እ.ኤ.አ በ2022 በወጣ መረጃ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ662 ሺ በላይ ሴቶች በማህፀን በር ካንሰር ይያዛሉ። ከ348 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ። ከሌሎች የካንሰር ዓይነቶች ጋር ሲነፃፀርም የማህፀን በር ካንሰር በአደገኛነቱና በመያዝ ምጣኔ በስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በገዳይነቱ ደግሞ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህፀን በር ካንሰር የሚያዙና የሚሞቱ ሴቶች ቁጥርም ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል።
በየዓመቱ በማህፀን በር ካንሰር ምክንያት ከሚከሰተው 348 ሺ ሞት ውስጥ 90 ከመቶው የሚሆነው ሞት የሚመዘገበው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ነው። በየሁለት ደቂቃውም ሁለት ሴቶች በማህፀን በር ካንሰር ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ። በየዓመቱ 8 ሺ 168 አዳዲስ የማህፀን በር ካንሰር ታማሚዎችና 5 ሺ 975 ሞቶች ይመዘገባሉ። በኢትዮጵያም የማህፀን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ለበርካታ ሴቶች ሞት ምክንያት ሆኗል።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የማህፀን በር ካንሰር ቡድን አስተባባሪ ሲስተር ታከለች ሞገስ እንደሚናገሩት፣ የማህፀን በር ካንሰር በማህፀን በር ዙሪያ ያሉ የሰውነት ህዋሳት ከተለመደው ውጪ ያለ ቁጥጥር ሲራቡና ሲያድጉ ይከሰታል። ይህም በየጊዜው እያደገና እየተሰራጨ የሚመጣ ቁስለትን እና እባጭን በማህፀን በር ላይ ይፈጥራል። የማህፀን በር ካንሰር መነሻ ምክንያቱ 99 ነጥብ 7 ከመቶ ‹‹ሂሙን ፓፒሎማ›› በተሰኘ ቫይረስ ነው። ይህም ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ ከ10 እስከ 20 ዓመት ይፈጃል። የሂውማን በፓፒሎማ ቫይረስ ( ኤች ፒ ቪ) በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት ስለሚተላለፍ ከአባለዘር በሽታዎች የሚመደብም ነው።
የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ደግሞ በማህፀን በር ዙሪያ ያሉ የሰውነት ህዋሳት ከተለመደው ውጪ ያለ ቁጥጥር መራባት ሲጀምሩ በማህፀን በር ዙሪያ ያሉ የሰውነት ክፍል የሚሸፍኑ ህዋሳት ላይ የሚመጣ እና በልየታ ምርመራ ወቅት በባለሙያ ሊታይ የሚችል ግልፅ ለውጥ ነው። የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች ብዙ ጊዜ ምንም የህመም ምልክት አያሳዩም። ነገር ግን በጊዜ ታውቆ ህክምና ካላገኙ ወደ ካንሰር ደረጃ ተሸጋግሮ ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ሊሆን ይችላል። የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር በጊዜ ከተለየ ካንሰር ደረጃ ሳይደርስ በቀላል ህክምና መታከምና መዳን ግን ይቻላል።
ይህ ከቅድመ ካንሰር እስከ ካንሰር ድረስ ያለው ከ10 እስከ 20 ዓመት የሚፈጅ ጊዜ መኖር በጊዜ ቀደም ብሎ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ለማድረግ፣ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምልክቶች የተገኘባቸውን ለመለየትና ለማከም መልካም እድል ይፈጥራል።
ለማህፀን በር ካንሰር አጋላጭ የሆኑ የተለያዩ መንስኤዎች ያሉ ሲሆን፣ ማንኛውም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽማ የምታውቅ ሴት ሁሉ ለማህጸን በር ካንሰር ዋነኛ መንስኤ ለሆነው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመጋለጥ አጋጣሚ አላት። በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ግን በሽታ መከላከል አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ሴቶች ለምሳሌ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ፣ የሰውነት በሽታ መከላከል አቅምን የሚቀንሱ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙና ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች ናቸው።
ብዙ ጥናቶች ሲጋራ ማጨስ በማህፀን በር ካንሰር የመጠቃት እድልን እንደሚጨምርም አሳይተዋል። እነዚህ እንዳሉ ሆነው ሌሎች ለማህፀን በር ካንሰር አጋላጭ መንስኤዎች አሉ። እነዚህም በልጅነት እድሜ (ከ20 ዓመት በታች ) ወሲባዊ ግንኙነት መጀመር፣ ከአንድ በላይ የወሲብ አጋሮች መኖር፣ እንዲሁም በሌሎች የአባላዘር ህመሞች መጠቃት ናቸው።
ሲስተር ታከለች እንደሚያብራሩት፣ የማህፀን በር ካንሰርን በተለያዩ መንገዶች መከላከል ይቻላል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከ 9 እስከ 13 ዓመት ለሆኑ ልጃገረዶች የሂማን ፓፒሎማ ቫይረስ /ኤች ፒ ቪ/ ክትባት መስጠት ነው። ልጃገረዶች ወሲባዊ ልምምድን ከመጀመራቸው በፊት ኤች ፒ ቪ ክትባት የሚያገኙ ከሆነ ማህፀን በር ካንሰርን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል። በሌላ በኩል ከ20 ዓመት በታች ያሉ ሴቶች የማህፀን በራቸው ያልዳበረና ኤች ፒ ቪ መስፋፋት አመቺ በመሆኑ ሴቶች ከ20 ዓመት በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዳይፈፅሙ / እንዳይጀምሩ ማስተማርም ሌላኛው የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ መንገድ ነው።
በሌላ በኩል የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ማድረግና የቅድመ ካንሰር ምልክት ለተገኘባቸው አፋጣኝ ህክምና ከተቻለ በዛው ቀን በመስጠትም የማህፀን በር ካንሰርን መከላከል ይቻላል። ሁሉንም እድሜያቸው ከ 30 እስከ 49 የሆኑ ሴቶች ማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ማድረግ፣ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ተደርጎላቸው ምልክቱ ያልተገኘባቸው፤ እድሜያቸው 49 ዓመት እስኪሆን ድረስ ከ 3 እስከ 5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተደጋጋሚ የልየታ/ምርመራ ማድረግም ለመከላከል ይረዳል።
ሁሉንም እድሜያቸው ከ 15 እስከ 49 የሆኑ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ማድረግ፣ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ተደርጎላቸው ምልክቱ ያልተገኘባቸው ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ሴቶች እድሜያቸው 49 ዓመት እስኪሆን ድረስ በየ 2 ዓመት ተደጋጋሚ የልየታ/ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸውም ይመከራል። በማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ወቅት የካንሰር ህመም ሊገኝባቸው ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች አስፈላጊውን ተጨማሪ ምርመራና ህክምና በትስስርና በቅብብሎሸ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል።
በተጨማሪ በምርመራው መሰረት ማህፀን በር ካንሰር እንዳለባቸው የታወቀ ሰዎች አስፈላጊውን ህክምና እንዲሁም ማህበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል። አንድ ለአንድ መወሰን፣ የአባለዘር በሽታዎችን መከላከል፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ ኮንዶምን ባግባቡ መጠቀምና የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ማዘግየት ተጨማሪ የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ዘዴዎች ናቸው።
የማህፀን ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ በሽታው ተባብሶ ለሕይወት አስጊ ከመሆኑ በፊት ታክሞ መዳን ይቻላል። የማህጸን በር ቅድመ ካንሰር ምልክት መኖር ያለመኖሩን ለመለየት የተለያዩ ምርመራዎች በሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎች ይደረጋሉ። ከማህፀን ቅድመ ካንሰር ምርመራ በኋላ ደግሞ የማህጸን በር የቅድመ ካንሰር ሕክምና ይኖራል። የማህጸን በር ቅድመ ካንሰር የህክምና አይነቶችም cryotherapy ( በቅዝቃዜ ማከም) እና thermal ablation( በሙቀት ማከም) በመባል የሚታወቁ ሲሆን ውጤታማም ናቸው። እነዚህ ህክምናዎችም በአብዛኞቹ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ በሚያደርጉ የጤና ተቋማት ይሰጣሉ።
ትንሽ መጠናቸው ከፍ ያለ የማህጸን በር ቅድመ ካንሰር ምልክት ለተገኘባቸው ህሙማን ደግሞ LEEP የሚባል ቅድመ ካንሰር ምልክት የተገኘበትን የማህፀን በር ክፍል ብቻ ቆርጦ የማውጣት ህክምና ይሰጣል። ታማሚዎችን ህክምናው ወደሚሰጥበት የጤና ተቋማት በቅብብሎሽ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል። በተጨማሪም በማህጸን በር ቅድመ ካንሰር የታከሙ ሰዎች ከ6 ወር እስከ አንድ ዓመት ውስጥ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ልየታ/ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ስር የሰደደ የማህፀን በር ካንሰር ሲያጋጥም ምልክቶቹን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። በተለይ የቅደመ ካንሰር ምርመራ በወቅቱ ካልተደረገ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች የህመሙ ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ። የማህፀን በር ካንሰር ሥር እስኪሰድ ድረስ ምንም ዓይነት ስሜትና ምልክት ሳይኖረው ከ15 እስከ 20 ዓመት ሊቆይ ይችላል። ከተባባሰ በኋላ ግን ከግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ ደም በብልት ይፈሳል። ይህ ሁኔታ የወር አበባ ባቋረጡ ሴቶች (በዕድሜ ምክንያት) ላይም ይከሰታል። ከዚህም ሌላ ያልተለመደ የማሕፀን ፈሳሽ በብዛት ይፈስሳል። በሽታው እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ የማህጸን አካባቢ ህመም ይኖራል። ሕመሙ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ሊሰማ ይችላል። ስለዚህ እነዚህ የህመም ምልክቶች ሲያጋጥሙ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ህክምና ማድረግ ይገባል።
እንደ ሲስተር ታከለች ገለፃ፣ የማህፀን በር ካንሰርን እ.ኤ.አ በ2030 የህብረተሰብ ጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ የሚያደርሰውን መንገድ ለመያዝ የዓለም ጤና ድርጅት የ 90 -70- 90 ስትራቴጂ አስቀምጧል። በዚህ ስትራቴጂ መሠረት ሀገራት 90 ከመቶ ያህል ከ9 እስከ 15 ዓመት ያሉ ልጃገረዶች የኤች ፒ ቪ ክትባት እንዲውስዱ፣ 70 ከመቶ እድሜያቸው ከ30 እስከ 49 ያሉ ሴቶች የቅድመ ማህፀን ካንሰር ልየታ እንዲያደርጉና 90 ከመቶ የቅድመ ማህፀን ካንሰር የተገኘባቸው ሴቶች ህክምና እንዲገኙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያም ይህን ስትራቴጂ ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባትን በሚመለከት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2023 ክትባቱን አስጀምራ እ.ኤ.አ እስከ 2024 ድረስ ከ7 ሚሊዮን 700 ሺ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው 14 ዓመት የሆናቸው ልጃገረዶች ተከትበዋል። አሁን ደግሞ እድሜያቸው ከ9 እስከ 13 ዓመት የሚሆናቸው ልጃገረዶች በመጪው ኅዳር ወር ክትባቱን ይወስዳሉ።
የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል በጤና ሚንስቴር በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከነዚህ ሥራዎች ውስጥ አንዱ የቅድመ ካንሰር ህክምናና ምርመራ አገልግሎት በ1 ሺ 450 ጤና ተቋማት ውስጥ እየተሰጠ መሆኑ ነው። ይህ ሥራም በጤና ሚንስቴር በኩል የተጀመረው በ2008 ዓ.ም ነው። በክልልም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተከናወኑ የሚገኝ ሲሆን ለአብነትም በኦሮሚያ 505 እንዲሁም በአማራ 390 በሚሆኑ ጤና ተቋማት ውስጥ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራና ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
እነዚህ የጤና ተቋማት ቢያንስ ለአስር ሰው የቅድመ ካንሰር ምርመራና ህክምና አገልግሎት ቢሰጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን ተደራሽ ማድረግ ይቻላል። ከ2007 እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ከ69 ሺ 972 እስከ 673 ሺ 96 ለሚጠጉ እናቶች የቅድመ ካንሰር ልየታና ምርመራ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። በክልል ደረጃም በኦሮሚያ ባለፈው ዓመት ብቻ ለ329 ሺ 685 ሴቶች የማህፀን ቅድመ ካንሰር ልየታና ምርመራ ተደርጓል።
ይህም ከሌሎች ክልሎች አንፃር ሲታይ ከፍተኛ አፈፃፀም ሆኖ ተመዝግቧል። በአማራ ክልል ለ78 ሺ 126፣ በአዲስ አበባ 96 ሺ 969 እንዲሁም ደቡብ ኢትዮጵያ 54 ሺ 619 ለሚሆኑ ሴቶች የማህፀን ቅድመ ካንሰር ልየታና ምርመራ በማድረግ እንደየቅደም ተከተላቸው ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ጥሩ አፈፃፀም አሳይተዋል። ከዚህ አንፃር የማህፀንን በር ካንሰርን ለመከላከል ወሳኙ ነገር የቅድመ ካንሰር ልየታና ምርመራ በመሆኑ ይህ ሥራ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም