በሰው ልጆች ማንነት ውስጥ አንዳንዴ ራስን የመውደድ ልማዶች ጎልተው ይታያሉ። ይህ እውነታ ደግሞ የተፈጥሯዊ ሥብዕና መገለጫ ነው። ከዚህ አኳያ ማንም ራሱን ከፊት አስቀድሞ ስለሌሎች ችላ ብሎ ቢገኝ ለምን ብሎ መቃወሙ ተገቢ ላይሆን ይችላል። ሰው ማለት በአንድም ይሁን በሌላ ራሱን ከሌሎች በላይ መመዘኑ ብርቅ አይደለምና ፡፡
በተለምዶ ሰዎች የራስ ጥቅም ተገዢዎች ናቸው ቢባልም አንዳንዶች ደግሞ ከራሳቸው ይልቅ ስለ ሌሎች መኖርን በተግባር ያሳዩናል። እንዲህ አይነቶቹ ልበ መልካሞች ፍቅር ይሉትን ታላቅ ጉዳይ ስለእውነት የሚተረጉሙ፣ ኖረውትም የሚያሳዩ ናቸው። እነሱ በትክክልም ከራሳቸው ይልቅ ስለሌሎች ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን ያውቃሉ፡፡
እርግጥ ነው፤ እንዲህ አይነት ልበ -መልካሞች አሉ ቢባል ከስንት አንድ ሊሆን ይችላል። ቅን አሳቢነታቸውን አውቆ የተከተላቸው ቢኖር ግን በሕይወቱ ጠቀሜታን ማግኘቱ አይቀሬ ነው። በነገሬ መግቢያ ላይ ወደ ጠቆምኩት የራስ ወዳድነት ጉዳይ ልመለስ። ይህን ርዕስ ለማንሳት ምክንያት የሆነኝ አንድ እውነታ ነው፡፡
ሰሞኑን በአንድ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንደዋዛ ከጆሮዬ የደረሰው ጉዳይ ሲያስገርመኝ ከርሟል። በድንገት ነው። ከእይታዬ የገባውን አጭር የቪዲዮ ምስል እንደነገሩ ማየት ጀምሪያለሁ። አንድ ሰው አንዲት አነስ ያለች እሽግ በእጁ ይዞ የሆነ ነገር ይናገራል። ፊቱ ላይ ግርምት ቢጤ ያየሁ መሰለኝ። መልዕክት እያስተላለፈ ሳይሆን አይቀርም፡፡
መጀመሪያ ሁኔታው የተለመደ የቲክቶክ ጨዋታ መስሎኝ ነበር። ቆይቶ ግን ጉዳዩ የቀልድ አለመሆኑን ስረዳ ዓይንና ጆሮዬን ሰጠሁት። ሰውዬው በተለየ ትኩረት ማብራራቱን ቀጥሏል። በእጁ አጥብቆ የያዘውን እሽግ ምንነት ለማወቅ ጓጓሁ። ከአንደበቱ በሚወጣው ቃል ደግሞ ይበልጥ ተስቤ ወደእአርሱ ማተኮሬን ቀጠልኩ።
ልብ አላልኩትም እንጂ ከሰውዬው በስተጀርባ ‹‹አቁሙ›› የሚል ጽሁፍ በጉልህ ይነበባል። ጽሁፉ በአምስት ጣቶች ምልክት የታጀበ ነው። ተናጋሪው ለማስጠንቀቅ ‹‹ቁም›› ለማለት የምናሳየውን ማገጃ ለጉዳዩ ሃያልነት ተጠቅሞበታል። ከአጠገቡ ደግሞ አስቀድሜ ያልኳችሁ እሽግ በወጉ ተቀምጦ ሁለመናውን ያስጎበኛል፡፡
በመጠኑ ለመረዳት እንደሞከርኩት ከእሽጉ በስተጀርባ ማንነቱን የሚገልጽ ስያሜ ተቀምጧል። የተመረተበት ዘመን ፣ አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜና ሌሎች መረጃዎች ጭምር በአግባቡ ተጽፈዋል። የመልዕክት አስተላላፊው ድምጽ አሁንም አልተለሳለሰም። ሃይለ-ቃል እንደተሞላበት ነው።
አሁን ጉዳዩ የተለመደው አይነት ተራ ወሬ አለመሆኑ ገባኝ። ‹‹እስከመጨረሻው አዳምጡት›› የሚለውን ማስፈንጠሪያ ነክቼ ሃሳቡን አንድ በአንድ ማዳመጥ ጀመርኩ። የተናጋሪው ሃሳብ ገና ከመነሻው እያስገረመኝ ነው። እውነትም እስከ መጨረሻው…. ማዳመጥ አለብኝ። በአትኩሮት ክትትሌን ቀጠልኩ፡፡
ተናጋሪው ዋናውን ሃሳብ ከመዘርዘሩ በፊት ከእሽጉ ጋር በተያያዘ ያዘነበትን እውነታ ይነግረናል። በላዩ ላይ የተጻፈውን ሀቅ ሳያነቡ ማንኛውንም ምርት በሚገዙና በሚጠቀሙ ሰዎች ልማድም በእጅጉ ማዘኑን፣ እንደውም ማፈሩን ጭምር አይደብቅም።
ይህ ሰው በእጁ አንስቶ የሚያሳየንን ብስኩት መሰል እሽግ ያገኘው ከሱቆቹ ሆድ በአንደኛው ለገበያ ቀርቦ ነበር። እሱ እንደሚነግረን ይህ እሽግ በዚህ ቦታ እንደዋዛ ለሽያጭ መቅረብ የሌለበት ነው። ነገር ግን እንደማንኛውም ብስኩት በተገቢው መጠቅለያ ተሸፍኗል። ተመሳሳይ ምርት በሚሸጥበት ዋጋም ለሽያጭ ቀርቦ የሚፈልጉት ጠያቂዎች ሁሉ እንዳሻቸው እየገዙት ነው፡፡
ጉዳዩ ይህ መሆኑ ብቻ አይደለም። ‹‹ጉድና ጅራት ከወደኋላ›› እንዲሉ ብስኩት ተብሎ የሚቸበቸበው ጣፋጭ እንደታሰበው ለዚህ ፍላጎትና ዓላማ ሲባል የተሠራ አልነበረም። ይህን ጥቅል አገላብጦ ምንነቱን ሊመረምር የሚፈልግ ቢኖር እውነታውን በግልጽ ይረዳዋል። ታዛቢው ሰውም በእሽጉ ጀርባ ላይ ተጽፎ ያገኘውን እውነት ቃል በቃል እንዲህ ሲል ያነበዋል፡፡
‹‹በምግብ እጥረት ወይም በርሃብ ምክንያት ለሚሞቱ ህጻናት በአሜሪካው የርዳታ ድርጅት በ ዩኤስ. አ.ዲ አማካኝነት ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ‹‹ነፍስ አድን ምግብ››
ጉድ ፈላ ! አዳሜ ለካ ‹‹ይጣፍጣል›› እያለ የሚኮረሽመው ‹‹ፍላንፍሌት›› ይሉት ብስኩት በርሃብ ለሚሞቱ ህፃናት የተዘጋጀውን ምግብ ኖሯል። ለዛውም ‹‹ነፍስ አድን›› የሆነውን ንጥረ ነገር። ጉዳዩ ከማስገረም አልፎ በእጅጉ አስደነገጠኝ። ታዛቢው ‹‹ባየሁት ሁሉ አፍሬያለሁ›› ያለው ለካ እውነቱን ነበር። መለስ ብዬ ቀሪ ንግግሩን ለማዳመጥ ጆሮዬን ጣልኩ። አሁንም ከነግርምቱ ሃሳቡን ይዘረዝር ይዟል፡፡
ታዛቢው አገኘሁት እንዳለው ጥናት በአፍሪካ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ600 ሺህ በላይ ህጻናት በየዓመቱ በርሃብ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ። በሀገራችን በብስኩት ስም በየሱቁ የሚቸረቸረው ንጥረ ነገር ደግሞ ለዚህ አይነቱ ፈታኝ ችግር ጥቅም ላይ እንዲውል ሲባል ብቻ የተዘጋጀ ነው። ነገሩ ሁሉ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ሆኗል ፡፡
እንደ አባባል ‹‹በልጅ አመሀኝቶ ይበሏል አንጉቶ›› ይሉት ብሂል ቢኖርም እንዲህ ዓይን ባወጣ መልኩ ነፍስን ከእጅ ላይ ለሚነጥቅ ሁኔታ ግን አልተተረከም። በእርግጥ ለዚህ ነውረኛ ድርጊት ተጠያቂው ይለይ ቢባል ሚዛኑ በገዢው ሳይሆን ለገበያ በሚያቀርበው ወገን ላይ ሊያጋድልና ሊያስረፈርድ ይችላል። እኔ ግን ተጠያቂነቱ ሁሉም ወገን ይውሰደው ባይ ነኝ፡፡
ለምን ቢባል ገበያ አቅራቢው በራስ ወዳድነት ሕይወትን በገንዘብ ሲለውጥ ገዢው አካልም አውቆም ሆነ ሳያውቅ የድርጊቱ አጋር ሆኗልና። ዛሬ ዓለማችን በብዙ ችግሮች እየተፈተነች ነው። ጦርነት ፣ስደት፣ ርሃብና ድርቅ በሚመላለስባት አፍሪካም በርካታ ጨቅላዎች በምግብ እጥረት እየረገፉ ናቸው፡፡
ለእኛ መሰል ድሃ ሀገራት ደግሞ የልመና እጆችን በሚያጥፉልን ምእራባውያን ክንድ መውደቅ አዲስ አይደለም። ሁሌም ለርሃባችን ማስታገሻ ስለነፍስ በሚሰጡን ትንፋሽ ማራዘሚያ ህይወታችን ይተርፋል። በስደትና መፈናቀል ጊዜ ለርሃብ የሚጋለጡ ህጻናት በነፍስ አድን ንጥረ ነገር ነፍሳቸው ትመለሳለች። ንጥረ ነገሩ ከዚህ አልፎም ብርታት ጥንካሬ ይሆናቸዋል። ምግብ ፣ እንጀራቸው ሆኖም ለነገዋ ጀንበር ያሻግራቸዋል።
ይህ ብስኩት መሰል ምግብ ለነዚህ ህጻናት ነፍስ አድን ነው። ከሞት አፋፍ ይመልሳቸዋል። ቆመው እንዲሄዱ፣ በወጉ እንዲተነፍሱ ሃይል ጉልበት ይሆናቸዋል ። ወዲህ ስንመለስ ደግሞ ይህ በርዳታ አልያም በነጻ የሚገባው ነፍስ አድን ዛሬ የሱቆች ተራ ሸቀጥ ሆኗል። ገንዘብ እየተከፈለበት ፣ ገበያ ያመጣል። የነጋዴዎችን ኪስ ያደልባል፡፡
በትኩረት ሳየው ወደነበረው ቪዲዮ ተመልሼ ከስር የተሰጡ አስተያየቶችን መቃኘት ያዝኩ። አብዛኞቹ ይህን ንጥረ ነገር ያውቁታል። እንደውም አንዳንዶቹ እሱን በመብላት ሱስ እንደያዛቸው ይናገራሉ። ከአስተያየቶቹ ጥቂት የማይባሉት ድርጊቱን የኮነኑ ናቸው። ከእነዚህ መሀል ደግሞ ንጥረነገሩን የሚሸጡ ነጋዴዎች ከሞተ ሰው ከፈን ቀዶ፣ ኪስ በርብሮ እንደመውሰድ ያህል የድርጊቱን ጸያፍነት ሊያሳዩት ሞክረዋል። በእርግጥም ይህና ሌላ ስሜት በውስጣችን ቢመላለስ አይገርምም። ጎበዝ ! ወዴት እየሄድን ይሆን ? ለጥቅም፣ ሲባል የሌሎችን ሕይወት እስከመንጠቅ መስገብገቡስ እስከመቼ? በዚህ ጉዳይ ብዙ ማለት ይቻላል። ለማንኛውም ልቦናውን ይስጠን።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም