የመፍትሄን ጠጠር – ሁሉም ይወርውር

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የሚያሳዩ እርምጃዎችን ሲወስድ አስተውለናል። ከእነዚህ ተግባራት ውስጥ ዘርፉን ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ እንደ አንዱ በመቁጠር የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉ ይጠቀሳል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መጠሪያ ሁለት ዘርፎችን አጣምሮ የያዘውን አደረጃጀት በመነጣጠል ሁለቱም በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ አንዲዋቀሩ ማድረጉ ሌላኛው የውሳኔው አካል ተደርጎ ይቆጠራል።

መንግስት በቱሪዝም ዘርፍ ከወሰዳቸው የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ፣ የመዋቅራዊ አደረጃጀትና የሕግ ማሻሻያዎች በተጨማሪ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አዳዲስ መዳረሻዎችን ማልማትና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄድ ካከናወናቸው ውጤታማ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ስራዎች ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት በእርግጥም ተጨባጭና መሬት ላይ የወረደ መሆኑን ያመላክታሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገርና ገበታ ለአገር ተገንብተው ወደ ስራ የገቡት እንዲሁም በገበታ ለትውልድ በሚል በግንባታ ላይ የሚገኙት ታላላቅ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ቱሪዝም መፃኢ ተስፋን ብሩህ እና ውጤታማ እንደሚያደርጉ የታመነባቸው ናቸው። ከአዳዲስ የመስህብ መዳረሻዎች ባሻገር ነባር የባህል፣ የታሪክ እና ሌሎች አርኪዮሎጂካልና የአርክቴክቸራል የኪነ ሕንፃ ቅርሶችን የመጠበቅ እና እድሳት የማድረግ ተነሳሽነትም እንዲሁ የመንግስትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው።

በመገናኛ ብዙሃንና ዘርፉን በሚመሩት የመንግስት ተቋማት አማካኝነት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ኢትዮጵያ የታሪክ፣ የባህል፣ የተፈጥሮ መልከዓ ምድር እና ሌሎችንም በርካታ ሀብቶች ከማልማትና ከመጠበቅ ያለፉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው። ከእነዚህ መካከል መስህቦቹ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት እንዲያገኙና ወደ አገሪቱ የሚገባው የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ለማድረግ በመንግስት በኩል ሀብቶቹን የማስተዋወቅና በዩኔስኮ በዓለ ቅርስነት የማስመዘገብ ጥረቶች ይጠቀሳሉ። በዚህ ስራ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የባህል፣ የታሪክና የአርኪዮሎጂካል ሀብት የሆኑ ከአራት በላይ ቅርሶች ለዓለም ማስመዝገብ ተችሏል።

ከላይ በዝርዝር ያሰፈርኳቸው ውጤታማ ስራዎች በመጪዎቹ ጊዜያት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኙ ያስችላሉ፤ ይሁን አንጂ ለቱሪዝም እድገት፣ ለቅርሶች መጠበቅ፣ ለቱሪስት ፍሰት መጨመርና በጥቅሉ ለአገርና ለማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ እድገት እነዚህ አርምጃዎችና ውጤቶች ብቻ በቂ አይሆኑም።

ለቱሪዝም ዘላቂ እድገት እነዚህ ውጤታማ ተግባራት በእጅጉ አስፈላጊ ቢሆኑም፣ ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር ለማንሳት በፈለኩት በአንድ ቁልፍ ጉዳይ ምክንያት ግን የሚፈለገው ውጤትና በሚፈለገው ጊዜ ላይመጣ ይችላል። ይህ ለቱሪዝም እድገት በእጅጉ ወሳኝ የሆነው ጉዳይ እንደ እኔ ምልከታ ‹‹ሰላም›› ነው። ቱሪዝምና ሰላም አይነጣጠሉምና፡፡

እንደሚታወቀው ቱሪዝም አንድ ሰው ለመዝናናት፣ ለህክምና እንዲሁም ለተለያዩ የግልና የቡድን ፍላጎቶችን ለማሳካት ሲል የሚያደርገውን የአጭር ጊዜ ጉዞ (ጉብኝት) መሰረት ያደረገ ነው። ይህ ማለት ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ አንድ ራቅ ወዳለ ስፍራ ሲጓዙ በሚያወጡት ገንዘብ እና በጊዜ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም ሰዎች ለጉብኝትም ይሁን ለሌሎች መሰል ምክንያቶች ጉዞ ለማድረግ ሲያቅዱ ቅድሚያ ግምት ውስጥ የሚያስገቡት ደህንነታቸውንና የሚሄዱበትን አካባቢ ሰላማዊ ከባቢ ማረጋገጥ ነው።

በዚህ ወቅት እንበልና ለጉብኝት የመረጡት አካባቢ ሰላም እና መረጋገት ከሌለበት፤ በተቃራኒው ግጭትና ደህንነትን ስጋት ላይ የሚጥሉ ተግባራት ከበዙበት ጎብኚዎቹ የጉዞ እቅዳቸውን መሰረዛቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ እርምጃቸው የሚሄዱበትን አገር አሊያም አካባቢን በቀጥታ የሚጎዳና ከጎብኚዎቹ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስቀር የዚያን አካባቢ ገፅታ በማጠልሸት ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል ይሆናል። በዚህ ምክንያት ነው ቱሪዝም ሰላም ከሌለ መሰረተ ልማት ቢገነባ፣ መዳረሻ ቢለማ በቂ እንደማይሆን አስረግጬ ለማስረዳት የሞከርኩት። ቱሪዝም ያለ ሰላም ‹‹አሳ ያለ ውሀ›› እንደማለትም ይሆናል።

የዘላቂ ቱሪዝም እድገት ያለ ሰላም እና መረጋጋት እውን እንደማይሆን መተማመን ላይ ከደረስን ወደሚቀጥለው ጉዳይ ማለፍ እንችላለን። አርሱም ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች፣ ከቦታ ቦታ በሚደረግ እንቅስቃሴ ወቅት በታጠቁ ኃይሎች የሚደርሰው አፈና መንግስት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ እያደረገ ያለውን ማሻሻያ፣ የልማት ስራና ከፍተኛ ትኩረት ይጎዳሉ፡፡

በመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፍን እድገት የሚያረጋግጡ በርካታ ማሻሻያዎች ተወስደዋል። ይሁን እንጂ በአገሪቱ በተከሰቱ እና አሁንም ድረስ በሚታዩ አለመረጋጋትና ግጭቶች ምክንያት የተደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚጎትቱ ተግባራት እየተመለከትን ነው። በማሻሻያዎቹ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲሻሻል ይጠበቃል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው አለመረጋጋት በቱሪስቶች ዘንድ ስጋትን የሚያጭር እና የጉዞ እቅዳቸውን ዳግም እንዲያጤኑ የሚያስገድድ ከባቢ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

በእርግጥ በእዚህ ሁሉ ስጋት ውስጥም ግን ወደ አገሪቱ የሚገባው የጎብኚ ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ የቱሪዝም ሚኒስቴር በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የውጪ አገር ጎብኚዎችን ኢትዮጵያ ስለማስተናገዷ ካወጣው መረጃ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው አለመረጋጋት ከኢንዱስትሪው የሚጠበቀውን ያህል ኢኮኖሚ እንዳያመነጭ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል። ይህ ሁኔታ ከሁሉም በላይ የአገር ውስጥም ሆነ የውጪ አገር ቱሪስቶች ለደህንነታቸው እንዲሰጉ በማድረግ በአገሪቱ ገፅታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳርፍ የሚችል ስጋትን ያጭራል።

በመፍትሄው ላይ ስንመክር

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመንግስት የተወሰዱ በጎ የቱሪዝም ማሻሻያዎች በሰላም እጦት ምክንያት እንዳይሰናከሉ ሁሉም ባለድርሻዎች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። እንደሚታወቀው መንግስት ከቱሪዝም ዘርፍ ከግብር እና ከአንዳንድ የውስጥ የገቢ ምንጮች ውጪ በቀጥታ ገቢ አያገኘም፤ ማህበረሰቡ፣ የግሉ ዘርፍ እና ቱሪዝምን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሁሉ የዘርፉ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ናቸው። ለእዚህም ሆቴሎች፣ የቱሪዝም ምርት አቅራቢዎች፣ አስጎብኚዎችና አስጎብኚ ደርጅቶችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

አንድ የቱሪዝም መስህብ ባለበት ስፍራ (እንደ ምሳሌ በትግራይ አክሱም፣ በአማራ ላሊበላ፣ በኦሮሚያ ባሌን መጥቀስ ይቻላል) የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ቱሪስቶች በስፍራው ሲገኙ የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል፤ መሬት ላይ ያለው እውነታም ይህ ነው። ነገር ግን በዚያ አካባቢ ወይም ወደዚያ አካባቢ የሚወስድ መንገድ ባለበት አካባቢ ግጭት ሲነሳ ጎብኚዎች አይኖሩም፤ በዚህ የተነሳም ሆቴሎች፣ መዳረሻዎች የቱሪዝም ምርት የሚያቀርቡ ሱቆች፣ አስጎብኚ ደርጅቶች እና መሰል አካላት በቀጥታ ተጎጂ ይሆናሉ። ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ይዳከማል፤ ስራ አጥ ይፈጠራል፤ ይበራከታል። ይህ በራሱ ይዞት የሚመጣው ሌላ ቀውስ አለ፤ ለማያቋርጥ የሰላም እጦትም ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በመሆኑም መንግስት ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ቀዳሚ ድርሻና ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ህብረተሰቡም የራሱ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከፍ ብለን እንደጠቀስነው በቱሪስቱ መምጣት የሚጠቀመው ህብረተሰብ ብዙ ነው፡፡ ትራንስፖርት አቅራቢው፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኚዎች፣ የቱሪስት ምርት አቅራቢዎች፣ ወዘተ በቱሪስቱ መምጣት በእጅጉ ይጠቀማሉ፡፡ የቱሪዝም ስፍራው ኤኮ ቱሪዝም ሲሆን ደግሞ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት በእጅጉ ይሰፋል፡፡

ይህ ሁሉ ህብረተሰብ የገቢ ምንጩ እንዳይቋረጥ፣ ስራ አጥነት እንዳይስፋፋ፣ የማንነቱ መገለጫ የሆኑ የባህል፣ የታሪክ፣ የቅርስ የአርኪዮሎጂና ሌሎች መስህብ ሀብቶቹ እንዳይወድሙ መጠበቅና መከላከል ይኖርበታል፡፡ ለእዚህም በራሱም ከመንግስት ጋር በመተባበርም በአካባቢው ብቻ ሳይሆን ወደ አካባቢው የሚወሰዱ መንገዶች፣ በጎረቤት አካባቢዎች ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን አበክሮ መስራት ይጠበቅበታል።

የቱሪስት መስህቦችን የሚጎዳ፣ የቱሪስት እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል ጠላት ከሩቅ ብቻ አይመጣም፡፡ በትናንሽ ጉዳዮች ያኮረፈ፣ የተቆጣም፣ የህብረተሰቡን መጠቀም የማይፈልጉ እንዲሁም ህብረተሰቡን በመጉዳት መንግስት የጎዱ የሚመስላቸው አካላት ተላላኪ የሚሆን የአካባቢው ሰው አይጠፋም፡፡ እንዲህ አይነቶቹን ችግሮች ህብረተሰቡ ራሱ አስፈላጊ በሆነ ጊዜም ከመንግስት ጋር በመሆን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት፡፡

በኢትዮጵያ መቀመጫቸውን ያደረጉ ኢምባሲዎች፣ ቆንፅላ ፅሀፈት ቤቶች እና አንዳንድ የዲፕሎማሲ ተቋማት አንዳንድ ኮሽታዎችን ሲሰሙ የውጪ አገር ዜጎች ለጉብኝት ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ መዳረሻዎች እንዳይንቀሳቀሱ፤ ከሄዱም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ክልከላና ማስጠንቀቂያ እንደሚያወጡ ባለፉት ዓመታት ተመልክተናል፡፡

በዚህ ክልከላ ሳቢያ አሁንም ድረስ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎች በሚገኙባቸው በዓላት፣ ቅርሶች እና የተፈጥሮ መዳረሻዎች በአለመረጋጋቶች ምክንያት ጎብኚዎች አይገኙባቸውም፤ የዚህ ምክንያት የሰላምና መረጋጋት መጥፋት ነው። ይህ ደግሞ በዘላቂነት የአገር ውስጥም ይሁን የውጪ ቱሪስቶች እምነት እንዳይኖራቸው ተፅእኖ ያሳድራል። ሰላምና መረጋጋቱ ቢመለስ እንኳን ዳግም መልካም ስምና ገፅታን መልሶ ለመገንባት አዳጋች ሊሆን ይችላል።

እነዚህ ቁልፍ ችግሮች መንግስት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ እየወሰደ ካለው የልማት፣ የጥበቃ፣ መስህብ የማስተዋወቅ ህግና ስርዓትን የማሻሻልና የመተግበር ስራ ባሻገር ተጨማሪ ኃላፊነት ወስዶ መስራት ያለበት ወሳኝ ተግባር እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ሁኔታው መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በዲፕሎማሲው መስክም እንዲሁ ብዙ መስራት እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ከሰላምና መረጋጋት እጦት ጋር ተያይዞ እንዲጠፋ የተደረገን ስም መመለስ ብዙ መስራትን ይፈልጋልና በዲፕሎሚሲው መስክም ብዙ ሊሰራ ይገባል፡፡

ህዝቡ በተለይ ዳያስፖራው በእዚህ ጉዳይ ላይ በትኩረት መስራት ይኖርበታል፡፡ መላ ሀገሪቱ በሰላም እጦት ውስጥ አይደለችም፤ የሰላምና መረጋጋት ችግር በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ይታወቃሉ፡፡ ሰላምና መረጋጋት ወደ አለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ጉብኝት በማድረግ ይህንን ጉብኝታቸውን በተለያዩ መንገዶች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች እንዲታወቅ በማድረግ ሀገሪቱ ሰላም ያለባትና ለጎብኚዎች ምቹ መሆኗንም ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

መንግስት በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ የሚፈለገው ውጤት እንዲታይ የሀብቱ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ማስተባበር እና ተከታታይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ማከናወንም ይጠበቅበታል። ማህበረሰቡ የሰላም እጦቱ ግንባር ቀደም ተጎጂ እንደሆነ በማስገንዘብ ሰላሙን እንዲጠብቅ ማድረግ ይገባል፡፡ ሁሉም አካል የሰላም እጦት ይዞት የሚመጣውን የተራዘመ መዘዝ ለመከላከል በቅንጀት መስራት ይገባዋል።

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You