የኒውዮርክ ማራቶን በታምራት ቶላና ጥሩነሽ ዲባባ ይደምቃሉ

ከዓለም ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የኒውዮርክ ማራቶን ነገ ለ53ኛ ጊዜ ይካሄዳል። ኢትዮጵያውያን የረጅም ርቀት ኮከብ አትሌቶችም በሁለቱም ፆታ ለአሸናፊነት የታጩ ሲሆን የውድድሩ ድምቀት በመሆንም ትኩረት አግኝተዋል።

የረጅም ርቀት የትራክ ውድድሮች የምንጊዜም ድንቅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በውጤት ከደመቀው ዘመኗ በኋላ በማራቶን ብዙ ታሪክ ትሠራለች የሚል እምነት ቢጣልባትም ከወሊድና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብዙ ርቀት አልተጓዘችም። ከመም ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ፊቷን በጎዳና ላይ ውድድሮች ካደረገች በኋላ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን ከአስር ዓመት በፊት በ2014 ለንደን ላይ ነበር ያደረገችው።

በዚያ ውድድር 2:20:35 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ካጠናቀቁት ኬንያውያን አትሌቶች ኤድና ኪፕላጋትና ፍሎሬንስ ኪፕላጋት በ11 ሰከንድ የዘገየ ሰዓት ነበር ያስመዘገበችው። በመጨረሻ ኪሎ ሜትሮች ውሃ ለማንሳት የፈጀባት ሠላሳ ሰከንድ ቀዳሚ ሆና እንዳታጠናቅቅ አንዱ ምክንያት እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ በኋላ ጥሩነሽ የመጀመሪያ ልጇን በመገላገሏ ለረጅም ጊዜ ከውድድር ርቃ ቆይታለች። ከዓመት በኋላ ዳግም ወደ ለንደን ማራቶን ብትመለስም አቋርጣ ነበር የወጣችው። ይሁን እንጂ በተመሳሳይ ዓመት በማንቸስተር 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ አሸንፋለች።

በዚያው ዓመት የበርሊን ማራቶን ደግሞ ሰዓቷን አሻሽላ በ2:18:55 ሦስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ በዴልሂ ግማሽ ማራቶን ደግሞ ስድስተኛ ነበረች። ከነዚህ ውድድሮች በኋላ ሁለተኛና ሦስተኛ ልጆቿን ከተገላገለች ከዓመታት በኋላ ወደ ውድድር የተመለሰችው በ2023 ሂውስተን ግማሽ ማራቶን ነበር። ይህን ውድድርም በ37 ዓመቷ 16ኛ ሆና አጠናቃለች። ተደጋጋሚ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ባለድሏ አትሌት ወደ ድንቅ አቋሟ ለመመለስ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በዚህ ወቅት በነገው የኒውዮርክ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ትፎካከራለች።

ከጥሩነሽ በተጨማሪ በዚህ ውድድር ኬንያዊቷ የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ አትሌት ሔለን ኦቢሪ፣ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሰንበሬ ተፈሪና ዴራ ዲዳ ለአሸናፊነት የሚያደርጉት ፉክክር በጉጉት ይጠበቃል። ጥሩነሽና ኦቢሪ በትራክ ውድድሮች የነበራቸውን የተፎካካሪነት ታሪክ በማራቶን ለመመልከት ብዙዎች ጓጉተዋል። ጥሩነሽ በረጅም ርቀት የነበራትን ድንቅ አቋም በማራቶን መድገም ባትችልም ኒውዮርክ ላይ በርቀቱ የመጀመሪያ ድሏን ለማጣጣም ትፎካከራለች። የቦስተን ማራቶን አሸናፊዋ ኦቢሪ የወቅቱ የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል።

በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር እንደሚፎካከር ከወራት በፊት ያሳወቀው የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ታምራት ያለፈው ዓመት የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ሲሆን የቦታውን ክብረወሰን በ2:04:58 ሰዓት ከአስራ ሁለት ዓመት በኋላ ማሻሻሉ አይዘነጋም። የ2022 የርቀቱ የዓለም ሻምፒዮን ዳግም ኒውዮርክ ላይ እንደሚፎካከር ከወራት በፊት ካረጋገጠ በኋላ በሰጠው አስተያየት፣ “የኦሊምፒክ ክብረወሰን አሻሽዬ ካሸነፍኩ በኋላ የኒውዮርክ ማራቶንን ክብር ለማስጠበቅ ዕድሉን በማግኘቴ ተደስቻለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር።

በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ ከዝግጅት ጀምሮ የነበረው ፈተና ዘንድሮ ኒውዮርክ ላይ የተሻለ ፈጣን ሰዓት ለመሮጥ እንደ ዝግጅት ሊጠቅመው እንደሚችልም ታምራት ተስፋ አለው።

ኢትዮጵያዊው አትሌት አዲሱ ጎበና እንዲሁም ባለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች በርቀቱ ሜዳሊያ ውስጥ በመግባት ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን ያስመሰከረው ቤልጂየማዊው አትሌት አብዲ በሽር የታምራት ብርቱ ተፎካካሪዎች ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ከሀምሳ ሺ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚሮጡ በሚጠበቅበት የነገር የኒውዮርክ ማራቶን በርቀቱ ከዚህ በፊት ማሸነፍ የቻሉ በአጠቃላይ 14 ፕሮፌሽናል አትሌቶች ተፎካካሪ ናቸው። ከወራት በፊት በፓሪስ ኦሊምፒክ የተሳተፉ 31 አትሌቶችም የፉክክሩ አካል እንደሚሆኑ የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You