ችግሮችን በውይይት የመፍታት ሀገራዊ እሴቶችን መላበስ ይጠበቅብናል

እንደ ሀገር በየትኛውም ሁኔታ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ ማህበራዊ እሴቶች አሉን። እንደ ሀገር ካለው ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ ብዛሓነት አኳያም እሴቶቹ ዘርፈ ብዙም፣ መልከ ብዙም፣ ባለ ብዙ መፍትሔ አመላካችና አምጪ አቅም ባለቤትነትን የሚያጎናጽፉን ናቸው፡፡ በዘመናት መካከልም ሀገረ መንግሥቱን በማጽናት ሂደት እነዚህ እሴቶች የነበራቸው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ እንደሆነ ይታመናል።

ምክንያቱም፣ በሀገሪቱ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በውስጣቸው ከዛም ባለፈ ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር የሚያጋጥሟቸውን አለመግባባቶች መፍታት የሚያስችሉ ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች አሏቸው። እነዚህ እሴቶች ደግሞ ሰላምን ከማጽናት ባለፈ፤ እንደ አንድ በብዙ መልኩ እንደተጋመደ ማህበረሰብ ሀገር ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚያስችሉ የአስተምህሮ እና አስተምህሮውን ለመኖር የሚያስችለንን ሰብዕና እንድንላበስ የሚያደርጉን መሠረትም ናቸው።

በአብዛኛው ቁጭ ብሎ በመምከር/በመነጋገር ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳያድጉ፣ “አንተም ተው፤ አንተም ተው“ በሚሉ አስታራቂ ሃሳቦች እንድንመራም፣ እንድንገዛም የሚያደርጉት እነዚህ እሴቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን በማክበር፣ ከነሱ የሚመጡ የእርቅ ሃሳቦችን ለግለሰባዊ፣ ለቤተሰባዊ እና ማህበራዊ እርቅ/ ሰላም ወሳኝ አቅም ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።

በቀደሙት ዘመናት ትውልዶች በነዚህ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ማህበረሰባዊ እሴቶች ተኮትኩተው እንዲያድጉ፤ ከስነ ምግባር ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው አካላት ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶች እና የሃይማኖት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

በርግጥም እነዚህ እሴቶች ዛሬም ቢሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ሰላምን በማጽናት ሂደት ውስጥ ትልቅ አበርክቶ ያላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም በዚሁ ማህበረሰባዊ እሴት ውስጥ ያደጉ፤ ስለሰላም የተሻለ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል በሚባሉ ፖለቲከኞቻችን ሳይቀር ተገቢውን ከበሬታ አግኝተው እንደ አንድ የግጭት መፍቻ መሳሪያ ተደርገው ሲወሰዱ አይስተዋልም።

ከዛ ይልቅ በፖለቲካው መስክ የሚያጋጥሙ ችግሮችን/ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ሀገር እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ፤ እንደ ሀገር ለዘመናት በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድናልፍ አስገድደውናል። ሀገርን ለድህነት እና ለኋላቀርነት ዳርገዋል፤ ትውልዶች ሕልሞቻቸውን እንዳይኖሩ ፈተና ሆነውባቸዋል።

ይህ ችግር ዛሬም ላይ እንደሀገር ያልተሻገርነው፤ አሁን ያለውን ትውልድ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለ ያለ፤ በትውልዱ እጣ ፈንታ ላይ ተግዳሮት ሆኖ የቆመ የአስተሳሰብ ስብራት ነው። አሁንም ቢሆን በችግሩ ዙሪያ ቆም ብለን በሰከነ መንፈስ ማሰብ ካልቻልን እንደቀደሙት ዘመናት ነገዎቻችንን ሊናጠቀን እንደሚችል እሙን ነው።

በተለይም በፖለቲከኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ለውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ትልቅ አቅም እየሆኑ ባለበት በዚህ ዘመን፤ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ያለመታከት መስራት ይገባል፡፡ ከዚህ ባለፈም ለማህበራዊ እሴቶች ቦታ በመስጠት ማህበረሰቡ የኔ ባላቸው እሴቶች ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንዲያደርግ እድል መስጠት፤ ለጥረቱም አጋዥና ተባባሪ ሆኖ በአለመግባባቶች ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶች ቀድሞ በሚደረጉ መነጋገሮችና መወያየቶች እንዲረግቡ ሆነው ሀገር እና ሕዝብን ካልተገባ ዋጋ መታደግ የተገባ ነው።

“የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል” እንደሚባለው፣ ዓለም ለተፈጠሩ ግጭቶች መፍትሔ ከመሆን ይልቅ በቡድን ተቧድኖ ከግጭቱ ስለሚያተርፈው ትርፍ እያሰላሰለ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ለሚታዩ ችግሮች ተጨማሪ ችግር እየሆነ ባለበት በዚህ ዘመን፤ ልዩነቶች ወደ ግጭት ሳይሻገሩ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ሀገራዊ አጀንዳ ላላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጭምር ዋነኛ የቤት ሥራ መሆን አለበት። ይሄ ደግሞ ስለ ሀገር እና ሕዝብ በተጨባጭ ስለማሰባቸው ማሳያ ነው።

ለዚህ ደግሞ፣ በየአንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ዘላቂ የችግር መፍቻ እሴቶችን ለትውልድ ግንባታ አቅም አድርጎ መውሰድ ይገባል፡፡ ይሄን ማድረግ ሲቻል እሴቱን አውቆ የሚጠቀም ትውልድ ይፈጠራል፤ አሁናዊ ችግሮቻችንንም እልባት የመስጠት ሰብዕናን ያላብሰዋል፡፡ ምክንያቱም እሴቱን ያወቀ ትውልድ ለችግሮቹ መሻገሪያ አቅም አድርጎ ይጠቀማል፡፡

በመሆኑም ለራሱ ማህበራት እሴቶች ታምኖ ግጭቶችን መከላከል የሚያስችል፣ ማህበራዊ ስብእና ያለው ትውልድ መገንባት፤ ለዚህ የሚሆን ማህበረሰባዊ ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል። ይሄ ሲሆን፣ ችግሮችን በውይይት የመፍታትን ሀገራዊ ባህልን በተጠናከረ መንገድ ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ትውልዱ ልዩነቶችን በኃይልና “በይዋጣልን” መንፈስ ለመፍታት ከመነሳሳት ይልቅ፤ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ለራሱ፣ ለሀገሩ እና ለመጪው ትውልም የሚተርፍ የአስተሳሰብ መሰረት እንዲኖረው ያግዛል፡፡ ይሄንን በማድረግም እንደ ሀገር የሚታዩ ችግሮቻችንን ቁጭ ብሎ በውይይት የመፍታት እሴቶቻችንን መላበስ ከሁላችን ይጠበቃል፡፡ አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You