ምርትን በወቅቱ መሰብሰብ የሁላችንንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው

የህልውናችን መሰረት፣ የኢኮኖሚያችን ዋልታና ማገር የሆነውን፣ የግብርናውን ዘርፍ (ሴክተር) ከሌሎቹ ሁሉ ለየት የሚያደርገው አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር የ“ባለ ድርሻ አካላት” ጉዳይ ነው።እንደሚታወቀው ሁሉም ዘርፍ ባለ ድርሻ አካላት አሉት። ለምሳሌ ትምህርትን ብንወስድ ባለ ድርሻ አካላቱን ተማሪ፣ ወላጅ፣ አስተማሪ ወዘተ እያልን ልንዘረዝራቸው እንችል ይሆናል።

ወደ ግብርናው ስንመጣ ግን ጉዳዩ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፤ እሱም የግብርናው ዘርፍ ባለ ድርሻ አካላት አንድ፣ ሁለት… ተብለው የሚዘረዘሩ ሳይሆኑ፤ የግብርና ባለ ድርሻ አካላት ምግብ የሚመገብ ፍጡር ሁሉ መሆኑ ነው። ምግብ የሚመገብ ሁሉ የግብርናና ተዛማጅ ዘርፎች (ጉዳዮች) ሁሉ በጥብቅ ይመለከቱታል።

በግብርና ጉዳይ ከተሜ ነኝና አይመለከተኝም፤ የተማርኩ ነኝና አይኮነስረኝም፤ ባለስልጣን ነኝና አይነካካኝም፤ ተማሪ ነኝና ምን አገባኝ ወዘተ ይሉ ነገር አይሰራም፤ ቦታም የለውም።ዘንድሮ እናስመዘግባለን ብለን ካቀድነው አጠቃላይ እድገት ውስጥ 40 በመቶውን የሚሸፍነው፤ ከ80 በመቶ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቀጥተኛ የህልውና መሰረት (livelihood) የሆነው፣ ወደ ውጪ ከምንልካቸው ምርቶች 90 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው የግብርናው ዘርፍ ነው።

ከሙያና ባለቤትነት አኳያ ጉዳዩ ለገበሬው ተደርጎ ይወሰዳል እንጂ ጉዳዩ የሁላችንም ነው። ይህ አገላለፅ ካለንበት የፀደይ ወቅት አኳያ ምን ማለት እንደ ሆነ ለብዙዎቻችን ግልፅ ቢሆንም፤ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልእክት “የጋራ ርብርብን የሚጠይቀው የምርት አሰባሰብ ተግባር ላይ ሁላችንም እንሳተፍ” የሚል ነው።

በግልፅ እንደምንመለከተው የሀገራችን ታራሽ መሬት በአረንጓዴ ሰብሎች ተሞልቷል። ከዛም አልፎ አንዳንድ የሰብል አይነቶች ደረስኩ፣ ደረስኩ … እያሉ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ድሮው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በ“የከተማ ግብርና” አማካኝነት በከተሞቻችንም እየተስተዋለ መሆኑ የእያንዳንዳችን ተግባርና ኃላፊነት ከቀድሞው ዘመን ለየትና ሰፋ ያደርገዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የዝናብ ተከታትሎ የመዝነብ ሁኔታ ይታያል። በዚህ በፀደይ ወቅት ደግሞ ሁለቱ አብረው የሚሄዱ አይደሉም፤ አንዱ አንዱን ማምለጥ አለበት። ማምለጥ ካለበት ደግሞ በእኛው ቁጥጥር ስር ያለው ሰብል የመሰብሰብ ተግባር ነውና እሱ ላይ ሁሉም ሰው ሊረባረብና በሰብል ስብሰባው ተግባር አርሶ አደሩን ሊያግዝ የግድ ይሆናል።

ሁላችንም እንደምናውቀው፣ አንዳንዶቻችንም በብዛት እንደ ተሳተፍነው በምርት ስብሰባ ወቅት አርሶ አደሩን ማገዝ አዲስ ተግባር አይደለም። ትምህርት ቤቶች ለቀናት ተዘግተው ተማሪዎችና መምህራን ገበሬውን ያግዛሉ። የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሳሪያቸውን አስቀምጠው በምርት ስብሰባው ተግባር ከአርሶ አደሩ ጎን ሲቆሙ ማየት ከቶውን አዲስ ይደለም። ሌላውም እንደዛው።

በተለይ አሁን አሁን፣ በሀገራችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ ወዘተ ጉልህ ሚናን የሚጫወተው ግብርና በከተሞችም ከመስፋፋቱ አኳያ በሰብል ስብሰባው ወቅት የሚሳተፉ ባለ ድርሻ አካላትን አይነትና ብዛት ከፍ የሚያደርገው ነው፤ ምርት የመሰብሰብ ተግባር ለገጠር አካባቢዎች ብቻ የተተወ ይመስል የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ፣ ዛሬ ተግባርና ሙያው የሁሉም ይሆን ዘንድ እውቀትና ቴክኖሎጂ ፈቅደዋል። በመሆኑም፣ ወቅቱ ከዳር እዳር ሁሉም ኃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ ግድ ይላል ማለት ነው።

በተለይ፣ ወቅቱ በአየር ንብረት ለውጥ (መዛባት) ምክንያት መሆኑ ግልፅ ሆኖ፣ ያልተጠበቀ ዝናብ ድንገት፣ ምንም ሳይታሰብ መዝነቡና በመሰብሰብ ላይ ያለን፤ ወይም ሊሰበሰብ የተቃረበን ሰብል ማበላሸቱ የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ አርሶ አደሩ ቢመስልም፣ ችግሩ የሁላችንም፣ የሀገር ነውና በምርት ስብሰባው ሂደት ያለችውን ክፍተት ተጠቅመን የመሰብሰብ ስራውን ልናከናውን ይገባል።

ዘንድሮ “ተወደደ” የማይገልፀው ጤፍ በሚቀጥለው ከነጭራሹ ከገበያው እንዳይርቅ፤ ዘንድሮ ተወደደ እያልን የምናማርረው በቆሎ በሚቀጥለው ከነስሙ እንዳይሸፍት ወዘተ ከወዲሁ ሲለፋና ሲደክም የቆየውን ገበሬ በሰብል ስብሰባው እንኳን ልናግዘው፤ ከጎኑም ሆነን ያደረሰውን ምርት ልናሰባስበው ይገባል።

እንደ አህጉር ስንመለከተው፣ የግብርናው ዘርፍ በአፍሪካ ደረጃ በየዓመቱ እየተሻሻለና ምርትና ምርታማነት እየጨመረ እንደመጣ በተደጋጋሚ ይነገራል። በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ስለ መሆኑ በርካታ ወቅታዊ ጥናቶች እያመለከቱ ነው። ይህ ስኬት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችለው ስለ ታረሰና ተዘራ ብቻ ሳይሆን ተሰብስቦ ጎተራ እስከ ገባ ድረስ ብቻ ነውና የምርት ማሰባሰብ ስራ የዋዛ ተግባር ሳይሆን የብዙኃንን ርብርብ የሚጠይቅ ነው።

በተለይ እንደ እኛ ያሉ፣ የሁሉም ነገር የጀርባ አጥንታቸው ግብርና የሆኑና በዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች ያልተደራጁ ሀገራት በምርት መሰብሰብ ወቅት የዜጎች ርብርብ ማስፈለጉ በጠቅላላ እውቀት ደረጃ ግንዛቤ የተያዘበት ጉዳይ ነው። ልክ አርሶ አደሩ እርስ በርሱ እንደሚረዳዳና እንደሚደጋገፍ ሁሉ (ደቦ፣ ጂጌ፣ ወንፈል · · ·)፤ ከተሜውም ሆነ በየአካባቢው ያሉ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሰብል ስብሰባው ተግባር ሙሉ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል።

“ለፍቶ መና” ከመሆኑ በፊት፣ የየመስሪያ ቤትና ተቋማት ሥራ ኃላፊዎችም በዚሁ መንፈስ ተቋሞቻቸውን ሊያንቀሳቅሱ ይገባል። በተለይ የዘርፉ ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጎን ዞር ሊሉ አይገባም። የአየር ትንበያ ባለሙያዎችም ወቅቱ አደገኛ መሆኑን ተገንዝበው የማንቃትና ማሳወቅ ሥራዎቻቸውን ተግተው ያከናውኑ ዘንድ ያለንበት የፀደይ ወቅት ያስገድዳልና አደራ!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You