ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሠራች ነው። ለዚህም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርጻ እየተገበረች ትገኛለች። በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ ሲሆን፤ የኦንላይን የገንዘብ ዝውውሩም እያደገ መጥቷል። የዜጎችን የዲጂታል እውቀት ለማሳደግም ደግሞ አምስት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠና በኦንላይን እየተሰጠ ይገኛል።
ለመሆኑ በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች ምን ይመስላሉ? በቀጣይነትስ ከዘርፉ ምን ይጠበቃል?
የዓለም አቀፉ የሞባይል ኮሙኒኬሽን ሲስተም ማህበር (ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ጥናት፤ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚው ሀገራዊ አስተዋጽኦ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል። የሞባይል ኢንተርኔት ግንኙነቶች በ65 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ የ4ጂ ሽፋን በስምንት እጥፍ ጨምሯል። በዚህም እ.ኤ.አ. በ2023 ዘርፉ 700 ቢሊዮን ብር ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አበርክቷል። 57 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢም አስገኝቷል።
የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚነት እና በቴሌኮም ገበያ ላይ ያለው ውድድር እንዲጨምር ኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ዘርፉ እኤ.አ በ2028 ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ያበረክታል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ሥራዎች እንደሚፈጠሩ እና ለመንግሥት 57 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የታክስ ገቢ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ይፋ አድርጓል።
በእአአ 2028 ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ከሞባይል ኢንተርኔት ጋር ይገናኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ይህም በእአአ 2028 በግብርና ዘርፉ ላይ 140 ቢሊዮን ብር፣ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የ114 ቢሊዮን ብር አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የዲጂታላይዜሽን አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት አቅርቦትን ማመቻቸት፣ ፈጣን የቴሌኮም ማሻሻያ ማድረግ፣ የሞባይል ቀፎዎችን ዋጋ ተመጣጣኝነት ማሻሻል፣ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን ማስፋፋት እንዲሁም የዲጂታል ክህሎትን እና የመንግሥት አገልግሎቶችን ማሳደግ የሚሉ ጉዳዮችን ማህበሩ በምክረ-ሃሳብነት አቅርቧል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚውን በጂጂታል ቴክኖሎጂ ለማገዝ እያከናወነች ያለው ሥራ ውጤታማ ሆኗል። ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርትም ስምንት በመቶ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በተወሰዱ እርምጃዎች ሀገሪቱ ቀደም ሲል ከነበራት የኢንተርኔት ተደራሽነት እያደገ መጥቷል የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ይህም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሀገሪቱን በአፍሪካ ደረጃም ተጠቃሽ አድርጓታል።
በእኤአ 2018 የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 37 ሚሊዮን እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ 79 ሚሊዮን መድረሱን ጠቁመዋል። የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችም ከ16 ሚሊዮን ወደ 46 ሚሊዮን ማደጉን አንስተው፤ ዛሬ ላይ 424 ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥርም 34 ሚሊዮን ደርሷል።
ገጠሩ አካባቢ ማህበረሰብ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል በተመጣጣኝ ዋጋ የዘመናዊ ስልክ ቀፎ የማቅረብ ሥራ የተከናወነ ሲሆን በቀጣይነትም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለክታሉ።
ሥራውን ማስፋት አስፈላጊ በመሆኑም በተያዘው ዓመት አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመድቧል የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከዚህም ተጨማሪ 400 ከተሞች የ4ጂ፣ 15 ከተሞች ደግሞ የ5ጂ አገለግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ያስረዳሉ።
በትብብር የሚከናወኑ ሥራዎች ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደሚያስችሉ አመላክተው፤ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ያቀርባሉ።
በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዘላለም አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ማንበብና መጻፍ የሚችል ትውልድ ለማፍራት እንደሚሠራ ሁሉ የዲጂታል ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራትም በትኩረት እየተሠራ ነው። ለዚህ አስቻይ የሆኑ የተለያዩ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ተቀርጸው እየተተገበሩ ነው።
የአይሲቲ ትምህርት ከታች ጀምሮ እንዲሰጥ ማድረግ እና በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ከዚህም ባለፈ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከትምህርት ውጪ ላለው ማህበረሰብ የዲጂታል ክህሎትን የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን እየሰጡ ነው። በቀጣይነትም ለሁሉም ዜጋ የዲጂታል ክህሎት ማበልጸጊያነት የሚያገለግል ሥርዓተ ትምህርት እየተዘጋጀ መሆኑንም ይገልጻሉ።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም