በኢትዮጵያ በፍልሰት የሚገቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከሚታይባቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባ ቀዳሚዋ ነች። ወደ አዲስ አበባ ከአራቱም አቅጣጫ በልዩ ልዩ ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ይጎርፋሉ። በዋናነት ግን ወደ ከተማዋ የሚመጡት ሰዎች ስራ ፍለጋን እንደ ምክንያት ያነሳሉ። በእርግጥ ከተሞች ከሌሎች አካባቢዎች በሚመጡ ዜጎች ጭምር በእድገታቸው ላይ በጎ ተፅእኖ ቢያሳድሩም፤ አንዳንድ አሉታዊ ነገርም አይጠፋም። አዲስ አበባም በእነዚህ ሁለተ ዋልታዎች ውስጥ ትገኛለች።
ወደ ከተማ (አዲስ አበባ) የሚደረገው ፍልሰት በተለይ የመኖሪያና የንግድ ቤት ኪራዮች ዋጋ እንዲንር መንስኤ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ደሞ ለህገ-ወጥነት በር ከፋች ሆኖ ቆይቷል። ከእነዚህ ድርጊቶች መካከል የመሬት ወረራ በቀዳሚነት ይገኝበታል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የወረዳና የክፍለ ከተማ ሹሞች እየተሳተፉበት ጭምር ደላሎች ያገኙትን ክፍት መሬት ሲቸረችሩ መቆየታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ህገወጥ ድርጊቱም ለዓመታት መፍትሄ ሳይበጅለት ቆይቷል ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መሬትን በመውረር በአቋራጭ ለመክበር የሚደረገው ጥረት እልባት እያገኘ ይመስላል። ችግሩን ለመቆጣጠር አሁን ላይ እየተሰማ ያለው ዜና በእርግጥም የህገ- ወጦችን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነው። እውነታው የመሬት ወረራ ግብዓተ መሬት ሊፈፀም ተቃርቧል ወደሚል መደምደሚያ ሊወስድ የሚችል ነው ።
ምስጋና ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ይግባውና ሕገ ወጥ ግንባታዎችና የመሬት ወረራዎች በቅርቡ እልባት ያገኛሉ፡፡ በየአስር ዓመቱ ማስተር ፕላን እየወጣላት ሲመረቅላት የነበረችው መዲናይቱ፤ ማስተር ፕላኑን በአግባቡ የሚተገብርና የሚያስተገብር ጠፍቶ በየእርከኑ ያሉ ደላሎችና ኃላፊዎች መሬቷን የሚቀራመቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ድርጊታቸውን ተከታትሎ ጥፋተኛ የሚያደርጋቸው ሀይ ባይ አልነበረም። በዚህ ምክንያት የከተማዋን ውበት የሚያበላሹ በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል።
በአንድ ወቅት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ‹‹የመሬት ወረራ የሚባል ካንሰር አለቀቀንም›› ብለው ነበር፡፡ አሁንስ ያ ካንሰር ይለቀን ይሆን? የካንሰር በሽታ በወቅቱ ካልደረሱበት በሕክምና የማይድን ነው፡፡ የመሬት ወረራም ሕገወጥ ግንባታም በወቅቱ እርምጃ ካልተወሰደበት በርግጥም እንደካንሰር የማይለቅ ነው፡፡
በወቅቱ የከተማዋ ማስፋፊያ አካባቢዎች ያሉ ስድስት ክፍለ ከተማዎች የመሬት ወረራው ቀላል በማይባል ደረጃ ደርሶ እንደነበር አምነው ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ የወረዳ አስፋፃሚ አካላት አመራሮች በንዋይ ፍቅር የታወሩ፣ በአድርባይነት የታጠሩ በመሆኑና ነገሮች አይተው እንዳላዩ ማለፋቸው ለተከሰቱት ችግሮች ዋነኛ ምክንያት እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ሕገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ፤ ሊባባስ የቻለው ርምጃው አሳፋሪዎችን (መሬት እንዲወረር ሰው እንዲሰፍር የሚፈቅዱትን) እየለቀቀ ሰፋሪዎችን ብቻ እያነቀ መያዙ ነው፡፡ ለሕገወጥ ግንባታ የሹመኛው ይሁንታ ነበረበት፡፡ መሬት ወረራና ሕገወጥ ግንባታ በመዲናዋ ሲፋፋም በፍጥነት ማስቆም ያልቻሉት ለምንድን ነው? የመሬት ወረራ ችግርን መግለጫ በመስጠት ብቻ ማቆም አይቻልም፡፡ እርምጃው የመሬት ወረራ እና ሕገወጥ ግንባታ በፈፀመ አካል ላይ ብቻ ሳይሆን ከዜጎች ገንዘብ እየሰበሰቡ ሕገወጥ ግንባታ ሲፈጸም አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ የሚያልፉ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡
የቤቱ ፍላጎትና ነዋሪው መጣጣም አልቻሉም። ብር ያላቸውም በህጋዊ መንገድ ቤት ተደራጅተው ሊገነቡ የሚችሉበት መንገድን ማመቻቸትም ሕገ ወጥ ግንባታንና የመሬት ወረራን መከላከል ነው፡፡ በባለሀብቶች እየተሠራ ያለው ግንባታ መካከለኛና ዝቅተኛ ነዋሪውን የዘነጋና የማያስጠጋ ነው፡፡
ሪል እስቴት ሕንፃዎች ሲገነቡ የተወሰነ ለድሀው ሊከራይ የሚችል መኖሪያ ቤት ቢገነቡ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ነው፡፡ ከሰሞኑ ለሕዝብ እንደራሴዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ቤት ማደስና መገንባት ተገቢ መሆኑን አንስተው የሰጡት ዝርዝር ሀሳብ አሁን ላለው ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ሀሳብ ነው።
ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በወጣ መረጃ በአዲስ አበባ የነበረውን ሕገወጥነት የሚያስቀር የመሬት ዲጂታላይዜሽን ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተረድተናል፡፡ የመሬት ወረራንና ሕገወጥ ግንባታን ለዘለቄታው ለመግታት የሚቻልበትን ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እየተተገበረ ነው፡፡ የመሬት ወረራውና ሕገ ወጥ ግንባታን የሚገታ ነገር ተፈጠረ ማለት ነው፡፡
ቀድሞ የመሬት ወረራና ሕገወጥ ግንባታ ሲካሄድና ግንባታው ሲበዛ ደግሞ ለማፍረስ ሙከራ ሲደረግ አይተናል፡፡ ነገሩ የልጆች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ይመስል ነበር፡፡ ደንብ አስከባሪዎች ከከተማዋ ዳር ሕገወጥ ግንባታ የሚገነቡትን ለማስቆም ሲጥሩ ነበር። አሁን ግን በከተማዋ ዳርቻ ለሚታየው የመሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታን የሚገታ መፍትሔ እየመጣ ነው፡፡
በአዲስ አበባ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሪፎርም፤ አሠራሩን ለማዘመን የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ተግባር፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የሚመራ ቡድን ጉብኝት አድርጎ ነበር።
የከተማው የመሬት ልማት አስተዳደር ባለሙያዎችና ኃላፊዎች በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ላይ በሰጡት ገለፃ፤ በቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ተቋማትን በድረ ግብር (ኔትወርክ) ማገናኘት፣ የሲስተም ልማትና የመረጃ ዲጅታላይዜሽን ሥራ ዘርፎች ዋነኛዎቹ ናቸው። የተቋሙ አደረጃጀት እና ቅንጅታዊ አሠራሮችም በሪፎሙ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑ ተብራርቷል።
ስለጉብኝቱ ከንቲባዋ በሰጡት መግለጫ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮው ብልሹ አሠራርና የተገልጋይ እንግልት የተንሰራፋበት እና በርካታ ውጣ ውረዶች የነበረበት ተቋም እንደነበር ተናግረዋል። የመሬት መረጃዎች በኮምፒውተር ስካን ተደርገው እንዲያዙ ዲጂታላይዝ እንዲደረጉ አዳዲስ ፋይሎች አስርጎ ማስገባት እንዳይቻል፣ አላግባብ መሬት የሚወስዱትን ለመቆጣጠር፤ ወደ ሲስተም እንዲገባ አገልግሎታችን ተደራሽ ጥራት ያለው ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
ወደ 40 ሺህ በላይ ተገልጋዮች በሲስተሙ መመዝገባቸው እየተገለፀ ነው፡፡ ፋይል ጠፋ የሚባለውን ነገር በዲጂታላይዝ እናስቀራለን፤ፋይል ተከፍቶለት መብቱ ተጠብቆለት ይኖራል፡፡ ከዚህ በኋላ በመሬት ዙሪያ ለማታለል የሚደረግ ነገር ይገታል ብለዋል፡፡ ዜጋው ውጭ ሀገርም ቢሆን ባለበት የመሬት ካርታ መረጃ የሚያገኝበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ በሪፎሙ የተዘረጋው ቴክኖሎጂ ከተማ አስተዳደሩ ያሉትን ሀብቶች በተገቢው እንዲያስተዳደር የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ሌብነትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ያስችላል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ የመሬት መረጃ በአግባቡ መዝግቦ ይዞ ማየት ችለናል፡፡ ይህ ለሌሎች ከተሞችም ተሞክሮ ነው፡፡ ለከተሞቻችን ከፍታም አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ቢሮው በቴክኖሎጁ የታገዘ አሠራር መዘርጋቱ ለአገልግሎት አሰጣጡ ምቹ መደላድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በመሬትና ልማት አስተዳደር ቢሮ የተቀናጀ መሬት አያያዝ ቡድን መሪ አቶ ፍፁም ኤልያስ በዚሁ ዙሪያ በሰጡን መረጃ የማኅደር ዲጂታላይዜሽን እና የስፓሻላይዝ መረጃ እየተካተተ ነው፡፡ ዋነኛው የማኅደርን ሥራ ፤ የማኅደር ስካን ነው፡፡ አዲስ አበባ እንደ አጠቃላይ የመሬት ተቋም ትልቁ ሀብቱ ማኅደር ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ማኅደር ከሰዎች ንክኪ ጠፋ ከሚባልበትም ቦታ ለማውጣት ትልቅ ሥራዎች ተሠርቷል፡፡
በዚህ ወደ 670 ሺህ በላይ ማኅደሮች ዲጂታላይዝ ተደርገዋል፡፡ መረጃዎቹ በ11 ክፍለ ከተሞች ተለይተው ወደ አንድ ቋት ገብተዋል፡፡ በመረጃ ቋት ውስጥ የገባ መረጃ ማንም ሊያጠፋው ሊሰርዘው ሊደልዘው አይችልም፡፡ ሰብስበን ለአገልግሎት ብቻ የምንጠቀምባቸው ናቸው። ይህም ደግሞ ከስም ጀምሮ ሁሉን መረጃ የያዘ በሰኮንድ መረጃ ማውጣት ማግኘት ይቻላል። ‹‹ማኅደሬ የለም፣ ማኅደር ጠፋ፣ ከማኅደሬ ላይ ንቅለ ተከላ ተደረገበት ፣ቅጽ ተቆርጦ ወጣ›› የሚሉ ሌሎችን በሙሉ እንደሚያስቀር ሰምተናል፡፡
አዲስ አበባ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የስፓይሻል መረጃዎችን በማደራጀት አንድ ማዕከላዊ ቤዝ ማፕ ፈጥራለች፡፡ ስለዚህ 11ዱም ክፍለ ከተማ የሚሠራ የትኛውም አገልግሎት የትኛው መብት ፣ የካሳ፣ የምትክ፣ የጨረታ ምደባ ቡድኖች በአንድ ማዕከላዊ ቤዝ ማፕ ላይ የሚወራረሱበት ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡
ይሄም ባለሙያው በሁለት መንገድ ታውቆ ወይም ሳያውቅ የሚሠራቸው ስህተቶች ለመከላከል ነው፡፡ ሳያውቅ የሚለውን ብንተወው አውቆ አላስፈላጊ የጥቅም ፍላጎት በማሳደር ሊፈጠር የሚችል አንድ ቦታ ላይ ሦስት አራት ካርታ ማውጣት፣ ቦታው ባለቤቱ ላልሆነ ግለሰብ መስጠት፣ የመሳሰሉት ነገሮችን እንደሚያስቀር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንድ ቦታ አንድ ክፍለ ከተማ ለአንድ ሰው ካርታ ተሠራ ማለት ሙሉ መረጃው ካርታው አጠቃላይ በሰከንድ ውስጥ በክፍለ ከተማው ያለው ነገር የሚታይበት ነው፡፡ ስለዚህ እዛ መሬት ላይ የሚፈጠር ነገር አይኖርም፡፡
በዚሁ ስፓይሻል ዳታ ላይ የመሬት ባንክ፣ ካሳ፣የመሬት ዝግጅት አብረው የተደራጁ መረጃዎች አሉ፡፡ በከተማችን ላይ ያሉ ክፍት ቦታዎች የተያዙበት፤ ለሚፈለገው ሥራ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ የተቻለበት ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ከተማዋ ላይ ያሉ ክፍት ቦታዎች ‹‹ለምን ለምን አገልግሎት ይውላሉ?›› የሚለውን መረጃዎች የቴዘበጠ በቀላሉ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ የተደራጀበት ሁኔታ ነው፡፡ በሐሰተኛ (ፎርጅድ) ካርታ ቤት መሸጥ አልያም ከባንክ ብድር ማግኘትም ዘበት ይሆናል፡፡
የትኛው አካባቢ ያለ መሬት ቦታ ባለቤት ካለው ማንም አይወረውም ፤ በዋናነት መንግሥት እያደረገ ያለው ቦታውን ማወቅ ባለቤትነቱን ማስከበር ነው። ቦታው ላይ ባለቤት እስከሆነ ድረስ ማንም መጥቶ አይወርም፡፡ ይሄን ለማረጋገጥ ያሉትን ክፍት ቦታዎች በሙሉ ተመዝግበው ተይዘዋል፡፡ የትኛውም ክፍለ ከተማና ወረዳ ላይ ያለች ክፍት ቦታ ምን ያህል ካሬ እንደሆነች ተመዝግቦ ኮድ ተሰጥቶት ተይዟል፡፡
ስለዚህ ክፍት ቦታዎች ተቆጥረው እስከተያዙ ድረስ የመሬት ወረራ የሚካሄድበት ሁኔታ የለም። የመሬት ወረራ ብዙ ጊዜ የሚካሄደው ባለቤት በሌላቸው ቦታዎች ነው፡፡ ጫካዎች፣ ደኖች፣ ወንዝ ዳርቻዎች በእነዚህ ቦታዎች በሙሉ ባህሪያቸው ለመሬት ወረራ ተጋላጭ ነበሩ፡፡ እነዚህን ቦታዎች ግን አንደኛ ልማት በማልማት ሁለተኛው ለልማት የማይበቁትን የመንግሥት እንደሆኑ ተሰፍረው ተለክተው መለያ ቁጥር ተሰጥቷቸው የሚቀመጡበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡
ሙሉ ለሙሉ ለማለት ባይቻልም ከዚህ በፊት የነበሩ በተለያየ ጊዜ በደቦ ፣በዘመቻ (mass Invasion) የሚደረጉ የመሬት ወረራዎች መቅረቱ የከተማዋ አመራሮች ይፋ አድርገዋል፡፡ በርግጥም በመዲናዋ የሚሠራው የመሬት ዲጂታላይዜሽን ሌሎች ከተሞች ሊማሩበት ይገባል፡፡ ለዚህ ነው የመሬት ወረራ ግብዓተ መሬት በቅርቡ ይፈፀማል የምለው!!
ይቤ.ከደጃች ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም