ቱሪዝም የበርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን የሚጠይቅ ዘርፍ ነው። በዓለማችን ካሉ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የስራ እድል በመፍጠር ረገድም ወደር አይገኝለትም። ከአለም ሰራተኞች 10 በመቶ የሚሆኑት በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።
በዚህ መነሻ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና ግለሰቦች ለዘላቂ ቱሪዝም እድገትና አካታችነት ቅንጅታዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። በአብዛኛዎቹ አገራት በጥቅል አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ድርሻም ከፍተኛ ነው። ያደጉ አገራት ሀብትና የሰው ኃይል አቅማቸውን በማቀናጀት ላቅ ያለ ጠቀሜታን ያገኙበታል።
ከቱሪዝም የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ለማላቅ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ምሁራ በተደጋጋሚ ያስገነዝባሉ። ይህ መባሉም ሁሉም ባለድርሻዎች የተናበበና የተሰናሰለ ሕብረት መፍጠር እንደሚኖርባቸው ለማመላከት ነው።
ለዘላቂ ቱሪዝም እድገት መንግስት ፖሊሲ፣ ሕግና ስርዓትን ከማበጀት ጀምሮ የመስህብ ሀብቶችን በመጠበቅ፣ በማልማትና በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻን መውሰድ አለበት። የግሉ ዘርፍም እንዲሁ በሆቴልና በሌሎች መሰል አገልግሎቶች (hospitality and service)፣ በአስጎብኚ ድርጅት፣ በቱሪዝም ምርት አቅርቦቶች እና በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ ንቁ ሆኖ መሳተፍ ይኖርበታል። ማህበረሰቡም የማንነቱ መገለጫ የሆኑ እሴቶቹን በመጠበቅና በማስተዋወቅ የድርሻውን መውሰድ እንዳለበት ይታመናል። ይህ ቅንጅት ሁለንተናዊ እድገት እንደሚያመጣ ይታሰባል።
በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ የማይተካ ሚና ከሚጫወቱት ውስጥ የሆስፒታሊቲ ዘርፉ በመጀመሪያዎቹ ረድፎች ላይ ይቀመጣል። ሆቴሎች፣ ሎጆች፣ ሪዞርቶች እና ሬስቶራንቶች ወደ አንድ አገር ለጉብኝት የሚገቡ ቱሪስቶች በቂ ማረፊያ፣ መዝናኛና የተሟላ አገልግሎት አግኝተው ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ በማድረግ በኩል ወሳኝ ድርሻ አላቸው።
በዚህ ሁሉ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት ቱሪዝምን ከዋና ዋና ኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ ወስዶታል፤ ባለሀብቶችም መዋለ ንዋያቸውን በእዚህ ላይ እንዲያፈሱ እያበረታታ ይገኛል። በቱሪዝም ኢንቨስትመንት የግሉ ዘርፍ ከሚሳተፍባቸው ዋና ዋና መስኮች የሆስፒታሊቲ ዘርፉ ተጠቃሽ ነው።
የሆስፒታሊቲ ዘርፉ መነቃቃትና ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር ቱሪዝም በዘላቂነት ውጤታማ እንዲሆንና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም እንዲገኝ እድል እንደሚከፍት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ቱሪስቶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የተሟላና የአገር ገፅታን የሚገነባ መስተንግዶ አግኝተው ወደመጡበት እንዲመለሱ፤ በቀጣይም እምነት አግኝተው ዳግም ለጉብኝት እንዲመጡ የሆስፒታሊቲ መስኩ መዘመን የግድ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ጎብኚዎች በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ የመስህብ መዳረሻዎች እንዲመጡ የመሳብ አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ።
አቶ ሳህሌ ተክሌ በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ጥናትና ምርምር ክፍል ከፍተኛ ተመራማሪ ነው። እርሱ እንደሚለው፤ ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የመስራት አቅም መፍጠር ይችላሉ። በአገሪቱ የሚገኙ ስማቸውን የገነቡ ባለኮኮብ ሆቴሎችን ጨምሮ በሆስፒታሊቲ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባም ያስረዳል።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ቱሪስቶች በብዛት የሚመጡት በአስጎብኚ ድርጅቶች እና በመዳረሻ ቦታዎች አማካኝነት እንደሆነ ጠቅሶ፣ ሆስፒታሊቲ ላይ የሚሰሩትም ለቱሪስት ፍሰቱ ማደግ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ይገለፃል።
‹‹በአንድ የቱሪዝም መስህብ መዳረሻ ላይ በርካታ ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች ሊገኙ ይችላሉ›› የሚለው ከፍተኛ ተመራማሪው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው ልምድ ቱሪስቶችን በስፍራው ሲገኙ ከማስተናገድና ማረፊያ ከማቅረብ የዘለለ ድርሻ እንደሌላቸው የሚያሳይ መሆኑን ያመለክታል። በኢትዮጵያ የቱሪስት ቁጥሩ እንዲጨምርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ለማድረግ የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስልት ነድፈው በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ይገልፃል። ከዚህ መካከል የሆስፒታሊቲ ሚናን ማሳደግ አንዱ እንደሆነም ያስረዳል።
በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ሆቴሎች በመዳረሻዎች አካባቢ ለሚገኙ ቱሪስቶች የሚሰጡት የተሟላና አርኪ አገልግሎት ቆይታቸውን ለማራዘም ምክንያት ይሆናል የሚለው ከፍተኛ የሆቴልና ቱሪዝም ተመራማሪው አቶ ሳህሌ፤ ከሌሎች የቱሪዝም ዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር (አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሁነት አዘጋጆች፣ መዳረሻዎች) በመቀናጀት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዓለም አቀፍ ድርሻ ማሳደግ አንደሚችሉ ይገልፃል።
‹‹መልካም ስም ተሻጋሪ ነው። ገበያ እንዲፈጠርና ቱሪስቱ ፍላጎት ኖሮት ቆይታ እንዲኖረው ያስችላል›› የሚለው ከፍተኛ ተመራማሪው፤ ሆስፒታሊቲ ዘርፉ በቱሪዝም ላይ በጎ ተፅዕኖ እንዲኖረው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን ማሳደግ እንደሚገባ ያስረዳል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከአንዳንድ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ባሻገር ዓለም አቀፍ ቱሪስቱን በተሟላ ሁኔታ ሊያረካ የሚያስችል አገልግሎት ማግኘት አዳጋች መሆኑን አመልክቷል። ይህንን ለመቀየር የሚቀርበው ምርትም ይሁን አገልገሎት በቱሪስት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ጠቅሶ፤ ይህም የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ስምና ዝና በሚመጥን መልኩ ሊቀናጅ እንደሚገባው ያመለክታል።
የቱሪዝም ዘርፉ እድገት እንዲፋጠን ሆስፒታሊቲ ዘርፉ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የሚናገረው አቶ ሳህሌ፣ ከዚህ ውስጥ ሆቴሎች ዓለም አቀፍ የምርት ስም (Brand) መገንባት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁሟል። ለዚህም የግዴታ ታዋቂ ከሆኑ ድንበር ተሻጋሪ የሆቴል ስሞች ጋር ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልግ በመግለፅ አዲስና አገራዊ የሆኑ ታዋቂ ስሞችን መገንባት እንደሚቻል ያስረዳል።
ለዚህም የኃይሌ ሪዞርትስ እና ሆቴሎች፣ የጁፒተርና ካፒታል ሆቴሎች አሁን የደረሱበትን እውቅና ደረጃ በምሳሌነት ይጠቅሳል። የኃይሌ ሆቴሎችን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ታዋቂ የኢንዱስትሪው ተሳታፊዎችም ለቱሪዝም እድገትና ለቱሪስት ፍሰት መጨመር አዎንታዊ ድርሻ እንዳላቸው ይጠቁማል። የኢትዮጵያን መዳረሻዎች ሊጎበኝ የመጣ ቱሪስት እነዚህን አገልግሎት ሰጪዎች ተመራጭ ማድረጉ የማይቀር መሆኑን በማንሳት መሰል አርኪ አገልግሎት የሚሰጡ ስም ያላቸው ሪዞርቶች፣ ሎጆችና ባለኮኮብ ሆቴሎች ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ይናገራል።
‹‹ቱሪስቶች ከዋና ዋና መዳረሻዎች ጉብኝት ባሻገር ሁነቶች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት አላቸው›› የሚለው አቶ ሳህሌ፤ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ ሎጆችና የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው ተሳታፊዎች ከአስጎብኚ ደርጀቶች፣ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ማምጣትእንደሚችሉ ይናገራል። የቱሪስት ቆይታን ከማራዘም አንፃርም መሰል ሁነቶቸን ማሰናዳት ትልቅ ውጤት እንዳለው ነው ያመለከተው።
በሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ (ሆቴል፣ ሪዞርቶች፣ ሬስቶራንት፣ ሎጆችና የባህል ቤቶች) የምግብ ቱሪዝም እንዲያድግ ደርሻቸው የላቀ ነው የሚለው ከፍተኛ ተመራማሪው፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለመመገብ፣ ለማወቅ የሚመጡ ቱሪስቶችን ለመሳብ በእጅጉ ወሳኝ መሆናቸውን ነው የሚያስረዳው።
የባህል፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክና ቀደም ያሉ የኪነ ሕንፃ ቅርሶችን እንዲሁም የአርኪዮሎጂካል ግኝቶቸን ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ወቅት ባህላዊ ምግቦችን ለመመገብና ከአካባቢው ጋር ራሳቸውን ለማላመድ ፍላጎት እንደሚኖራቸው ጠቅሶ፣ ይህንን አገልግሎት በጥራት ለማቅረብ የሚያስችል ቁመና በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ መኖር እንደሚገባው አቶ ሳህሌ ተክሌ ምክረ ሀሳቡን ሰጥቷል።
የዝግጅት ክፍላችን የቱሪስት ቆይታን ለማራዘምና ፍሰቱን ለመጨመር ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ከተመራማሪው ባሻገር ሆቴሎች የሚመለከታቸውን አካላትንም አነጋግሯል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ሼባ ቪሌጅ ሪዞርትና እና ጃሎ ሆቴል ይገኙበታል።
ያብስራ አረጋዊ የሼቫ ቪሌጅ ሪዞርት ፍሮንት ኦፊስ ባለሙያ ነው። የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት በስካይ ላይት ለሶስት ቀናት ሲዘጋጅ የሼቫ ቪሌጅን የምርት ስም (Brand) ሲያስተዋውቅ ነበር። እርሱ እንደሚለው፤ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ሪዞርታቸው በርካታ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ማረፊያ ነው። በ25 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይህ ሪዞርት ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ በሚመጡበት ወቅት ቆይታቸውን አራዝመው፤ ተዝናንተውና ከተማዋን ጎብኝተው እንዲሄዱ ምቹ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በዚህም ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ አቅም እየሆነ ነው።
‹‹ቢሾፍቱ በሀይቅ ዳርቻዎቿ በስፋት ትታወቃለች። ሼቫ ቪሌጅ ሪዞርት ግን ሌላኛውን የከተማዋን ገፅታ የሚያሳይ ነው›› የሚለው የፍሮንት ኦፊስ ባለሙያው፤ ሪዞርቱ በተራሮች የተከበበና ለጎብኚዎች ማራኪ እይታን በሚፈጥር አቀማመጥ ላይ እንደሚገኝ ያስረዳል።
እንደ ባለሙያው ገለፃ ፤ የሼቫ ቪሌጅ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በከተማዋ ምቹ ቆይታን እንዲያደርጉ ታስቦ የተገነባ ነው። 20 ቪላ ቤቶች በባለ ሶስት እና በባለ አምስት መኝታ ቤቶች ሲኖሩት እያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ መሆናቸውን ያስረዳል። ይህም ቱሪስቶች የሚፈልጉትን ምቾትና የግል ደህንነት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። በተጨማሪ ተፈጥሮን ለመመልከትና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተራራ መውጫ (hiking) እና ሌሎች ተዝናኖት የሚፈጥሩ ሁነቶች እንደሚያዘጋጅ ነግሮናል። በቀጣይ ሪዞርቱ ለቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ አቅም መፍጠርና ኢትዮጵያ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን የመስራት እቅድ መያዙንም አስረድቶናል።
ሌላኛው የዝግጀት ክፍላችን ያነጋገረው በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘውን የጃሎ ሆቴል የሩም ዲቪዥን ማኔጀር የሆነውን ዳግም ጌቱን ነው። እርሱእንደሚለው የሆስፒታሊቲ ዘርፉ ለቱሪዝም እድገት ከፍተኛ ደርሻን ይወስዳል። ኢንዱስትሪው ያለ ሆስፒታሊቲ ዘርፉ አንካሳ መሆኑንም ይገልፃል። እርሱ በሩም ዲቪዥን ማኔጀርነት የሚሰራበት ጃሎ ሆቴልም ቱሪዝም በኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስተዋፆ ለማድረግ በማሰብ የተቋቋመ ነው።
ጃሎ ሆቴል በሻሸመኔ ከተማ የሚገኝ ባለ አራት ኮኮብ ሆቴል መሆኑን የሚገልፀው ሩም ዲቪዥን ማኔጀሩ፤ ለሶስት ዓመታትም የውጪ እና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን በእንግድነት በመቀበል የተሟላ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ይናገራል። ከተማዋ አምስት መግቢያ በሮች እንዳሏት በመግለፅም ቱሪስቶች፣ ኤግዚቢሽን፣ ስብሰባ እንዲሁም ሌሎች ሁነቶች ላይ የሚሳተፉ ተጓዦቸ ምርጫቸው ስለሚያደርጓት በቂ የሆስፒታሊቲ አቅርቦት መስጠት እንደሚያስፈለግ ያነሳል። ጃሎ ሆቴልም ይህንን ክፍተት ለመሙላት መቋቋሙን አስታውቋል።
‹‹በቱሪስቶች ከፍተኛ ተመራጭ እና በኢትዮጵያ ሁለተኛው የሆነውን የደቡብ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መስመር ተደራሽ ለመሆን እየሰራን ነው›› የሚለው ማኔጀሩ ዳግም ጌቱ፤ ወደ ባሌ፣ ወደ አርባ ምንጭ፣ ወደ ሀዋሳ፣ የሚደረገው ጉዞ አንዲያቀላጥፍና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር እየተጉ እንደሆነ ያስረዳል።
በየዓመቱ በሚካሄደው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ጃሎ ሆቴል ባሳለፍነው ዓመት በምርጥ የቱሪስትና የደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ የዋንጫ ተሸላሚ ነበር። ምርጫው ላይ ድምፅ የሰጡት ደንበኞች እና ቱሪስቶች ናቸው። ሆቴሉ ለቱሪስቶች የተራራ መውጣትና የእግር ጉዞ ከማዘጋጀት ባሻገር ለጉብኝት ተመራጭ የሆኑ መዳረሻዎችን በመጠቆም ተወዳጅ መሆኑንም ዳግም ነግሮናል። ይህን መሰል አገልግሎት በሁሉም በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ በሚገኙ የኢንዱስትሪው አንቀሳቃሾች ተግባራዊ ቢሆን አሁን ካለው የቱሪስቶች ቁጥር በበለጠ ኢትዮጵያ ማስተናገድ እንደምትችል አስታውቋል።
መረጃዎች አንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ በርካታ የመስህብ ስፍራዎችና መዳረሻዎች ቢኖሩም ይህንን የሚመጥን የቱሪስት ፍሰት ግን የለም። በየዓመቱ አንድ ሚሊዮንና ከዚያ በታች የሆነ ዓለም አቀፍ ጎብኚ ብቻ ኢትዮጵያን እየጎበኘ ነው።
በተቃራኒው ከኢትዮጵያ ያነሱ መስህቦች ያላቸው አገራት በሆስፒታሊቲ፣ በማስተዋወቅና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፍ ጥራት ያለው አቅርቦት ስላላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ያስተናግዳሉ። በዚህ ምክንያት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሰሩ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ስኬታማ የቱሪዝም ዘርፍ ለመገንባት እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የመንግስትንና የግሉ ዘርፍ አቅም አቀናጅታ መስራት እንደሚጠበቅባት ይመክራሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም