ወንደላጤ ጓደኛሞች አብይ ጾምን ለመቀበል ከአንድ ታዋቂ ስጋ ቤት ተቀምጠናል፡፡ ብርንዷቸውን ለመቁረጥ ያላቸውን የብር መጠን ሲያሰሉ ጥብስ ነው የምንበላው ብዬ ራሴን ከቁርጡ አገለልኩ፡፡ ጦይሌው ደግሞ “ዛሬስ የትኛው መጽሐፍ ቅዱስ ብርንዶ እንዳይበላ ከልክሎ ይሆን?” አለ በማሾፍ፡፡ ሁልጊዜ ይቀልዳል፤ ጫት አትቃም ስለው “መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አትቃም የሚል ካለ አሳየኝ” ብሎ ይሟገታል፡፡ አሁን ደግሞ ይኸው ብርንዶ እንዳይበላ የትኛው መጽሐፍ ቅዱስ ከለከለ? ይላል፡፡ ቢቀበለኝም ባይቀበለኝም ካልክስ አልኩትና ለማስረዳት በስልኬ ያስጫንኩትን መጽሐፍ ቅዱስ በረበርኩ፡፡
“ደም የነፍስ ማደሪያ ነውና ከሰውነታችሁ መካከል ደማችሁን እንዳልፈልግ ደመ ነፍስ ያለችበትን ስጋ አትብሉ” የሚለው ሀይለ ቃል የሰው ዘሮች በሙሉ ብሩንዶ እንዳንበላና ልንጠብቀው የሚገባ የጸና ዘላለማዊ ህግ መሆኑን መጽሐፈ ኩፋሌ ምዕራፍ 7÷6-14 እንደሚያትት አሳየሁት፡፡ ጃፈርም ቀበል አድርጎ “ይህ ካልክ ካህናቱስ በየሰርጉና በየተስካሩ ሙዳ ስጋቸውን ለምን ይጎምዳሉ?” በማለት ጠየቀኝ፡፡ በውይይቱ ደስ እየተሰኘሁ ማስረዳቴን ቀጠልኩ፡፡
ግራኝ አህመድ አቢያተ ክርስቲያናትን በሚዘርፍበትና በሚያቃጥልበት ጊዜ ካህናቱ ቅርስና ንዋያተ ቅድሳቱን ይዘው በዱር በገደል ተሰደዱ፡፡ ያን ወቅት ነፍሳቸውን ለማቆየት እንስሳትን አርደውና ስጋቸውን ጠብሰው ይመገቡ ነበር፤ ዳሩ ግን የግራኝ አህመድ ሠራዊት የሳቱን ጭስ እየተከተለ በካህናቱ ላይ ግፍና በደል ስላደረሰባቸው ጠብሰው ይመገቡት የነበረውን ስጋ በጥሬው ለመብላት ተገደዱ በማለት ገለጻ አደረኩለት፡፡ ቧልት የማይለየው ጦይሌው “ጀለሴ ከሃሳብህ የተረዳሁት ቢኖር…በማወቅና ባለማወቅ በመከራና በደስታ የተፈጠረ ስህተትም ቅብብሎሽ እንዳለው ነው” አለና አስተናጋጁን በጥቅሻ ጠራው፡፡
ትህትናው ከፊቱ እየተነበበ ከአንገቱ አዘንብሎ ለመታዘዝ ፍላጎታችንን ጠየቀን፡፡ ለኔ ኖርማል ጥብስ ለነሱ አንድ ኪሎ ቁርጥ አዘዝን፡፡ አስተናጋጁም ከሄደበት እየሮጠ መጥቶ “ይቅርታ ወንድሞቼ የምትፈልጉት በኛ ወይስ በመንግሥት?” አለን፡፡ ግራ ተጋብተን እርስ በእርስ ተያየን፡፡ ተረበኛው ጦይሌው “ሁለቱንም አምጣልን” አለው፡፡ የሚሆነውን በትግስት ስንጠባበቅ አስተናጋጁ ግራ ቀኝ ሁለት እቃ አንጠልጥሎ ተመለሰ፡፡ ከፊታችን እንዳኖረው ጃፈር አስተናጋጁ ላይ አፍጥቶ “የትኛው ነው የእናንተ ?” በማለት ጠየቀው፡፡
በቤቱ ያለው የስጋ አቅርቦት ሁለት አይነት ነው አንደኛው በዝቅተኝ ዋጋ የሚቀርብ ዋጋውን የሚመስል ሲሆን ፤ ሌላው ደግሞ ዋጋው እንደምጻት ቀን ቢያስደነግጥም ስጋው ጥራት አለው፡፡ መጠኑ ግን ደህና ጎረምሳ አንዴ ጎርሶ ዳግም አያሰናዝርም፡፡
ለነገሩ ስጋ ከበላሁበት ወቅት ይልቅ ስጋት ውስጥ የገባሁበት አጋጣሚ ነው በልጦ የሚታወሰኝ ። ስጋ ለባሽ ሁኜ ስጋ ላልበላ ምዬ ነበር። የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ሆኖብኝ ሻርኩት እንጂ። “በድሮ ጊዜ በግ ገዝተን ቆዳውን እጥፍ ስለምንሸጥ ስጋ በነጻ ነበር” እያሉ ሲያወጋጉኝ ያማረህን መብላት እና መሳም ድሮ ቀረ ማለት ነው? ብዬ አጠይቃለሁ። እግረ መንገዳችሁን ወደ ልጅነት እድሜዬ ልውሰዳችሁና ትዝ ያለኝን ነቆራ ላጫውታችሁ።
አንድ ቀን ከቀይ ባህር እየጠጣ ያደገና ከጥጃነቱ አንስቶ ጉርጉሱም ላይ እየፈነጨ ያደገ ያልፋል የሚሰኘው በሬያችን አዲሱን በረት አለምደው ብሎ
“ያውና ይታያል ያገሬ ሰማይ ፣
እንዲህ ሆዴ ቆርጦ መጥቻለሁ ወይ።
እ ህ ህ ይላል ያሰሩት ፈረስ፣
ሳር ባይጥሉለት የልቡ ባይደርስ።”
እያለ አንጀት በሚበላ እንጉርጉሮ እንደተብሰከሰከ ኑሮ ሳይጥምበት አለፈ።
የቀዬው ሰው ሁሉ ከደም የወፈረ እንባ ማፍሰስ ብቻ ሳይሆን የያልፋልን ስጋ የበላን እንደሆነ “እርም ይሁንብን” አሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በቀያችን ወንድ ጥጃ ከተወለደ ያልፋል ነው የሚባለው።
ወደ ቀድሞ ነገር እንመለስ እንድል መጽሐፉ ፍራጅ አውጡለት ተብለን እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ያለን ህጻናት የያልፋልን ስጋ እንድንበላ ተፈቀደ። ይህን ማድረጋቸው ስለ ልጆቻችን ብለህ ማረን ማለታቸው ነው። እናላችሁ አንድ ጊዜ ፍየል ሳግድ የአሰብ ጠራራ ፀሐይ አቅም ነስቶኝ ቁጥቋጦ ተከልዬ የያዝኩትን ቋንጣ ስነጭ ወዲያ ማዶ ካለው በረት ውስጥ አጮልቆ የሚያይ እኩያዬ የሆነ እረኛ እጁን ዘርግቶ እንድሰጠው ለመነኝ።
ላካፍለው አልኩና ገና ለገና ከማሳው ዳር ስላየኝ ብቻ “አዝመራዬን ከብት አስበላህ” ብሎ በሳማ የገረፈኝ አባቱ ፊቴ ድቅን ሲል ልቤ ሻክሮ ነፈኩት። “ቆይማ የኛ በሬም ሲሞት አልሰጥህ” አለ ያው ልጅ እምቢ ስላልኩት በግኖ። ሳቅ እያንፈራፈረኝ የትኛው በሬያችሁ? ስለው የሰሙ አንድ አዛውንት ከኋላዬ ቆመው ኖሯል በብረት ከዘራቸው ጎሸም ሲያደርጉኝ ምላሴን ዋጥኩት።
ቶሎ ብዬ ቀልብ በመግዛት ጉልበት ስሜ የእግዜር ሰላምታ ዘየርኳቸው። በብረት ከዘራቸው ሲጠቅሱት ስጋዬን የከለከልኩት ልጅ ዙሪያ ገባውን አይቶ ማንም እንደሌለ ሲያውቅ ብርር ብሎ መጣና እግራቸው ስር ወድቆ እጅ ነሳ። ጉንጭ ለጉንጭ አሳሳሙንና ጸሎት አድርሰው ሲያበቁ ያነገቱትን አገልግል አውርደው ቢፈቱልን በእንቁላል ታጅቦ በቅቤ የራሰ ቋንጣ ፍትፍት ጋር ተገናኘን ። አስኳሉን ብቻ በልተን አልቀረንም አስኳላ ትምህርትም ገባን ። እርስዎስ ለምን አይበሉም? ብለን ብንጠይቃቸው ትዝታቸውን ያባርሩ ይመስል ጭራቸውን እያወዛወዙ ከስጋ የራቁበትን መንስኤ ነገሩን።
“አንድ የባለጸጋ ልጅ አይኔን አልፋ ልቤ ውስጥ ገባችና ደሜን አሞቀችው። ይሁን ተባብለን የፍቅርን አቦል ፉት ማለት እንደጀመርን ጥሜን ሳልቆርጥ ከተማ ገብታ ተሰወረችኝ። ናፍቆት አዝዬ ሃብቴ አለቀ ሳልል በየስርቻው ፈለኳት። በአንደኛው ቀን ረፋድ ላይ ልቡልቅ ስጋ ቤት ዘልቄ የጎዳችውን ጎኔን ልጠግን የሚያዛጋ ኪሴን አማክሬ እንዳቅሙ አዘዝኩ። ጣሪያ የሚበሳ የንግድ ሳቅ ትኩረቴን ስቦት አቀርቅሬ ወስፋቴን ከማደምጥበት ቀና ስል ውባለም ጋር አይን ለአይን ተገጣጠምን ። ለካስ የከተማ መኳንንት ወዳ ነው ወሬዋ የጠፋኝ። ከዚያን እለት ጀምሮ ስጋ በአፌ ዞሮ አያውቅም አሉና በፉጨት አንጎራጎሩ ።
ላሜን አረድኩና በአህያ ጫንኳት፣
ጅብን ንዳ ብዬ ውሻን ደገምኩት፣
ሁለት ሃሳብ የለሽ ከመንገድ በሏት።”
ጓደኞቼ የጎደለውን ሂሳብ “ሙላ” ሲሉኝ ከሄድኩበት ሰመመን ተመለስኩ።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም