በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ/ ካፒታል ገበያ/ ጉዳይ በስፋት ይነሳል። ገበያው በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም በእጅጉ ሲጠቆም የነበረ ሲሆን፣ ገበያው ለሀገር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብም መንግሥት በኢትዮጵያም እውን እንዲሆን እየሰራ ይገኛል።
ለመሆኑ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ማለት ምን ማለት ነው? የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉትም፤ ገበያው ለተቋማት የገንዘብ ምንጭ እና ማደግ፣ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) መጨመር እንዲሁም ለተሳለጠ የአክስዮን ግብይት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ገበያውን የሚመራ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተሰኘ ተቋም ተቋቁሞ መሥራት የጀመረ ሲሆን፣ በቅርቡም ገበያ ወደ ሥራ እንደሚገባም ይጠበቃል። ለዚህም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይቷል። በተለይም የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመቅሰም ለካፒታል ገበያው ጠንካራ ምህዳር እንዲፈጠር የሚመለከታቸው አካላት ሰርተዋል፤ እየሰሩም ይገኛሉ። በቅርቡም የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በሙዓለ ገበያ ላይ ከሚሰራው አይ ካፒታል ኢንስቲትዩትና ከኬንያው ኤንኤስኢ (Nairobi securities exchange) ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
በሰነደ ገበያው ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል እንዳሉት፤ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ማለት የሰነዶች ገበያ ሲሆን፤ ለአብነትም በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ወደ ገበያ ያመጣው የአክስዮን ሽያጭ አንዱ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አይነት ነው። ሌሎች ቦንዶች ከመንግሥት የሚወጣ እና ኩባንያዎች የሚያወጧቸው የዕዳ ሰነዶች ወይም ቦንዶች በአንድ ላይ ሲሰባሰቡ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ይባላሉ። ይህ ሀብት ደግሞ ገበያ ያስፈልገዋል። ይህን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው።
እስካሁን እስከ አራት መቶ ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን አክስዮን ገዝተዋል። ነገር ግን እንዴት ነው የሚገበያዩት ተብሎ ሲጠየቅ በማሕበራዊ ሚዲያ ዋጋ እያዩ፤ ዋናው የባንኩ መስሪያ ቤት እየሄዱ ገዢና ሻጭ ተፈላልገው ተገናኝተው፤ ገንዘብ በባንክ በኩል አስተላልፈውና ሰነደ ሙዓለ ነዋዩ ላይ ስማቸው እየተፋቀ መዝገቡ እየተቀየረ ነው።
ይህም ብዙ ጊዜ የሚወስድ ወጪ ያለው አካሄድ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ለአብነት የኢትዮ ቴሌኮምን አክስዮን መቀሌ ላይ ያለ ሰው ከገዛ በኋላ ጅማ ላለ ሰው መልሶ ልሽጥ ቢል በአካል ሁለቱም ሻጭና ገዢ የኢትዮ ቴሌኮም ዋናው መሠሪያ ቤት ወዳለበት ሊመጡ የግድ ነው። ይህ ጊዜ የሚወስድ፣ ወጪ የሚጠይቅና የሚያሰራ ባለመሆኑ መገበያያ መድረክ አስፈልጓል።
በዚህና መሰል ምክንያቶች አሁን ላይ የአክሲዮን መገበያያ መድረክ ተፈጥሯል። ከዚህ ቀደም በየባንኮቹ የነበረው የአክሲዮን ግብይት ብዙ የሚያስወጣና ጊዜ የሚፈልግ እንዲሁም በቂ የሆነ ገበያ ያልነበረው ነው። በዚህ ምክንያት ተሳታፊዎቹ መሀል አዲስ አበባ አካባቢ ያሉ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ምክንያቱም የግብይት ሥርዓቱ ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ አዲስ አበባ ላለ ሰው ብቻ ይቀላል። ይሁንና የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ግቡ ይህ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለበት ቦታ ሆኖ ባለው አቅም መቆጠብ እንዲችል ነው። ለአብነትም የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን እስከ አስር ሺ ብር ያለው ሰው እንዲቆጥብበት ዕድሉን አመቻችቷል።
ይህም አክስዮን ግዢ መቆጠቢያ መንገድ ነው። ስለዚህ አክስዮን የሚገዛ አንድ ሰው ወደፊት ልጆቹን ሊያስተምርበትና ሊሸጠው ከፈለገ፣ በውርስ ሊያስተላልፈው ከፈለገና ለሌሎችም ጉዳዮቹ ከፈለገው ገንዘቡን መቆጠቢያ መንገድ መሆን አለበት። በመሆኑም አንድ ኢትዮ ቴሌኮም ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትና የግል ተቋማት መምጣት አለባቸው። እነዚህ ተቋማት ሲመጡ አትራፊና አዋጭነታቸውን በማየት አክስዮኖችን ገዝቶ መቆጠብ ይቻላል። በዋነኛነት የትርፍ ድርሻ የሚከፈልበት ሲሆን፤ ጥሬ ገንዘብ በቁጠባ ደብተር ብቻ ከማስቀመጥና በኪስ ከመያዝ ባለፈ አክስዮኖችን መግዛት የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ጭምር ይረዳል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በዋናነት ይህን ሥራ ለማቀላጠፍ የተቋቋመ ነው ያሉት ዶክተር ጥላሁን፤ ሰዎች መገበያየት በፈለጉ ጊዜ የትም ቦታ ሆነው በአገናኝ አባል በኩል ወይም በሞባይል አፕሊኬሽን ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን መግዛትና መሸጥ ይችላሉ። ለዚህም የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አብዛኛውን ሥራ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቅርቡም ወደ ተግባር ይገባል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በዋናው ሲስተም ላይ ሙከራ እያደረገ ሲሆን፤ በቅርቡ በይፋ እንደሚጀምር ጠቅሰው፣ አሁን የኢትዮ ቴሌኮም አክስዮንን እየገዙ ያሉ ሰዎች ወደፊት መሸጥ መለወጥ ሲፈልጉ መሸጫ መለወጫ በሆነው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መሸጥ መለወጥ እንደሚችሉም አስረድተዋል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥርዓት መዘርጋቱ አበርክቶው ዘርፈ ብዙ ነው የሚሉት ዶክተር ጥላሁን፤ በዋናነት ሻጭና ገዢን በማገናኘት ዋጋ ማውጣት አንዱ ሥራ ነው ይላሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ዋጋ ማወቅ ደግሞ ባለሀብቱ ዛሬ የሚያወጣው ብር ዋጋ እንዳለውና መሸጫና መለወጫ ቦታ እንዳላቸው ሲያውቁ ቀድመው የመሳተፍ ፍላጎት ይኖራቸዋል። ሌላው የመረጃ አቅርቦት ሲሆን ለአብነትም የገዙት ነገር የተሻለ ትንተና እና የገበያው ዋጋ ስንት ነው የሚለውን እንዲያውቁ ያደርጋል። ይህም ወጪ ቆጣቢ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ይኖረዋል።
የቁጠባ መንገዶችን በማሻሻል በትንሹ በጥሬ ገንዘብ/ በካሽ/ መቆጠብን ጨምሮ ቦንድና አክስዮን መግዛትና መሸጥ የሚችሉበት የገበያ መድረክ አስፈላጊ ነው ያሉት ዶክተር ጥላሁን፤ ለዚህም የሰነዶች ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አንዱ የመገበያያ መድረክ ነው ብለዋል። በዚህ የመገበያያ መድረክ አማካኝነት አሁን የተጀመረውን የኢትዮ ቴሌኮም አክስዮንን ጨምሮ ወደፊት የሚመጡ የተለያዩ የአክስዮን እና የሰነድ ግብይቶች የሚፈጸምበት ይሆናል። የመገበያየ መድረኩ በመፈጠሩ ምክንያትም በርካታ ሰዎች በአክስዮን ሥርዓት ላይ እንዲሳተፉ እንደሚጋብዝም አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የመገበያያ መድረኩ ደንበኞችን ለማፍራት ሳቢ የሆኑ መግለጫዎችን በማውጣት የደንበኞቹን ቁጥር ማሳደግ ይጠበቅበታል። እስከ ዛሬ በነበረው አካሄድ የደንበኞች ሳቢ መግለጫ አይወጣም። የማንበብና የመተንተን ባህሪም አልነበረም። አሁን ግን ስለ እያንዳንዱ አክስዮን ምንነት ሙሉ መረጃ የሚሰጥ አካል አለ። ለአብነትም ኢትዮ ቴሌኮም ምንድነው፤ ማነው፤ ራዕዩ ምንድነው፤ ለምን እገዛለሁ የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘትና ሰለ ኢትዮ ቴሌኮም አክስዮን ሰዎች መረዳት አለባቸው።
ለዚህም አሁን ያለው ጅማሮ ጥሩ ነው። ወደፊት ግን ሰዎች ሰፋ ያሉ መግለጫዎችን የማንበብ አቅም የሌላቸው በመሆኑ በመሀል ያሉ ተሳታፊዎች በተለይም የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ያግዛሉ። እነዚህ አማካሪዎች ስለአክሲዮኑ የወጡ መግለጫዎችን አንብበውና በሚገባ ተረድተው ከደንበኛው ፍላጎት ጋር ሊስማማ የሚችለውን የኢንቨስትመንት አይነት በአማራጭ በማቅረብ የሚያማክሩ ይሆናል።
የመንግሥት ቦንድ ምንድነው፤ አክሲዮን ምንድነው፤ የግምጃ ቤት ሰነድ ምንድን ነው፤ የሚሉ ጉዳዮችን ማብራራትና ማስረዳት ያስፈልጋል። ለዚህም በመሀል ያሉ አገናኝ አባላት ያስፈልጋሉ። በተለይም የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ኬንያና ሌሎች ምስራቅ አፍሪካ ላይ ያሉ አገናኝ አባል ሆነው የሚያገለግሉ ኢንቨስትመንት ባንክ ሆነው የሚያገለግሉ ተቋማት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመጡ ያስፈልጋል። የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ኬንያ ናይሮቢ ከሚገኘው NSE (Nairobi securities exchange) የካፒታል ገበያ ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙም ለዚህ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ወደ ካፒታል ገበያ እያደረገች ያለችውን ጉዞ አስመልከተው ወደ ሀገራቸው በመመልስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እድል ያስተዋውቃሉ። ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ፍላጎት ያሳያሉ። ይህ ካፒታል ገበያውን ለማስፋትና ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል። የካፒታል ገበያ ተሳታፊዎች ማሟላት ያለባቸው መስፈርት ስለመኖሩ ያነሱት ዶክተር ጥላሁን፤ በካፒታል ገበያ ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶች እንደመኖራቸው ለአገልግሎቶቹም የተለያዩ መመሪያዎች እንዳሉ አመላክተዋል።
ለእዚህም መነሻ ካፒታል፣ የሰው ኃይል ማሟላት፣ የውስጥ ደንቦችና ሥርዓት ማሟላት፣ ስልጠና፣ ቢዝነሱን መረዳትና ፈቃድ ማግኘት የሚሉት በአብነት ይጠቀሳሉ። እነዚህን ዋና ዋና ጉዳዮች ማሟላት የቻሉ ተሳታፊዎች ከካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም አክስዮን መግዛት መለወጥ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር በመቀራረብ አዋጭ የሆነውን መንገድ እንዲከተሉ የማማከር ሥራ የሚሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
የአይ ካፒታል ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ገመቹ ዋቅቶላ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ አይ ካፒታል ያስፈልጋታል የሚል አቋም እንደነበረው አስታውሰው፣ አሁን ግን ካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ሊጀመር ጫፍ ደርሷል ብለዋል። ይህ ለአይ ካፒታል ትልቅ የህሊና እርካታ መሆኑንም ገልጸዋል።
ካፒታል ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ በቶሎ እንዲጀመር አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል ሲሉ አብራርተው፣ በተለይም የዘርፉን የምስራቅ አፍሪካ ፋይናንስ ጉባኤም በየዓመቱ ሲያዘጋጅ መቆየቱን አስታውሰዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ይህን ሲያደርግም ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ እንዴት አድርጎ ሌሎች ሀገራት የደረሱበት ደረጃ መድረስ ይቻላል የሚለውን ለመመለስ ሰርቷል። በተለይም ለፖሊሲ ጥናት ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ለሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት በሙሉ ሲሰጥ ቆይቷል።
ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውጭም የሚሰራ በመሆኑ በአቅም ግንባታና በማማከር አገልግሎትም ይሰራል። በቅርቡም የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ አዲስ ልምምድ እንደመሆኑ ለኢትዮጵያ ተቋማት ስለ ካፒታል ገበያ ምንነትና እንዴት እንደሚሰራ ባንኮችና ሌሎች በካፒታል ገበያ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ተቋማት ምን ማወቅና መረዳት አለባቸው የሚለውን በተግባር መረዳት እንዲችሉና እንዲያግዛቸው የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ሰርቷል፤ አሁንም እየሰራ ይገኛል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ለሚገኙ ባንኮች በአንድም በሌላ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማካፈል በተግባር እንዴት እንደሚሰራ ልምድ መቅሰም እንዲችሉ ተደርጓል። ምክንያቱም አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት የሌሎች ሀገራትን ልምድ በመቅሰም የሚሰራ በመሆኑ ኬኒያ በመሄድ በተግባር መረዳት እንዲቻል ተደርጓል።
ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያና ከ NSE (Nairobi securities exchange) ጋር የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነትም የካፒታል ገበያ ተግባራዊ ሆኖ ግብይት ሲጀምር ምን ማድረግ እንደሚገባና ተጨማሪ ሥራዎችን ለመለየት የሚያግዝ ነው ሲሉ ዶክተር ገመቹ አስታውቀዋል። ወደ ካፒታል ገበያ ለመግባት እስካሁንም በነበረው የተግባር ልምምድና ዝግጅት ብዙ ክፍተቶችን መሙላት ተችሏል ብለዋል። በተለይም ካፒታል ገበያ ምንድነው? እንዴት ነው የሚሰራው? እነማናቸው መሳተፍ የሚችሉት? እንዴት ነው የሚሳተፉት? ተቋማት ብቻ ናቸው ወይስ ግለሰቦች መሳተፍ የሚችሉት? የሚሉትን በመረዳት በኩል ትልቅ ክፍተት እንደነበር አስታውሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ካፒታል ገበያ ምህዳር ነው። ምህዳር ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች እኩል መምጣት አለባቸው። ምክንያቱም ሕጉ ብቻ ስለመጣና አንድ ሁለት ተቋማት ዝግጁ ስለሆኑ የካፒታል ገበያ ሥርዓትን መገንባት አይቻልም። ይህ ከሆነ ደግሞ በካፒታል ገበያ ውስጥ ሚና ያላቸው አካላት በሙሉ በተመሳሳይ ፍጥነት መሄድ እንዲችሉ ምን ማድረግ ይቻላል የሚለውን ለመረዳት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የጋራ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም ገንቢና አስተማሪ የሆኑና ጠንካራ የሆነ የካፒታል ገበያ ምህዳር ለመገንባት የሚያስችሉ መረጃዎችን ማግኘት ተችሏል።
ሌላው በካፒታል ገበያ ምህዳር ገበያ ላይ የሚሳተፉ ለምሳሌ አክስዮን የሚሸጡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ሁሉ ባንኮችና ሌሎችም መምጣት ይኖርባቸዋል። እነሱ ሲመጡ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች እንዴት ኢንቨስት እንደሚያደርጉ፣ ለምን ኢንቨስት እንደሚያደርጉና በማን በኩል ኢንቨስት እንደሚያደርጉ ዕውቀቱና ዝግጁነት ሊኖራቸው ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ገበያው በመኖሩ ብቻ ሼሮቹ ወይም አክስዮኖቹ በመኖራቸው ብቻ አይሻሻጥም። እንዲሻሻጥ ገዢውና ሻጩ ቀጥታ አይገናኙም። ለዚህ የተዘረጋ ሥርዓት አለው። በዚህ ሥርዓት በመሀል ገብተው የሚያመቻቹ የተለያዩ አማካሪዎች ዕውቀት ኖሯቸው ወደ ሥርዓቱ ሊገቡ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ባለስልጣን ፈቃድ ያገኛሉ ተብለው የተለዩት አማካሪዎች በመሀል ገብተው ሥራ መሥራት አለባቸው ያሉት ዶክተር ገመቹ፤ እነሱ በፍጥነት መዘጋጀት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ተቋማትም ይሁኑ ግለሰቦች ማንኛውም ባለሀብት እንዲሁ ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። እያንዳንዱ ግለሰብ እንዴት ይሳተፍ? በማን በኩል ይሳተፍ? የሚሉትን ግንዛቤዎች በመፍጠር በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት የግድ መሆኑን አመላክተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም