የታሪፍ ማሻሻያው ተግባራዊ ቁጥጥር ይጠናከር!!

የነዳች ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ በትራንስፖርት ዋጋ ላይ በቅርቡ ማስተካከያ መደረጉ ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ለተሠማሩ ሚኒ ባሶች፣ ሚኒ ባስ ታክሲዎችና የከተማ አውቶብሶች ላይ የአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የታሪፍ ማሻሻያው ከጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሲሆን፣ ከዚህ ቀን ጀምሮም አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል ።

የታሪፍ ማሻሻያው ወቅታዊ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ እና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን ያማከለ መሆኑን ቢሮው ገልጿል። የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች አዲስ በተሻሻለው ሕጋዊ ታሪፍ ተመን ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስቧል። ሕጋዊ ታሪፉን በሚተላለፉ አካላት ላይ ቢሮውና የሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ ርምጃ እንደሚወስዱም አስገንዝቦ ነበር፡፡ ህብረተሰቡም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ሲያጋጥሙ ለትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች፣ ለትራፊክ ፖሊሲና ባቅራቢያ ባለ የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በአካል ወይም በነፃ የስልክ መስመር 9417 ጥቆማ መስጠት ይችላሉ።

ይህ የተለመደና በየጊዜው በቢሮው በኩል የሚሰጥ መግለጫ ነው። እንዲህ አይነቱን መግለጫና ማሳሰቢያ ከመስጠት በዘለለ ታዲያ ሕጋዊ ታሪፉ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ተግባራዊ ቁጥጥር ማድረግና ከዚህ ውጪ ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲፈፀሙ አስተማሪና ሕጋዊ ርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። ለተግባራዊው ርምጃ አውን መሆን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና በተለይ የሕዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው።

እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ነው። የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ምርጫው ያደረገው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ በአብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ያለው እንደሆነ ይገመታል። ይህ ዝቀተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ለትራንስፖርት ክፍያ ወጪ የሚያደርገው ከእለት ጉርሱና ከቤት ኪራዩ ላይ ቀንሶ ነው። ከሚያገኛት ገቢ ላይ እየሸራረፈ ነው የትራንስፖርት ወጪውን የሚሸፍነው።

ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ ሁሉም ባይሆኑ አንዳንድ ስግብግብ የሚኒ ባስና ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች ከተቀመጠው ሕጋዊ ታሪፍ በተለይ ጨምረው የሚያስከፍሉ አሉ። ባቋራጭ ነው የምንሄደው፣ መንገዱ አይመችም፣ ነዳጅ ጨምሯል የሚሉና ሌሎች መሠረተ ቢስ ምክንያቶችን እየደረደሩ ከታሪፍ ውጪ ተጨማሪ ሂሳብ የሚያስከፍሉ በርካቶች ናቸው። በዚህ የተነሳ ታሪፉ አይደለም በሚል በረዳቶችና በተሳፋሪዎች መካከል ዱላ ቀረሽ ክርክሮች፣ ውዝግቦችና አለመግባባቶችን በየእለቱ መስማትና ማየትም ተለምዷል።

በዚህ አለመግባባትና ክርክር ደግሞ ተሳፋሪዎች ሰሚ አጥተው ከተጠየቁት ታሪፍ በላይ ከፍለው እየበገኑ ወደ ሥራ ገበታቸው አልያም ወደ ቤታቸው መግባት የዘወትር ሥራቸው ሆኗል። የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከከተማው ትራንስፖርት ቢሮው ዝርዝር የታሪፍ መረጃ የሚያሳይ ወረቀት በተሽከርካሪው ውስጥ ቢለጥፉም በታሪፉ መሠረት ተሳፋሪዎችን ሂሳብ ሲበሉ አይታዩም፡፡

በዚሁ ወረቀት ላይ ተሳፋሪዎች ከታሪፍ በላይ ሂሳብ ሲጠየቁ በነፃ የስልክ መስመርና በቢሮ ስልክ ደውለው ጥቆማ ለቢሮው እንዲያቀርቡ የሰፈረ ቢሆንም ችግሩ የገጠማቸው ተሳፋሪዎች ሲደውሉ ስልኮች እንደማይነሱም ነው ከብዙ ቅሬታ አቅራቢ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሚሰማው። ቢነሱም ቅሬታዎችን ሰምቶ አፋጣኝ ርምጃ ከመውሰድ አንፃር ክፍተቶች ይታያሉ።

ይህ ሲባል ግን በቀረቡ ጥቆማዎች መሠረት ሕጋዊና የእርምት ርምጃዎች እስካሁን ድረስ አልተወሰዱም ማለት አይደለም። ነገር ግን ርምጃዎቹ የአንድ ሰሞን ብቻ ናቸው፡፡ ተከታታይነትም የላቸውም፡፡ በቂም አይደሉም፡፡ ተገልጋዮች በሚያቀርቧቸው ጥቆማዎች መሠረት እነዚህ ርምጃዎች እየተወሰዱ እንኳን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በተለይ ሚኒ ባስ ታክሲዎች ከታሪፍ በላይ ማስከፈላቸውን አሁንም አላቆሙም።

አሁንም ቢሆን ፍራቻው በቢሮው በኩል እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች በተለሳለሰ ሆኑታ ከቀጠሉ ተገልጋዮች ከታሪፍ በላይ መጠየቃቸው አይቀሬ ነው። አንዳንድ የሕዝብ ትራንስፖር አገልግሎት ሰጪዎችም በዚህ የተለሳለሰ ውሳኔ የልብ ልብ ተሰምቷቸው ይህንኑ ሕገ ወጥ ተግባራቸውን መቀጠላቸውን አያቆሙም። በዚህ መሀል ደግሞ ምስኪኑና በዝቀተኛ ገቢ ራሱን የሚደጉመው የህብረተሰብ ክፍል ገቢው መናጋቱ አይቀርም ።

ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው ሚኒ ባስና ሚዲ ባስ ታክሲዎች ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ሲጠይቁ ጥቂት ተሳፋሪዎች ብቻ ናቸው ለመብታቸው የሚከራከሩት። እነዚሁ ጥቂት ለመብታቸው የሚከራከሩ ተሳፋሪዎችም በብዙሃኑ ተሳፋሪዎች ግልምጫና ተግሳፅ ሲደርስባቸው ነው የሚታየው። አብረዋቸው ከጎናቸው የሚቆሙና የሚከራከሩትም ጥቂት ናቸው። አብዛኛው ተሳፋሪ ለመብቱ ቆሞ ሲከራከርና ይህን ሕገወጥ ድርጊት በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ጥረት ሲያደርግና ሲቃወሙ አይታዩም፡፡ ከዚህ ይልቅ ነገሩን በቸልታ ሲያልፉና ምንም አናመጣም በሚል ተስፋ ሲቆርጡ ነው የሚታዩት።

ስለዚህ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ያልተገባ ታሪፍ ጨምረው ሲያስከፍሉ ለሚመለከተው አካል በመጠቆም ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድባቸው ከማድረግ ይልቅ ነገሩን በቸልታ ማለፍ ተገቢ አገልግሎት የማግኘት መብትን አሳልፎ መስጠት ነውና በተሳፋሪዎች በኩል ያለውን ችግር ማረም ያስፈልጋል። ገና ለገና በቢሮው በኩል የሚወሰደው ርምጃ የተለሳለሰና ውጤት የሚያመጣ ስላልሆነ ብቻ አገልግሎት ተጠቃሚው ማህበረሰብ ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚያደርገውን ጥቆማ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ሕጋዊና አስተማሪ ቅጣት እንዲወሰድ በማድረግ ረገድ ትልቁንና ዋናውን ድርሻ ሊወጣ የሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ነው። ቢሮው እስካሁን ድረስ ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ሲወስዳቸው የነበሩ ርምጃዎች እንዳሉ ሆነው አሁንም ቢሆን ይህን ርምጃውን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ።

በተለይ ደግሞ እንዲህ አይነት ያልተገቡ የታሪፍ ጭማሪዎች በትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ ተደርገው ወደቢሮው ጥቆማ ሲደርሱ ለጥቆማዎቹ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሚታይ፣ አስተማሪና ሕጋዊ የእርምት ርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም በድርጊት የሚገለፁና የሚታዩ ርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር ያልተገባ የዋጋ ታሪፍ ጨምረው የሚያስከፍሉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ወደሕጋዊ መስመር ስለሚመልስ ነው።

ምንም እንኳን በዚህ ጊዜ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ያልተገቡ የታሪፍ ጭማሪ ክፍያዎች መልካቸው ከጊዜ ወደጊዜ እየተለዋወጠና እየረቀቀ ቢመጣም በቢሮው በኩል የሚወሰዱ ርምጃዎች ይህን መሠረት ያደረጉ፣ ጊዜውን የዋጁና በጥናት የተደገፉ ሊሆኑ ይገባል። ይህ ሲሆን ጤናማና ፍትሃዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ይኖራል፡፡

ከዚህ ባሻገር በዚህ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሂደት የትራፊክ ፖሊሶች ያልተገባ የታሪፍ ዋጋ በተገልጋዮች ላይ እንዳይጨመር በመቆጣጠርና በመከላከል ረገድ ትልቅ ድርሻ አለባቸው። በተለይ የትራፊክ ፖሊሶች ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ተጠቃሚዎች ቅርብ እንደመሆናቸው ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ ተገልጋዮች ሲያጋጥማቸው ለቢሮው ከሚያደርጉት ጥቆማ በተጨማሪ ለትራፊክ ፖሊሶችም የሚጠቁሙበት እድል ስለሚኖረው ወደነርሱ ሲመጡ ቀና ትብብርና ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል። ከቻሉ ችግሩ እዛው እንዲፈታ ካልሆነ ደግሞ ለሚመለከተው ቁጥጥር አካል በመደወልና መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ መተባበር ይኖርባቸዋል።

እነዚህ ሶስት አካላት ማለትም የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ፣ አገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብና ትራፊክ ፖሊሶች በጋራና በቅንጅት ቢሠሩ ብሎም ያልተባ የታሪፍ ዋጋ ጭማሪ ሲታይ ሕጋዊና አስተማሪ ርምጃ ቢወሰድ በዚህ ረገድ የሚታየውን ችግር ማስቆም ይቻላል። ማቆም ባይቻል እንኳን መቀነስ ይቻላል ። ከዚሁ ጎን ለጎን ታዲያ በተቀመጠው ሕጋዊ የትራንስፖርት ታሪፍ መሠረት ተገልጋዩን ህብረተሰብ በቅንነትና በትጋት የሚያገለግሉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልሎት ሰጪዎችን ማድነቅ ተገቢ ነው። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ሕጋዊ ሥርዓትን ተከትለው የሚያገለግሉ ናቸውና!!

ሙዘይን ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You