አዲስ አበባ፡– አሁንም ያለን አቋም የትኛውም አይነት አለመግባባት በሠላም እንዲፈታ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትላንት በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሠላም አማራጭ ውጤቱ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት ግጭቶች በሠላም እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥቶ ሠርቷል ብለዋል፡፡ የኃይል አማራጭ ያልተገባ ጉዳት እንደሚያመጣ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ አሁንም ያለን አቋም የትኛውም አይነት አለመግባባት በሠላም እንዲፈታ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“ከማንም በላይ ሠላም እንፈልጋለን። ጦርነትን በተግባር እናውቀዋለን፤ አንፈልገውም። የትኛውም አካል በኃይል እና ጥላቻ መጠፋፋትን እንጂ ዓላማውን ማሳካት አይችልም። ሰከን ብሎ ማሳብ ይገባል። ሃሳብ አልባ ትግል ፍሬ የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሠላም ለልማት ሥራዎች አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በሀገሪቱ ላይ የሚጨበጥ ውጤት ለማምጣት ሕልም አለን በማለት፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሠላም እንደሚያስፈልግ ሠላምን በተሟላ ሁኔታ መረጋገጥ ካልተቻለ የሚታሰበውን እድገት ለማምጣት አስቸጋሪ እንደሚሆን አመላክተዋል።
መንግሥት የሠላም ጥሪን በተደጋጋሚ ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለንግግር ፍላጎቱ ለአላቸውና ማቀራረብ ለሚፈልጉ አካላትም የሠላም አማራጭ በሩ ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር እንዳለም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል አሁናዊ ሁኔታን አስመልክቶ በሰጡት ማባራሪያቸው፤ በክልሉ ላይ ከየትኛውም መንግሥት በላይ አሁን ያለው መንግሥት በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በአማራ ክልል ታላላቅ የመንገድ፣ የኢንዱስትሪ የቱሪዝም ልማቶች እየተከናወኑ እንዳለ አመላክተው፤ በዚህም ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የፋሲል ቤተመንግሥት በመታደስ ላይ መሆኑን፤ በክልሎች የተለያዩ ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተከናወነ እንዳለ ጠቅሰዋል።
መንግሥት የመገጭ ግድብን ሰባት ቢሊዮን ብር በመመደብ ከበርካታ ዓመታት የግንባታ መቋረጥ በኋላ በጠንካራ ክትትል እየገነባ እንዳለም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በክልሉ ልማት እንዳይከናወን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸውን አንስተዋል። ይህንን በትብብር ማስቆም እንደሚገባም አስገንዝ በዋል።
የአማራ ሕዝብ ማን እንደሚሠራለትና ማን እንደሚያ ወራለት ጠንቅቆ የሚያውቅ ጨዋ ሕዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ክልሉን የማልማት ሥራውን አሁንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን አስመልከቶ ባነሱት ሀሳብ፤ ኮሚሽኑ የተሻለ ስኬት እንዲያስመዘግብ የምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
ለተሐድሶ ኮሚሽንና እና ለሽግግር ፍትሕም መሰል ድጋፍ መደረግ እንዳለባት አመላክተዋል። ከዚህ ቀደም ከነበሩ ኮሚሽኖች ትምህርት በመውሰድ አሁን ያሉ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚገባና ከዚህ አኳያ መንግሥት እንደ አስፈጻሚ አካል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም