ሁለቱ አለምን በኃያልነት ለመምራት እየተገዳደሩ ያሉ አገራት የአሜሪካና ቻይና እሰጥ-አገባ አሁንም በሌላ ጉዳይ ቀጥሏል፡፡ አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ስምምነት እያጸደቀች መሆኑ በመሰማቱ የሁለቱ አገራት የእርስ በእርስ ውግዘትና ተቃርኖ ተባብሷል፡ ፡ ስምምነቱን አጥብቃ የኮነነችው ቻይና አሜሪካንን አስጠንቅቃለች፡፡ በሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የጦር መሳሪያ ከአሜሪካ ልትገዛ ስምምነቱን የፈረመችው ታይዋን ደግሞ እራሴን የመከላከል አቅሜን የሚያጠናክርልኝ ነው ማለትዋ ተገልጿል፡፡
“እኔ የአለም እራስ ነኝ! የምድሪቱን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በበላይነት የማሾር መብቱ እና ጉልበቱ የታደልኩት እኔ ብቻ ነኝ፡፡” እንደምትል በተለያዩ ድርጊቶች እንደምታሳይ ለምትታማዋ አሜሪካ፤ ቻይና ‹‹አንቺ ማን ነሽና በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ የምትገቢው? የታይዋን ጉዳይ ማለት ከራሴ ነጥዬ የማላየው የሉዓላዊነቴ ጉዳይ ነው፡፡›› በማለት ለአሜሪካ ድርጊት በቁጣ ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ከወደ አሜሪካ የተሰማው የጦር መሳሪያ ስምምነቱ ዜና ቻይናን አብግኗል፡፡ ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ልትሸጥላት ያቀደችው የሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት በፍጥነት ሊቋረጥ ይገባል የሚል ማሳሰቢያ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይዋ በኩል ሰጥታለች፡፡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጌንግ ሹአንግ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ አሜሪካ ለታይዋን ያፀደቀችውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚዳፈር መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ መግለጫ የአሜሪካ ያልተገባ ስምምነትና ተግባር ሀገራቸው በለዘብታ አትመለከተውም፡፡ ከአንድ የግል ግዛቴ ጋር ያለኔ ፍቃድ የተፈፀመ ህገ ወጥ ስምምነት ነውም ብለዋል:: ቆፍጣናውና ቃል አቀባዩ ጌንግ ሹአንግ ስምምነቱን ፈፅሞ ሊተገበር የማይገባ በኛ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣን ሙከራ እንዲያውም በድፍረት የተሞከረ ፀብ አጫሪነት ነው ብለውታል፡፡
በታይዋን እፈልጋለሁ ጥያቄና አሜሪካ “ኧረ ምን ገዶኝ የምፈልገውና አቅምሽ የቻለውን ላስታጥቅሽ ዝግጁ ነኝ! ብቻ የመሳሪያዎቹን ዋጋ ወዲህ በይ” ማለትዋን ተከትሎ ቻይና አሜሪካንን “ከዘመናዊ የጦር መሳሪያ ስምምነቱ እጅሽን ብትሰበስቢ ላንቺ ይበጅሻል ካልሆነ ግን ምላሼ የበረታ ነው” አስብሏታል፡፡ ቻይና በዚህ ጉዳይ ላይ ያላት አቋም ጠንካራ መሆኑን የሚያመላክተው መግለጫዋ እንደሚያትተው አሜሪካ የጦር መሳሪያ ውሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትሰርዝ የሚያስጠነቅቅ ነው።
አሜሪካንን የኮነነውና ያስጠነቀቀው የቃል አቀባዩ መግለጫ ድርጊቱ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ነው፤ በተጨማሪም ጉዳዩ አለማቀፋዊ ህግን የጣሰና የውጭ ግንኙነት ደንብም የተላለፈ መሆኑን ያትታል። ይህ የቻይና አቋም ደግሞ ታይዋን እንደ ሌላ ግዛት ሳይሆን የራስዋ ሉዓላዊ ግዛት አድርጋ መቁጠርን በፅኑ የሚያመላክትና የታይዋን ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው ማለትዋን ያሳብቃል፡፡
‹‹እኔ እራስ ገዝ ነኝ በኔ ጉዳይ ማንም ሊያገባው አይችልም፡፡ ለዚያም ነው እራሴን ለመከላከል የሚያስችለኝ የጦር መሳሪያ የምሸምተው ለዚህ ደግሞ የማንንም ፍቃድ አልሻም›› የምትለውና ራስ ገዝ የሆነውችው ታይዋን በቻይና ተቀባይነት አጥታለች:: ቻይና የራሴ ግዛት ናት ብላ የምታምን ሲሆን፥ ይህን አላማዋን ለማሳካትም የተለያዩ ዘዴዎችን በመተግበር ወደ ግዛቷ የማጠቃለል ፍላጎት አላት።
ሁሌም ስለኔ ወሳኝዋ እኔው ብቻ ነኝ የምትለዋ ታይዋን ከአሜሪካ ልትገዛው ያሰበችው የጦር መሳሪያ ስምምነቱ መፅደቅ እጅግ አስደስቷታል፡፡ ስምምነቱን ተከትሎ የታይዋን ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ለባለውለታቸው የአሜሪካ መንግስት፤ ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረባቸው ተገልጿል። የታይዋን ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤቱ ቃል አቀባይ ቱን ሃን፤ የጦር መሳሪያ ግዥው አገሪቱ እያከናወነች ላለው የመከላከያ አቅም ግንባታ ስራ የላቀ ሚና እንዳለውና ከፍተኛ መሻሻልን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የቻይናና የታይዋን ላንቺ እኔ ወሳኝ ነኝ፤ አይ ስለራሴ የምወስነው እኔ ብቻ ነኝ፡፡ የማለትና እርስ በርስ የመነቋቆሩ ነይ አልመጣም ውዝግቡ ከጅምሩ እስካሁን የዘለቀበት መነሻ ምክንያቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1949 ላይ ይጀምራል፡፡ የቻይና ግዛቶች የኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለምን ሲከተሉ፤ የተቀሩት ጥቂት የዴሞክራሲ ሪዮት አለምን በማቀንቀን ላይ ያሉት ግዛቶች ወደ ታይዋን በመጠቃለል ደሴቲቱን እንደ አገር ለመመስረት ቻሉ፡፡
ሆኖም የተለያየ የፖለቲካ ፅንፍ የሚከተሉት ቻይናና ታይዋን በአካባቢያዊ ጉዳያቸው በየጊዜው እየተካረረ የመጣ ንትርክ ውስጥ መግባት ጀመሩ፡፡ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢ ፒንግ ደጋግመው ታይዋን የቻይና ግዛት መሆኗን በይፋ ማወጃቸውና ይህንንም ማንም ሊክደው የማይችለው ሃቅ መሆኑ መናገራቸው ለታይዋን ራስ ገዝነት እውቅና ማሳጠት ዋንኛ ማመላከቻ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ በተደጋጋሚ መግለጫና ንግግራቸው አገራቸው ታይዋን ወደራሷ ግዛት ለመጠቅለል ማንኛውንም የሃይል እርምጃ መውሰድ እንደምትችልም ለእዚህም ዝግጁ እደሆነች መግለፃቸው ይታወሳል:: ቻይና ታይዋንን የኔ አደርግሻለሁ ማለትን በተሻገረ ፍላጎትና ተግባርዋ ያንቺን አጠቃላይ ሁኔታ በእኔ ትዕዛዝና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ማለትዋን ታይዋን አጥብቃ ትቃወመዋለች፡፡
ታይዋን ከቻይና የሚደርስባትን ማስፈራሪያና ዛቻ ወደ ተግባር ከተለወጠ ለዚህ መዘጋጀት ይገባኛል በማለት፤ ለመመከትም ያስችላት ዘንድ ለወታደሮቿ ከወትሮው የተለየ ልምምድ በመስጠት የሚከፈትባቸውን ጥቃት ለመመከት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ዛሬ ላይ ከአሜሪካ ልትገዛ የተስማማችው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ስምምነት ለወታደራዊ አቅምዋ መጠንከር አስፈላጊ መሆኑን አምናበት የወጠነችው ግብ መሆኑም እየተገለፀ ነው፡፡
ዛሬ ድረስ የአሜሪካና የቻይና ፍጥጫን የሚያፋፍመው ዋንኛ ጉዳይ ይሄው የታይዋንና የአሜሪካ ጥብቅ ቁርኝት ብሎም የጦር መሳሪያ ድጋፍና የሽያጭ ስምምነት ጉዳይ የሶስቱ አገራት ዋንኛ ትኩረት ሆኗል፡፡ ታላላቅ የአለም መገናኛ ብዙሀን የወቅቱን የሁለቱ አገራት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፉክክር ጋር እያገናኙ የታይዋን ራስ ገዝ አስተዳደርነት እና የቻይና ይህንን አልቀበልም ባይነት በልዩ ሁኔታ ተንትነውታል፡፡
አሜሪካን እራሷን እያገነነች ባላጋራዋ ቻይናን ለማዳከም ከምታደርገው የውስጥ ፖለቲካዊ ስትራጂዋ ባሻገር፤ ታይዋን እራሴን የመከላከል አቅሜን አጎለብትበታለሁ የምትልበትን መሳሪያ በማቅረብ ረብጣ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ተነስታለች፡፡ ቻይናም በአንፃሩ ሉዓላዊነቴን ተዳፈሩብኝ ባለቻቸው በዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ፤ የእራስ ምታቷን ደወል ደጋግማ የምታስጀምረው አሜሪካ እንድታርፍ ቻይና ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ከቃል አቀባይዋ ጌንግ ሹአንግ በኩል ማስተላለፍዋ ተሰምቷል፡፡
በተለይም የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ በዘገበው የሁለቱ አገራት የጦር መሳሪያ ስምምነትና የቻይና ማስጠንቀቂያ አዘል ኩርፊያ የሁለቱ ሃያላን አገራት ፍጥጫ ይበልጥ አጠንክሮታል፡፡ ቻይና አስቀድማ አሜሪካ ለታይዋን ልትሸጥ ያሰበችው መሳሪያ በእቅድ ላይ እንዳለ ከስምምነቱ በፊት ደርሳበት ይሄ ነገር ልክ አይደለም ከወዲሁ ይገታ ብትልም አሜሪካ የቻይናን “እረፊ” ማለትን ጆሮ ዳባ ልበስ ብላ እቅድዋን ወደ ስምምነት አድርሳዋለች፡፡
አንዱ ከአንድ ወገን ጋር በሚያደርገው ስምምነት አንዱ መገላመጡ ደግሞም አንዱ ከሌላው ጋር በሚያደርገው መግባባት ሌላው ማኩረፉ ውሎ አድሮ ከሮ በበዛ ጉዳይ መፋጠጡ የአገራቱ ተለምዷዊ ሁኔታ እየሆነ ይገኛል፡፡ አለም በበላይነት የመቆጣጠሩ ሽኩቻ ኢኮኖሚን ከላይ ሆኖ የመዘወሩ ፍላጎትና ትግል በሁለቱ አገራት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ለታይዋን አልሸነፍ ባይነት ትልቅ ደጀን መሆንዋ የሚነገርላት አሜሪካ የአካባቢውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ሁኔታ ለመዘወር ያመቻት ዘንድ በአጋርነት እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡ ታይዋን ላይ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውም ጥቃት አሜሪካ ከጎንዋ እንደምትቆምና ድጋፍ እደምታደርግላት በተደጋጋሚ በጦር ሃይልዋ መሪዎች የምትገልፀውም ለዚህ ነው፡፡
ታይዋን የአሜሪካ አለሁልሽ ባይነት የልብ ልብ ሰጥቷት የጦር ሰራዊትዋን ማጠናከርና የጦር መሳሪያ ግዢ ማድረግ ዋንኛ ግቧ አድርጋለች፡፡ ይህ ሁኔታ በቅርበት የምትከታተለዋ ቻይና ደግሞ የታይዋን እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ እጅጉን አስቆጥቷታል፡፡ አለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች በታዋቂ መገናኛ ብዙኋን እየቀረቡ ታይዋን በተመለከተ የአሜሪካና የቻይና ፍጥጫ ላይ የበኩላቸው አስተያየት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
በአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባላቸው አሜሪካና ቻይና መካከል የሚደረገው የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት መቆጣጠር ፍላጎት፤ ፍትጊያና ፉክክር ታይዋን በምታደርጋቸው ጉልህ እንቅስቃሴዎች ላይ ደምቆ ይታያል፡፡ ምክንያቱም ታይዋን በራሴ የቆምኩ ነኝ ብትልም፤ ታይዋን ለቻይና ግዛትዋ ለአሜሪካ ደግሞ ደጀንዋ ናትና፡፡ የታይዋንና የአሜሪካ በጦር ሃይል እርዳታና ሽያጭ ቀለበት ማጥለቅ ይህን ተከትሎ የቻይና ግልምጫ ቀጣዩን የጉዳዩ አቅጣጫ ከወዴት ያደርሰው ይሆን? ቀን ይፈታዋል፡፡ አበቃሁ!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
ተገኝ ብሩ