አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ምን ይዟል?

ዜና ትንታኔ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው 31ኛው መደበኛ ስብሰባ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ እንዲፀድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ከሰሞኑም የግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማትና የክልል የግብርና ኃላፊዎች በአዲሱ ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የግብርናና ገጠር ልማት የሚመራበት የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የማስፈጸሚያ ስልቶች በ1994 ዓ.ም ተቀርጸው ሥራ ላይ መዋላቸው ይታወቃል። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ከግብርናው ዕድገት ጋር አብሮ መጓዝ ባለመቻሉ፣ አሁንም የምግብ ዋስትና ያላረጋገጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች መኖራቸውና ለኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ጥሬ ዕቃ በበቂ ዓይነት፣ መጠንና ጥራት ማቅረብ አለመቻልም ፖሊሲውን ለመቀየር እንደ ምክንያትነት ይነሳሉ፡፡

ለውጪ ንግድ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን አቅርቦት ማሳደግና ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አለመቻልም ሌላኛው ተግዳሮት እንደሆነ ይጠቀሳል።

የግብርናና ገጠር ልማት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ፣ በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ ያሉትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እና የግብርናውን ዘርፍ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር የበለጠ ለማስተሳሰር በሥራ ላይ የነበረው የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ስልቶች በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መተካት አስፈላጊ ሆኗል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

ለመሆኑ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ምን አዲስ ነገር ይዟል? ከቀድሞ ፖሊሲ ምን ይለየዋል? የሚሉ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሥራ ኃላፊዎች ለኢፕድ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ፖሊሲ ዳይሬክተር አቶ ረታ ወጋር፤ የቀድሞ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የሰው ጉልበትና መሬት ላይ ያተኮረ ሲሆን አዲሱ ፖሊሲ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከቀድሞ ፖሊሲ እንደሚለይ ይጠቅሳሉ፡፡

አዲሱ ፖሊሲ በገጠር ያለው የሰው ኃይል ጉልበቱን እርሻ ላይ ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደ ኢንዱስትሪዎች የሚሻገርበትን እድል የሚያመቻች ነው ይላሉ፡፡

የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ የቀድሞው ፖሊሲ የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት መብት የገደበ ሲሆን፤ የአሁኑ ፖሊሲ አርሶ አደሩ መሬቱን አሲዞ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር የማግኘት ፣ መሬቱን የማከራየት ፈቃድ እንዲሁም የመሬቱን የማልማት አቅም እንደ ካሳ የመጠቀም መብት ተሰጥቶታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ካፒታል ለአንድ ሀገር እርሻና ገጠር ልማት እድገት ወሳኝ በመሆኑ በአዲሱ ፖሊሲ የተካተተው አንዱ ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ ረታ፤ በቀጣይ በርካታ የግል ሴክተሮች ወደ ገጠር የሚገቡበት፣ ባንኮች የሚቋቋሙበት፣ አርሶ አደሮች በቅርበት የብድር አቅርቦት የሚያገኙበት እንዲሁም መሬት ያሉ ሰብሎችንም ሆነ እንስሳቶችን ተጠቅሞ ዋስትና የሚያገኝበት እድል የሚፈጥር ፖሊሲ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ከፖሊሲው ከሚጠበቁ ውጤቶች አንዱ ቀጣይነት ያለው ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው፡፡ የአርሶ አደሩን ገቢ መጨመር ሌላኛው የሚጠበቅ ውጤት ነው ሲሉ ገልጸው፤ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥና ሁሉንም ዜጋ አሳታፊ የሚያደርግ ፖሊሲ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

ፖሊሲውን ለማስፈጸም በዋናነት የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስዶ የሚሰራ ሲሆን፤ ሌሎች 12 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፖሊሲውን እንዲያስፈጽሙ መንግሥት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም ፖሊሲው እንዲተገበር የሚያግዙ አዋጆች፣ ደንቦችና የህግ ማሕቀፎች ጸድቀው ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ ረታ፤ እስካሁንም 23 አዲስና ሰባት የሚከለሱ አዋጆች እንዲሁም 25 የሚሆኑ አዲስ ደንቦች እየተዘጋጁ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሥራ ላይ የነበረው ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ያሳካቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም የግብርና ዘርፉ አሁን በደረሰበት እና በቀጣይ ሊሠራ ከታሰበው ጉዳዮች ጋር የማይሄድ በመሆኑ አዲስ ፖሊሲ ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ ሆኗል ነው ያሉት፡፡

አዲሱ ፖሊሲ ቀደም ካለው ፖሊሲ ጋር ሲነጻጸር አዳዲስ ዕይታዎችን የያዘና በቀጣይ በግብርናው ዘርፍ ሊደርስ የሚችልበትን ደረጃ ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም ፖሊሲው ወደ ገጠር ወርዶ ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ አቅምን የሚጨምር መሆኑ የሚጠቀስ ነው ይላሉ፡፡

ፖሊሲው አሁን ካሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር አብሮ የሚሰራ ሆኖ አርሶ አደሩ አካታች የሆነ የፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርገው ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል አዲሱ ፖሊሲ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን በአኗኗር ዘይቤያቸው ላይ የተመሰረተ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ሌሎች ድጋፎችንም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ከዛም ባለፈ ግብርናው ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ይገልጻሉ።

ፖሊሲው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያበሰሩትን የገጠር ኮሪደር ልማትና የገጠር ከተማ ማዕከላት የኤሌክትሪክ ፣ የሎጀስቲክ መሠረተ ልማት ተደራሽነትን አስቀድሞ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You