የጡት ካሰንር ባደጉት ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ የሚከሰት የጤና ችግር ቢሆንም በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ስርጭቱ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ እንደመጣ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። እ.ኤ.አ በ2022 ከዓለም ጤና ድርጅት የወጣው ሪፖርት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በጡት ካንሰር በሽታ መያዛቸውንና ከነዚህ ውስጥ 666 ሺ 103 የሚሆኑ ሴቶች ሕይወታቸውን እንዳጡ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ደግሞ በየዓመቱ 16 ሺ 904 ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚያዙና በየዓመቱ 9 ሺ 626 የሚሆኑት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር ከሌሎች የካንሰር አይነቶች ጋር ሲነፃፀር በገዳይነቱ ወደር የማይገኝለት መሆኑን ያሳያል።
ለዚያም ነው የዓለም ጡት ካንሰር ቀን በየዓመቱ እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችና ዝግጅቶች እየተከበረ የሚገኘው። ቀኑን አስመልክቶም ከሰሞኑ ‹‹ዓለም ፍሬ ፒንክ ሃውስ ካንሰር ፋውንዴሽን›› የተሰኘውና በጡት ካንሰር ዙሪያ የሚሰራው ድርጅት የጡት ካንሰር ግንዛቤን ለማስፋት የሚያስችል የፓናል ውይይት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን አካሂዷል። በነገው እለት ደግሞ 3 ሺ 500 ሰዎች የሚሳተፉበትና በጡት ካንሰር ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ማስፋትን ታላሚ ያደረገ የእግር ጉዞ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።
ወይዘሮ ፀዳለ ፅጌ የዓለም ፍሬ ፒንክ ሃውስ ካንሰር ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ አባል ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ከተቋቋመ አስራ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል። ድርጅቱ የተቋቋመው በአሜሪካን ሀገር አትላንታ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ስራውን ከጀመረ ስድስተኛ ዓመቱን ይዟል። በነዚህ ስድስት ዓመታት ውስጥ ድርጅቱ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል። አስካሁንም ከ 8 ሺ በላይ ለሚሆኑ የጡትና በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ሕሙማን ሴቶች ድጋፍና እንክብካቤ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይህ የጥቅምት ወር እንደመሆኑ ደግሞ የጡት ካንሰር ቀን ሊከበርና ግንዛቤ ሊሰጥበት የሚገባ በመሆኑ የድርጅቱ አብዛኛው ትኩረት በጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ይሆናል። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ሴቶች የሚጠቁትም በጡት ካንሰር በመሆኑም ነው። ድርጅቱ ማረፊያ አጥተው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጡት ካንሰር ሕክምና እየተሰጣቸውና በድህነት ሕይወት ላይ ያሉ ሴቶችን ተቀብሎ የምግብ፣ የማረፊያ፣ የትራንስፖርትና የመድሃኒት ድጋፍ ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ሲያደርግ የቆየው።
አሁንም በአዲስ አበባ ከየካ ጤና ጣቢያ ጀርባ በሚገኘው የድርጅቱ ማእከል እናቶችና እህቶችን በመቀበል ይህን አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገው። ስለዚህ ዋናውና ትልቁ ነገር በጡት ካንሰር ዙሪያ ግንዛቤ መስጠት ነው። ሕክምናም ከመምጣት በፊት በሽታውን ካለማወቅ በጣም ጉዳት ከደረሰና በሽታው ከተባባሰ በኋላ ወደ ማእከሉ የመምጣት ሁኔታ በመኖሩ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸውም ሕይወታቸው የሚያልፍ ብዙ ሴቶች ይኖራሉ።
ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ሴቶች ሕመሙ ከተባባሰና ከጠነከረ በኋላ ነው ወደ ሕክምና የሚመጡት። ወደ ሕክምና ሲመጡ ደግሞ በሆስፒታል ወረፋ መጠበቅ፣ በትራንስፖርት፣ መድሃኒት ፍለጋና በሌሎችም ብዙ መንገላታት አለ። ይህም በሽታው ተባብሶ በአጭር ግዜ ውስጥ ሕይወታቸው የሚቀጭበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ በጡት ካንሰር ቀድሞ መከላከል ላይ ብዙ መሰራት እንዳለበት ይታወቃል።
በሽታው ከጀመረም በኋላ አንዳንድ ምልክቶች ሲታዩ በአካባቢ ወደሚገኙ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራና ሕክምና ማግኘት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ቢሰራ በርካታ ሴቶችን ከሕመምና ስቃይ ብሎም ከሞት ማዳን ይቻላል።
የጡት ካንሰር በሽታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ ነው። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ የሚችለውን ነገር ሁሉ እያደረገ ነው። ነገር ግን የሚዲያ ባለሞያዎች በተለይ በሕመሙ ዙሪያ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ብዙ ሊሰሩ ይገባል። ድርጅቱ በተከታታይ አራት ዓመታት የእግር ጉዞ ለማድረግ ሲያስብ አንዱና ዋነኛው ዓላማ በጡት ካንሰር ዙሪያ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው። የዘንድሮውንም የእግር ጉዞ ‹‹ብርታትሽ ብርታቴ›› በሚል መሪ ቃል 3 ሺ 500 ሰዎች በማሳተፍና መነሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ነገ ያካሂዳል።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን እንደሚናገሩት፣ የጡት ካንሰር የሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎና ርብርብ ይፈልጋል። ምክንያቱም የጡት ካንሰር ከጤና ባሻገር የስነ ልቦና፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ሌሎች ጉዳቶችንም የሚያስከትል በመሆኑ ነው። ከታማሚው ባሻገር ቤተሰብን፣ ማህበረሰብንና ሀገርን የሚነካም የጤና ችግር ነው። ስለዚህ የጡት ካንሰርን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃም ትኩረት የሚሰጥባቸው ነገሮች አሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት በየዓመቱ የጡት ካንሰር እያደረሰ ያለውን ተፅእኖ በተለያየ ግዜ በሪፖርቶቹ ያመላክታል። ካንሰር በቶሎ ወደ ሕክምና በመሔድ ሕክምና ካልተደረገ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። ስለዚህ በጡት ካንሰር ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች ቁጥርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛው ስፍራ ይይዛል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች መካከለኛና ዝቀተኛ ኢኮኖሚ ባላቸው ሃገራትም የጡት ካንሰር በሽታ ከግዜ ወደ ግዜ እየተስፋፋባቸውና ከፍተኛ የሕብረተሰብ ጤና ችግር እየሆነ መጥቷል።
የጡት ካንሰር በሽታን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአብዛኛው የሚከሰቱት ቅጥ ባጣ ውፍረት፣ ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግና ሱስ አምጪ ነገሮችን ማለትም ሲጋራ በማጨስና ከልክ ያለፈ አልኮል በመውሰድ ነው። ለጨረር የመጋለጥ ሁኔታዎች፣ በቤተሰብ ወይም በዘር፣ የሆርሞን መጠኖች መዛባት ለጡት ካንሰር አጋላጭ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆኖ የጡት ካንሰር በግዜ ተደርሶበት ምርመራና ሕክምና ከተደረገለት ብዙ ጉዳት ሳያስከትል ወደ ጤና መመለስ ይቻላል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ደግሞ በታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ያለው አብዛኛው ሰው ወደ ጤና ተቋም የሚመጣው የጡት ካንሰር ደረጃው ከፍ ካለ በኋላ ነው። ይህም በሕክምና የሚደረገውን እገዛ ብዙም ውጤታማ እንዳይሆን ትልቅ ተግዳሮት ይሆናል። ይህ ሲባል የጡት ካንሰር ታማሚዎች የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ከፍ ያለ ደረጃ አለ። አብዛኛዎቹ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ከ65 እስከ 70 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡት ካንሰሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው።
የጡት ካንሰር ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ወደ ጤናማ ሕይወት ለመመለስ የሚደረገው ሕክምና ደግሞ በጣም አዳጋች ይሆናል። ስለዚህ ትልቁ ነገር በመላው ዓለም እየተከበረ ያለው የጡት ካንሰር ግንዛቤ መስጫ ወር ላይ ግንዛቤን ይበልጥ ማሳደግ ያስፈልጋል። በተለይ የጡት ካንሰር ከሌሎቹ የካንሰር አይነቶች ቀድሞ ለመከላከል የተሻለ በመሆኑ ሴቶች በቤታቸው በየእለቱ መስታወት ፊት ቆመው ጡታቸውን እያዩ በቀላሉ በመዳሰስና ይህን ዘዴ በመጠቀም የጡት ካንሰርን የሚያመላከት ነገር መለየትና ባፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም በመሔድ ሕክምና አግኝተው ካንሰሩ የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ማስቆም ይችላሉ። ለዚህም ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ከዚህ በፊት በጡት ካንሰር ተይዘው አስቀድመው ወደ ሕክምና ቦታ በመሔዳቸው ታክመው የዳኑ ሴቶች መኖራቸው ነው።
መሪ ስራ አስፈፃሚዋ እንደሚገልፁት፣ ብዙ ግዜ ካንሰር የሕመም ምልክት አይኖረውም፡ ፡ ከዚህ አንፃር ብዙ ግዜ መዘናጋቶች ይታያሉ። የጡት ካንሰርን በሚመለከት በተለይ ደግሞ ሴቶች ጠዋት ላይ ሲነሱ ጡታቸውን በእጃቸው በመዳሰስና በመመርመር ምልክቶች ካዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም ሄደው በምርመራ ተገቢውን ሕክምና ሊያገኙ ይችላሉ። በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሴቶች በየዓመቱ በጡት ካንሰር በሽታ ይያዛሉ፤ ለሞትም ይዳረጋሉ። በኢትዮጵያም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በዚህ በሽታ በየዓመቱ ይያዛሉ። ከነዚህ መካከል ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ይሞታሉ።
ከዚህ አንፃር ዘግይቶ ወደ ሕክምና ተቋም መምጣት የጡት ካንሰር በሽታን ምን ያህል ሊያወሳሰብው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ስለዚህ አጠራጣሪ ምልክቶች ሲታዩ ሴቶች ወደ ሕክምና ተቋም በአፋጣኝ እንዲመጡ ከተሰራ በርካቶችን በጡት ካንሰር ሳቢያ ከመሞት መታደግ ይቻላል። ጤንነታቸው ታውኮ በሕይወታቸው ላይ ጫና እንደ ግለሰብ፣ እንደቤተሰብና እንደሀገር ከመድረሱ በፊት ወደጤና ተቋም በግዜ መጥቶ አስፈላጊውን ምርመራና ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋል።
እንደ ጤና ሚኒስቴርም የጡት ካንሰርን ለመከላከል እንደሌሎቹ የካንሰር አይነቶች ሀገር አቀፍ ስትራቴጂ ወጥቶለታል። የካንሰር ምርመራና ሕክምናን በተለያዩ የጤና ተቋማት ላይ እንዲሰጥ የተለያዩ ባለሞያዎችን፣ ምርመራና ሕክምና አግልግሎትን ይፈልጋል። ከዚህ አንፃር ከላብራቶሪ ጀምሮ እስከ ትልቅ ውስብስብ የሆነ መሰረተ ልማት እስከሚፈልገው ራዲዮቴራፒ ድረስ በኢትዮጵያ አገልግሎቱ ይሰጣል።
የባለሞያዎችን አቅም ከማጎልበት አንፃር ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች ጤና ሚኒስቴርና ሌሎች በዚህ ዙሪያ ላይ ያሉ አጋሮች በጋራ በመሆን በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሰጡ ይገኛሉ። የሕክምና ተቋማትን አቅም ለማስፋት በተለይ የጡትና ሌሎችም ካንሰሮችን ሕክምና የሚሰጡ በተለይ ኬሞቴራፒ መድሃኒት ሕክምና ቁጥሩን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። በአሁኑ ግዜም ወደ 30 የሚሆኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ ጤና ተቋማት ይህን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
የኬሞቴራፒ መድሃኒት ሕክምና አገልግሎት በጣም ውድና የመድሃኒት አቅርቦትን ይፈልጋል። ከዚህ በመነሳት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በመመደብ ቢያንስ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ለዚህ የኬሞቴራፒ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ መድሃኒቶች 65 ከመቶ ድጎማ ተደርጎባቸው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ወደ ጤና ተቋማት እንዲደርሱና አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። ይህም ላለፉት በርካታ ዓመታት የነበረ አገልግሎት ነው። በተጨማሪም የጡት ካንሰር ሕክምና መመሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለጤና ተቋማትና ባለሞያዎች እንዲደርስ ተደርጓል።
የዓለም ጤና ድርጅት የምዕተ ዓመቱ ግብ ብሎ ካስቀመጣቸው የጡት ካንሰር ላይ መቀመጥ ካለባቸው ሶስት ዋና ዋና መለኪያዎች አሉ። አንደኛው የጡት ካንሰር ደረጃው ከፍ ሳይል ሴቶች በቶሎ ወደ ጤና ተቋማት እንዲመጡ ማድረግ ነው። ይህም 60 ከመቶ ያህሉ ሴቶች የጡት ካንሰሩ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ሆኖ ወደ ጤና ተቋማት እንዲመጡ የሚያግዝ ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ ግንዛቤ መፍጠር፣ ተቋማት ላይ ያሉ ባለሞያዎችን አቅም ማሳደግ እንዲሁም የተቋማትን አገልግሎት መስጫ ማስፋት አብሮ የሚታሰብና እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው።
ሁለተኛው መለኪያ ደግሞ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ወደ ጤና ተቋማት ከመጡ በኋላ አስፈላጊ የሆነ ምርመራ አገልግሎት የሚያገኙበት ስርዓት እንዲጠናከር ማድረግ ሲሆን ይህም ቢያንስ በ60 ቀናት ውስጥ ተመርምረው ትክክለኛው ነገር እንዲገኝና እንዲለይ የማድረግ ነው። ይህም በተመሳሳይ እየተሰራበት ያለ ነው። ሶስተኛው መለኪያ ከሕክምና አንፃር የሚታይ ሲሆን 80 በመቶ የጡት ካንሰር ታማሚዎችን ሕክምናቸውን በተገቢው ሁኔታ አግኝተው እንዲያጠናቅቁ ነው። ሕክምና ሲባል ደግሞ የተለያዩ ሕክምናዎች አሉ። ከቀዶ ሕክምና ጀምሮ፣ የመድሃኒት፣ ራዲዮቴራፒ፣ ከቴሞቴራፒና የመሳሰሉት ሕክምናዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪም የስነ ልቦና ድጋፍ ይፈልጋል።
አብዛኛው ሰው ወደ ጤና ተቋም የሚመጣው የጡት ካንሰር ደረጃው ከፍ ካለ በኋላ ነው። ይህም በሕክምና የሚደረገውን እገዛ ብዙም ውጤታማ እንዳይሆን ትልቅ ተግዳሮት ይሆናል
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም