በመላው ኢትዮጵያ ሠላምና ልማት እንደሚመጣ እምነታቸው የጎላ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ የማኅበረሰብ መሪ በመሆን በምክክሩ ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙት ሻንቆ ጋኪናስ እንደሚጠቁሙት፤ ማኅበረሰቡ ወደኋላ በመመለስ አባቶቹ ያሳለፉትን የኑሮ ሁኔታ ዞር ብሎ ብመለከት ብዙ ችግሮችን ተፈጥረዋል። በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ውስጥ በየጊዜው ችግሮች ሲፈጠሩ ነበር ነገር ግን እነዛ ችግሮች በውይይት ሲፈቱ ቆይተዋል።
በዓድዋ ጦርነት ወቅትም ሀገር ስትወረር አባቶቻችን የውስጥ ችግሮቻቸውን ወደጎን በመተው ለሀገር ዘምተዋል ይህ የምክክር ሂደትም በተጨባጭ አሁን ላለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አስፈላጊ መሆኑ የማይካድ ነው የሚሉት አቶ ሻንቆ፤ መንግሥትም ሆነ ወደትጥቅ ትግል የገቡ ኃይሎች የሀገርን ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነት በማጽናት ለመጭው ትውልድ ሠላማዊትና በኢኮኖሚ እድገት የበለፀገች ሀገር ለማስተላለፍ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው ይላሉ።
እንደ አቶ ሻንቆ ገለጻ፤ በእንደዚህ አይነት መልኩ ተሰብስቦ ችግሮችን የመፍታት ዝንባሌ ማዳበርም ሁሉን አቀፍና አካታች ሠላም ለማምጣት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ለዚህም የሀገር ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ መንግሥትም፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ቡድኖችም በሕግ ጥላ ስር ሆነው በጋራና በነፃነት በመመካከር የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይትና በምክክር በመፍታት የተረጋጋች ሀገር ለትውልዱ አስረክቦ ማለፍ ይቻላል።
ትውልድ ሲያልፍ ትውልድ ይተካል እኛም አልፈን ሌላ ትውልድ መተካቱ አይቀርም። ግጭት ካለ ሕይወት ማጣት፣ የንብረት ውድመት፣ የሀገር ቅርስ ማጥፋትና ሌሎችም በርካታ ችግሮች መከሰታቸው የማይቀር ነው። በዚህ የምክክር ሂደትም ከየአቅጣጫዎች መረጃዎች የሚመጡ በመሆናቸው በእነኝህ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ የሀገርን ሠላም ማጽናት የዜግነት ግዴታችን ነው ሲሉ አቶ ሻንቆ ያስገነዝባሉ።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም የሀገርና የሕዝብ አደራ ያለባቸው በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚበጅ የዜጎችን አንድነትና አብሮነት ማጠናከር የሚችሉ አጀንዳዎችን ሊያዋጡ እንደሚገባም አቶ ሻንቆ ያወሳሉ።
ከሸካ ዞን ጌጫ ወረዳ አንድራቻ ከተማ ሴቶችን በመወከል ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙት ወይዘሮ ሠናይት ያውዶ በበኩላቸው፤ በተለይም በገጠር አከባቢ የሚገኙ በርካታ ሴቶች ችግር ይደርስባቸዋል እነኝህ ችግሮች እንዲፈቱና ጥንት የነበረውን ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናት ምክክሩ እንደሚጠቅም ይናገራሉ።
ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመቻቻል የውጭ ጠላትን ለመመከት በአንድነት እናደርገው የነበረውን አብሮነት ዛሬም በመድገም ውስጣዊ ችግሮቻችንን በምክክር በመፍታት ለትውልዱ አንዲት ኢትዮጵያን ማስተላለፍ ይጠበቅብናል በማለት ወይዘሮ ሠናይት ይጠቁማሉ።
ወይዘሮ ሠናይት፤ በምክክር መድረኩ ተሳታፊ የሆኑ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ አካላት ግለሰባዊ ከሆነ አጀንዳ በመውጣት ሊያግባቡ በሚችሉና የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አጀንዳዎችን ማንሳት እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም