አዲስ አበባ፡- በሩብ ዓመቱ በዲጂታል የክፍያ አማራጮች ሶስት ነጥብ አንድ ትሪሊዮን ብር መዘዋወሩን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ። በሩብ ዓመቱ ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር መሰብሰቡና ለ488 ሺህ 624 ዜጎች በሀገር ውስጥ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተገልጿል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አጠቃላይ የሀገራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እና የተጠሪ ተቋማቱን የስራ አፈጻጸምን ትናንት ገምግሟል።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትንተናና ፖሊሲ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ አስፋው በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሩብ ዓመቱ በዲጂታል አማራጮች 640 ሚሊዮን ግብይቶችን በመፈጸም ሶስት ነጥብ አንድ ትሪሊዮን ብር በዲጂታል ተዘዋውሯል።
ባንኮች በዲጂታል የክፍያ አማራጮች ቁጠባ፣ ብድር እና ግብይት ያከናውናሉ ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ቁጠባ መደረጉን እንዲሁም አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ብድር መቅረቡን ጨምረው ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ዘመን ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች በማስተዋወቅና የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ የራቀ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይም ክፍያን የማዘመን ሥርዓት ተደራሽነቱን የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም የባንኮች ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ሁለት ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸው፤ የባንኮች ተደራሽነትና የዲጂታል አገልግሎት መስፋፋት የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ እንዲያድግ አግዟል ብለዋል።
በሌላ በኩል የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ የታክስ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝድ የማድረግ እና የማሻሻያ ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት 180 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 180 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 64 ነጥብ ስድስት በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸው፤ መንግሥት የግብር አሰባሰቡ ላይ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋቱ እንዲሁም የግብር ሥርዓቱን ከሙስናና ብልሹ አሰራር ለማጽዳት በተሰሩት ስራዎች የግብር ገቢውን ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በተጨማሪ ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሎች የሚከፋፈል 11 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር የጋራ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 18 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ረገድ በሶስት ወራት ውስጥ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያስመዘገቡ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ታቅዶ፤ 890 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ያስመዘገቡ 108 ኢንቨስተሮችን መሳብ መቻሉን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት 108 ኢንቨስተሮች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የአምራች ዘርፉ ሲሆን፤ 74ቱ በአምራች፣ 29ኙ በአገልግሎት አምስቱ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የሚሰማሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ በሩብ ዓመቱና በተለያየ ጊዜ ፈቃድ ከወሰዱት የውጭ ኢንቨስተሮች መካከል 52ቱ ግንባታ መጀመራቸውን ጠቁመው፤ 45ቱ ደግሞ ወደ ምርት መሸጋገራቸውን አስረድተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መጀመሩን ተከትሎ የውጪ ኢንቨስትሮች ከዚህ በፊት ብዙም ተሳትፎ በማያደርጉባቸው ዘርፎች መሳተፍ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
72 ኢንቨስትሮች በገቢና ወጪ ንግድ ለመሳተፍ ማመልከታቸውን ገልጸው፤ ለ11 ኢንቨስተሮች ፍቃድ ለመስጠት በሂደት ላይ መሆኑን አመላክተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም