ሥልጡኖች በምን በለጡን?

ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብና የአመለካከት መሰልጠንን፣ በአጠቃላይ ዘመኑ የደረሰበትን ንቃት በተመለከተ፤ በዚህ በትዝብት ዓምዳችን ብዙ ብለናል። መሰልጠንን ስናነሳ ማንፀሪያ የምናደርገው አሜሪካና አውሮፓውያንን መሆኑ ግልጽ ነው። ሥልጣኔ ሲባል፤ የግድ በእነርሱ ‹‹ስታንዳርድ›› ብቻ መሆን አለበት ማለት ግን አይደለም።

ሀገራት የራሳቸውን ወግና ባህል ይዘው፣ በራሳቸው ማንነት ይሰለጥናሉ፤ ለዚህ ምሳሌ የሚደረጉት የሩቅ ምሥራቆቹ ሀገራት እነ ጃፓን እና ቻይና ናቸው። ሰፊ እና ዝርዝር ጉዳዩን እንተወውና፤ መሰልጠን ማለት በአጭሩ፤ ለሰው ልጅ ምቹ የሆነ ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው። ከቴክኖሎጂ አንፃር ካየነው፤ ጊዜንና ድካምን የሚቀንስ መሳሪያ መጠቀም፤ ከአስተሳሰብና ድርጊት አንፃር ካየነው፤ ለአካላዊና አዕምሯዊ ጤና ምቹ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ማለት ነው። ከዚህ አንፃር የሰለጠኑ የሚባሉ ሀገራት በምንድነው የሚበልጡን? የሚለውን እስኪ ልብ እንበለው።

ይህን ሃሳብ በድጋሚ እንዳነሳው ያደረገኝ ባለፈው እሁድ ምሽት፤ ኤን ቢ ሲ ቴሌቭዥን ላይ ‹‹የሳምንቱ ጨዋታ ከሰመረ ባሪያው›› የተሰኘውን ፕሮግራም አይቼ ነው። የፕሮግራሙ አዘጋጅ ለጉብኝት አሜሪካ በቆየባቸው ጊዜያት ያስተዋላቸውን የሥልጣኔ ልዩነቶች የተናገረበት ነው። አዘጋጁ ራሱ እንደተናገረው፤ ሊቆጨን እንደሚገባ እንድንወያይበት እንጂ ነገርየው አዲስ ሆኖ አይደለም። ማንም የሚገምተው እና በተደጋጋሚ ሲባልም የምንሰማው ነው፤ ዳሩ ግን ልንለወጥበት አልቻልንም።

ለምሳሌ፤ ከወራት በፊት ይመስለኛል ቅጥ ያጣ የተሽከርካሪ ክላክስን በተመለከተ በዚሁ ዓምድ ትዝብታችንን አጋርተን ነበር። አብዛኛው አሽከርካሪ ክላክስ የሚያደርገው አስፈላጊ ባልሆነ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ህገ ወጥ በሆነ ጉዳይ ጭምር ነው። ለምሳሌ፤ የትራፊክ መብራት በያዘው ተሽከርካሪ ላይ ያለምንም ማቋረጥ የሚያንባርቅ አለ። የሰለጠነ ሀገር የሄዱ ሰዎች ሁሉ ሲያወሩ እንደምንሰማው፤ ያለአግባብ ክላክስ ማድረግ አደገኛ ቅጣት ያለው ህገ ወጥ ድርጊት ነው። በአሜሪካ ለአንድ ወር ያህል እንደቆየ የተናገረው ሰመረ ባሪያው ‹‹የመኪና ክላክስ የሰማሁት ምናልባት ምናልባት ሁለት ቢሆን ነው!›› ሲል ነበር።

ዋናው ጥያቄ፤ ‹‹ሥልጡን ዜጎች በምን በለጡን?›› የሚለው ነው።

አንድ የቴሌቭዥን ወይም ሬዲዮ ጋዜጠኛ መንገድ ላይ ሰዎችን እያስቆመ ‹‹የሰለጠኑ ሀገራት በምን በለጡን?›› የሚለውን ጥያቄ ቢጠይቅ፤ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሰው ‹‹የተዘረጋ ሥርዓት ስላላቸው›› ማለቱ አይቀርም። ‹‹የሰለጠኑ ስለሆኑ፣ ምቹ መሰረተ ልማት ስላላቸው፣ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ስለሆኑ…›› የሚሉ ምላሾች ሊሰጡ ይችላሉ። አሁንም ግን ዋናው ጥያቄ፤ ‹‹ይሄን የተባለውን እንዴት ፈጠሩት?›› የሚለው ነው።

ዋናው መሰልጠን ጭንቅላት ላይ ነው። ከሞላ ጎደል አሜሪካና አውሮፓውያን የሚጠቀሙትን ቴክኖሎጂ እንጠቀማለን፤ ችግሩ ግን የአስተሳሰብ መሰልጠን ከሌለ እናበላሸዋለን። ቀላል ምሳሌ እንውሰድ። ብዙ ሰው ውድ የሚባል ስልክ ከውጭ ይላክለታል። ዳሩ ግን ስልኩ የሚሰጠውን አገልግሎት 10 በመቶ የሚሆነውን እንኳን ላይጠቀመው ይችላል። የማህበራዊ ገጽ መተግበሪያዎችን አውርዶ የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጭ ሊሆን ይችላል። ለሀገሩ መሰልጠን ሳይሆን ለሀገሩ ወደ ኋላ መጎተት ምክንያት ሆነ ማለት ነው። ስለዚህ አስተሳሰብ ካልሰለጠነ፤ የሰለጠኑት የሰሩት ቴክኖሎጂ ምናልባትም አደጋ የሚያመጣ ይሆናል ማለት ነው።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በአዲስ አበባ እጅግ ውብ የሆኑ መንገዶች እየተሰሩ ናቸው። አውሮፓና አሜሪካ ሄደው የመጡ ሰዎች ሲያወሩ እየሰማን፣ ወይም በፊልሞቻቸው እያየን ስንቀና የነበረውን በዓይናችችን እያየን ነው። በሁሉም አካባቢ ባይሆንም ቢያንስ ለናሙና ያህል የሰለጠኑት ሀገራት ውስጥ ያለውን መሰረተ ልማት ከሞላ ጎደል አገኘን ማለት ነው። ዳሩ ግን አንዳንድ የምናያቸው ነገሮች አናዳጅ ናቸው። ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ በሚወስደው በዚያ በሚያምር የእግረኛ መንገድ ላይ ብዙ ቀን የተጣለ ቆሻሻ አይቼ አውቃለሁ። አጠገቡ የቆሻሻ መጣያ ሳጥን አለ። ሶፍትም ሆነ ሌላ ነገር የሚጥለው ሰውዬ፤ ያ መንገድ እንደዚያ ማማሩ ምን ስሜት ፈጥሮበት ይሆን? ቆሻሻ መጣል ነውር መሆኑ ትዝ ባይለው እንኳን፤ እዚያ የሚያምር ሳር ላይ መጣል እንዴት አያሳሳውም?

የተቋማት እና ንግድ ቤቶችን መጸዳጃ ቤቶች ልብ በሉ። ሁሉም ለማለት ባያስደፍርም፤ መጀመሪያ ሲሰሩ ከሞላ ጎደል የሰለጠኑ ናቸው በሚባሉ ሀገራት ያለውን መስለው የሚሰሩ ናቸው። ሙያው የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተው የሚሰሩ ናቸው። ለምሳሌ፤ መጸዳጃ ቤት ማሟላት ያለበትን ነገር አሟልተው ይሰራሉ። ችግሩ የሚመጣው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ነው።

የመጀመሪያውና ዋናው ችግር፤ ተጠቃሚው በሰለጠነ መንገድ አይጠቀምም። ሁለተኛው ችግር ደግሞ፤ አንዴ የተበላሸ ነገር ቶሎ አይጠገንም።

‹‹ውሃ ይድፉ!›› የሚል ማሳሰቢያ የሚጻፍልን ዜጎች ነን። እጁን ታጥቦ ቧንቧ ሳይዘጋ የሚሄድ ብዙ ሰው አለ። ወጥ በነካ እጁ የቧንቧ መክፈቻውን ወጥ በወጥ አድርጎት የሚሄድ ብዙ ነው። መቼም በሁለቱም እጁ አይበላም፤ ታዲያ ምን አለ ወጥ ባልነካው እጁ ቢከፍተው? ከታጠበ በኋላ ቧንቧውን ሲዘጋው ወጥ አይነካውም ወይ? ለነገሩ ምን ዕዳ አለበት ሳይዘጋው ይሄዳል!

ከሰለጠኑ ሀገራት ጋር ራሳችንን ስናነፃፅር፤ ሌላው ትልቁ ልዩነት የህግና መርህ ተገዥነት ነው። ብዙ ነገራቸው ነፃ እና ልቅ ይመስለናል፤ እንደ ሰለጠነ ሀገር ግን የህግና መርህ ተገዥ የለም። በእኛ ሀገር ‹‹ነውር›› የሚባለውን ነገር እንኳን ሲያደርጉ ህግ አውጥተውለት ነው። በህግ ከተፈቀደ ብቻ ነው። ለእኛ ጭቆና የሚመስለን ነገር፤ ለእነርሱ ግን ህግ ነው። ለምሳሌ፤ ባቡር ውስጥ ስልክ ማውራት ከተከለከለ፣ በቃ ተከለከለ ነው! ህግ ነው፤ ህግ ነው!

እንኳን እንዲህ አይነት ትንንሽ የሚመስሉ ነገሮችን ይቅርና፤ ዋናዎቹን ጉዳዮች ሳይቀር ከህግና መርህ ይልቅ፣ በግለሰቦች ስሜት የምንጓዘው ይበልጣል። ጉዳይ ስናስፈጽም፤ ህግና መመሪያው ምን ይላል ከማለት ይልቅ ጉዳዩን የሚፈጽምልን ሰውዬ ማንነትና ምንነት ላይ እንንጠለጠላለን። አንድ ነገር ይፈጸምልናል ወይም አይፈጸምልንም ብለን ተስፋ የምናደርገው ከህግና መርህ ይልቅ በሰውየው መልካምነት ላይ ነው።

ለምሳሌ፤ ብዙ ጊዜ ለአንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ኃላፊ ሲሾም፤ የተቋሙ ሰራተኛም ሆነ አገልግሎቱን የሚያገኘው ደንበኛ፤ የተቋሙን ህግና ደንቦች ከማንበብና ከመጠየቅ ይልቅ ‹‹ሰውየው ምን አይነት ነው?›› የሚለው ላይ ያተኩራል። ‹‹ደህና ሰው ነው አሉ፤ ኧረ ክፉ ነው አሉ!›› የሚሉ ግለሰባዊ ባህሪያት ጉዳይ ይሆናሉ ማለት ነው። አገልግሎቱን የምናገኘውም ሆነ የምናጣው፤ ከህግና መርህ ይልቅ በግለሰባዊ ክፋትና ደግነት ይሆናል ማለት ነው። ‹‹የዓይኑ ቀለም አላማረኝም›› በሚል ብቻ አንድን ሰው ልንበድል እንችላለን። ‹‹እንዲሁ ሳየው ደስ አለኝ›› በሚል ብቻ ያለአግባብ አንድን ሰው ልንጠቅም እንችላለን።

ብዙዎቻችን ቅንነት ይጎለናል። በነገራችን ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቅንነትን በተመለከተ ብዙ ሥልጠናዎች ሲሰጡ አስተውያለሁ፤ ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው። ዳሩ ግን በተግባር መታየት አለበት። አንድ ተቋም ሠራተኞቹን ስለቅንነት ብዙ ሊያስተምርና ሊያሰለጥን ይችላል። ሥልጠናውን በወሰዱ በነጋታው ግን አንድን ደንበኛ ‹‹ቆሌው አላማረኝም›› በሚል ብቻ ሊያመናጭቁት ይችላሉ፤ ቅንነት ከልብ ሲሆን ነው።

ቅንነትና ትህትና ሲኖር ሥልጡንነትን ያመጣል። ለምሳሌ፤ አንድ ስነ ምግባር የጎደለው የመሰለን ሰው ሊመጣ ይችላል። ገና ስናየው ደማችን ከሚፈላ ይልቅ፤ ትሁት ሆኖ እሱንም ትህትና ማስተማር ነው። አንድን ሰው በስሜት ከተናገርነው እሱም ኢትዮጵያዊ ነውና ስሜታዊ ይሆናል። ይህን ሰው ትህትና ብናስተምረው ግን አንድ ሰው ሰራን ማለት ነው።

በአጠቃላይ፤ ሥልጡኖች የሚበልጡን በቁስ አካል ሳይሆን በጭንቅላት ነው። ሥልጡንነትና ሥልጣኔ የሚመጣው በትህትና፣ በቅንነት፣ በታታሪነት እና በአርቆ አስተዋይነት ነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You