ብሪክስ በዓለም የኃይል ሚዛን አሰላለፍ ሌላኛው አማራጭ እና ወሳኝ ኃይል ሆኖ መምጣት ከጀመረ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2006 ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ እና የምዕራባውያን ተጽዕኖ በተጫነው ነባራዊ ዓለም ተገዳዳሪ አማራጭ መንገድና አይዲዮሎጂ ያላቸው ሀገራት በጋራ በመሆ ን የፈጠሩት ጥምረት ነው፡፡
ሀገራቱ ይሄን ጥምረት ሲመሰርቱ የአሜሪካ እና ምዕራባውያን የበላይነት የሚዘወረውን የኃይል ሚዛን ለማስተካከል በማለም ነው። ከዚህ ባሻገር ለታዳጊ ሀገራት አማራጭ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ነጻነት መፍጠር ሌላ እሳቤ አለው። በዚህ እረገድ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሀገራቱን ተጽዕኖ ፈጣሪነት የታየበትና በርካታ የዓለም አገራት ጥምረቱን ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩበት ሊሆን ችሏል፡፡
ለዚህ ነው ባሳለፍነው ዓመት የብሪስክ አባላት ሲመሰረት የነበሩት አባላት ጨምረው ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሜሬትን በማካተት የአባላቱ ቁጥር ከጥር 2024 ጀምሮ ወደ አስር ከፍ ማለት የቻለው፡፡ የአባላት ቁጥሩ መጨመር ትብብሩ እያደገና እየጠነከረ ለመምጣቱ ሁነኛ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። የብሪክስ ሀገራት ጥምረት በዓለም የኃይል ሚዛን ውስጥ በኢኮኖሚውም ይሁን በፖለቲካው ያላቸው ድርሻ ግዙፍ መሆኑ በአደባባይ እየታየ ያለ ሀቅ ሆኗል፡፡
የብሪክስ ሀገራት ስብስብ ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሕዝብ በመያዝ የመላው ዓለምን 45 በመቶ ሕዝብ የሚጠቀልሉ ሲሆን የሀገራቱ ኢኮኖሚም ከ28 ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ዶላር በላይ በማለፍ አሁን ላይ ሀያ ስምንት በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ የዓለም ምርት እየሸፈኑ ይገኛሉ፡፡
ብሪክስን ወሳኝ ሚዛን የሚጫወት የኃይል ስብስብ የሚያደርገው ሌላኛው ጉዳይ አባል ሀገራቱ የዓለምን 47 በመቶ የሚሆነው ነዳጅ ያለባቸው ሀገራት ስብስብ መሆኑ ሲሆን ይህ ሁሉ አቅም በምዕራባውያን እና አሜሪካ ተጽዕኖ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ሌላ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አማራጭ ኑሯቸው ስብስቡን እንዲቀላቀሉ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡
በተለይም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ከባድ ተጽዕኖ ያላቸው በምዕራባውያን ተጽዕኖ የሚዘወሩት የዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን ሊገዳደር የሚችል ለታዳጊ ሀገራት የተለያዩ ብድሮችን የሚያመቻች አዲስ ባንክ እ.ኤ.አ በ2014 መመስረታቸው የስብስቡን ጠንካራ አቅም የሚያሳይ ሌላኛው መስካሪ ጉዳይ ነው፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለም ሀገራት መገበያያ ሁኖ በማገልገል ያለውን እና የአሜሪካ ጉልህ ተጽዕኖ የሚታይበትን የዓለም የግብይት ስርዓት በማስተካከል ሀገራት በዶላር ከመገበያየት ይልቅ በራሳቸው የገንዘብ ምንዛሬ እንዲገበያዩ የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችንም እያከናወኑ ይገኛል፡፡
በሰሞነኛው የዓለም አጀንዳም የሩሲያዋ ካዛን ከተማ አስራ ስድስተኛውን የብሪክስ መደበኛ ስብሰባ ለማስተናገድ ሽር ጉድ ስትል ሰንብታለች፡፡ ይህ መደበኛ ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳወዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሜሬት ስብስቡን ከተቀላቀሉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ስብሰባ ሲሆን ብሪክስ ከሚለው ስያሜ ወጥቶ ብሪክስ ፕላስ በሚል መጠሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥቅምት 12 እስከ 14 2016 ዓ.ም ድረስ ተካሂዷል፡፡
በዚህ ስብሰባ ከአባላት ሀገራቱ በተጨማሪ ከሀያ በላይ ሀገራት በሩሲያዋ ካዛን ተጋብዘው ጉባኤውን በንቃት ተሳትፈዋል። ብሪክስን መቀላቀል ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አኳያ እስካሁን ባለው መረጃ ከሰላሳ በላይ ሀገራት የብሪክስ ስብስብን ለመቀላቀል ያመለከቱ ሲሆን ከምስራቅ ኤሽያ እስከ አፍሪካ የተለያዩ ሀገራት የጥምረቱን ወሳኝነት በመረዳት የአባልነት ጥያቄያቸውን አቅርበው ውሳኔ እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡
ለብሪክስ አባልነት ጥያቄ ካቀረቡት ሀገራት መካከልም የዓለማችን ትልቅ የሙስሊም ቁጥር ሕዝብ ካላት ኢንዶኒዥያ እስከ የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ፣ ከአፍሪካ ባለ ብዙ ሕዝብ ቁጥሯ ናይጀሪያ እስከ ማሌዥያ ድረስ የተለያዩ ወሳኝ ሀገራት አባል እንሁን የሚል ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የብሪክስ ፕላስ አባላት ስብስብን መቀላቀል የሚያስገኘው ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም የአሜሪካ እና ምዕራባውያን ጫናን ለማቅለል እና የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እሳቤያቸው ሁሉ በእነሱ እንዲቃኝ የሚገደዱበትን ጫና በመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽዖ ይዞ መጥቷል፡፡
ሀገራት በእራሳቸው ገንዘብ እንዲገበያዩ እና አቅማቸውን እንዲያድግ ስብስቡ የጀመራቸው ስራዎች ብዙ ታዳጊ ሀገራት ወደ ብሪክስ ለመግባት እንዲሳቡ አድርጓቸዋል፡፡ በአባል ሀገራቱ መካከል የሚካሄደው የንግድ ልውውጥም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ እና በዓለም ባንክ እና ገንዘብ ድርጅት ፍቃድ ብቻ ላይ ተመስርቶ ሲሰጥ የነበረውን የብድር እና የእርዳታ ስርዓት በማስቀረት ሀገራት የተሻለ የብድር እና የእርዳታ አማራጭ እንዲኖራቸው የእድል በር ከፍቷል፡፡ የብሪክስ አባላት የንግድ ልውውጥ አቅምን የሚያሳየው ሌላኛው ጉዳይ የዓለማችን የቡድን ሰባት ሀገራት ተብለው የሚጠሩ ሀገራትን የንግድ ልውውጥ በመብለጥ ቀዳሚ ሁነው መገኘታቸው ነው፡፡
ምዕራባውያን በሰበብ አስባቡ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማስፈጸም እና ጫና ውስጥ ለመክተት በተለያዩ ሀገራት የሚያደርጉትን ማዕቀብ በመቀነስ ሀገራት ምርታቸውን በራሳቸው ምንዛሬ እየተገበያዩ ቀላል እና ፈጣን የሆነ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር አስችሏል፡፡
የተለያዩ ታዳጊ ሀገራት በተለይም የአፍሪካ እና የኤሺያ ሀገራት እንዲሳተፉ ፍላጎታቸውን እየገለጹ እና ስብስቡን ለመቀላቀል የበለጠ እንዲረባረቡ ያደረጋቸው ጉዳይም ይሄ ነው፡፡
የዓለማችን የኃይል ሚዛን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በቀዝቃዛው ጦርነት የምዕራብ እና የምስራቅ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እና አሜሪካ መሪነት ዓለም ለሁለት ተከፍላ ካሰለፈች በኋላ (በተለይም የሶቭዬት ሕብረት መፍረስን ተከትሎ) ዓለም የአንድ ዋልታ በተለይም የአሜሪካ ተጽዕኖ እጅግ የጎላበት ነበር፡፡
በአሜሪካ እና በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት የበላይነት ሲዘወር ከነበረው የቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት የአሜሪካ የበላይነት በዓለም ሚዛን ገዝፎ ይታይ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ የብሪክስ መምጣት የአባላት ሀገራት ትብብርን በማሳለጥ ለዓለማችን ሰላም፣ ኢኮኖሚ እና አጠቃላይ ሁኔታ ዘርፈ ብዙ ተዋናዮች ያሉበት ነባራዊ ዓለም መምጣቱን ብዙዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ይሄም ብዙ ሀገራት በዓለም ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ላይ በባለቤትነት የሚጫወቱበት ዘርፈ ብዙ ተዋንያኖች ያሉበት ስርዓት እየመጣ መሆኑን መስካሪ ሲሆን ይሄ ነባራዊ ሁኔታ መምጣቱ ሰላማዊ እና አሳታፊ የሆነ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲኖር በማስቻል ሁሉም ሀገራት ለመላው ዓለም ሰላም እና እድገት የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱበትን እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት የንግድ እና ኢኮኖሚ ልውውጥ ቻይና ከጀመረችው የቤልት እና ሮድ መሰረተ ልማት አንስቶ አፍሪካን እስያን እና ላቲን አሜሪካን በማስተሳሰር ረገድም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ብሪክስ በዓለማችን የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ተቋማት ለውጥ እንዲያደርጉ በተለይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት የታዳጊ ሀገራትን ድምጽ ሰምተው ማሻሻያ እንዲያደርጉ አባል ሀገራቱ ወሳኝ የኃይል ሚዛን እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
በአፍሪካ ከአምስቱ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ብሪክስን ከተቀላቀለች በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ በሩሲያ ካዛን እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) እና ልዑካን ቡድናቸው በተገኙበት በውጤታማነት ተሳትፋለች፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በዓለም ፖለቲካ ካላት ወሳኝነት አንጻር በስብሰባው የሚፈጠሩ እድሎችን በአግባቡ ተጠቅማበታለች ማለት ይቻላል፡፡ መሪዎች ንግግር ባደረጉበት በዚህ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) የኢትዮጵያን አቋም ለአባል አገራቱ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) በንግግራቸው አሁን ዓለማችን ከተጋረጠባት አያሌ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ሌሎች መሰል እንቅፋቶች ለመሻገር የብሪክስ አባል አገራት የባለብዙ ግንኙነት መድረክ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። እንደ አዲስ የብሪክስ አባል አገርነትም ትብብሩ ወደላቀ ደረጃ እንዲያድግ እንደምትሰራ አሳውቀዋል። ይህ ንግግራቸው ኢትዮጵያ በጥምረቱ ላይ የሚኖራትን ቀጣይ ድርሻ ያመላከተም ነበር።
የሪፐብሊክ ኦፍ ራሺያ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲንን ጨምሮ በርካታ የአገር መሪዎች በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ ጥምረቱ በማደግ ላይ ያሉትን እና ያደጉ አገራትን እኩል በፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንሳታቸው ኢትዮጵያ ለጥምረቱ ያላትን እምነት ያመላከተ ነበር። በማደግ ላይ ያሉ አገራት በዓለም ፍትሀዊ ያልሆነ ፋይናንስ ስርዓት ምክንያት እንቅፋት እንደገጠማቸው በንግግራቸው ላይ የጠቀሱት ይህም ኢፍትሀዊና ያልተመጣጠነ እድገት ማስከተሉን ገልፀዋል። ይህ ንግግራቸው በቀጥታ በአሜሪካና ምእራባውያን ጠንካራ እጅ የሚዘወሩትን የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ ኢፍትሃዊነት የተቸ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያው የብሪክስ ተሳትፎና ንግግራቸው ላይ ትኩረት የሰጡት የአየር ንብረት ለውጥ ነበር። በዚህ ረገድ ያደጉ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግን ችላ ማለታቸው ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት መሆኑን በማንሳት ተችተዋል። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ 40 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል እየሰራች መሆኑን በማንሳትም ጉዳዩ ትብብርና ትኩረት እንደሚሻ ለማሳየት ጥረት አድርገዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ከመደበኛ ስብሰባው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው በቀጣይ ከሁሉም ሀገራት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በማጠናከር መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ከመደበኛ ስብሰባው ጎን ለጎን በእስካሁኑ ቆይታቸው ከአረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት መሃመድ ዛይድ አልናህያን፣ ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ ከኢራኑ ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዥሺካን ጋር ያደርጓቸው ውይይቶችም ኢትዮጵያ የብሪክስ ስብስብን በውጤታማነት እየተጠቀመችበት ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የስብሰባው አዘጋጅ ከሆነችው ሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የነበራቸው ቆይታም ፍሬያማ እንደነበር የወጡት መረጃዎች ያመለክታሉ። ፕሬዚዳንት ፑቲን ኢትዮጵያ በዓለም ፖለቲካ ትልቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን በመግለጽ ኢትዮጵያ በብሪክስ ንቁ ተዋናይ ሁና እንድትቀጥል ያላቸውን መልካም ዝግጁነት እና በጎ ምኞት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያም ከሰላሳ በላይ የተለያዩ ሀገራት የአባልነት ጥያቄ ባቀረቡበት የብሪክስ ስብስብ የተመረጠችበት መንገድ የሀገሪቱ አቅም እና ጠቀሜታ የሚያሳይ መሆኑን በመረዳት እስካሁን በመንግስት የተሰሩ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ወሳኝ የሆነውን የብሪክስ ትብብር መቀላቀሏ ይዞት የሚመጣውን እድል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ያግዛታል። ቀጣይነት ያለው አሁንም መሰራት ያለባቸው ተግባራትን ማከናወን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅም ነው፡፡
በኤልያስ ጌትነት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም