“መንግሥት በቻለው መጠን በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያ ባንኮችን ለማጠናከር ጥረት አድርጓል” የሲዳማ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሐጢያ

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ለመተግበር የተለያዩ ሕጎች እና አዋጆች እየፀደቁ፤ ማሻሻያውን ከአንድ ወደ ሁለት በማሳደግ እየተተገበረ እና ውጤት እየተገኘበት ነው። በዚህ ላይ የባንኮች ሚና አንደኛው ሲሆን፤ ባንኮች እና የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ የሲዳማ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሐጢያን አነጋግረናል። ከባንኩ እንቅስቃሴ ጀምረን ሀገር በቀል ኦኮኖሚው እና ባንኮች መካከል ያለውን ግንኙነት ከዚሁ ጋር ተያይዞ ገበያ መር የውጪ ምንዛሪን እና ሌሎች ጥያቄዎችን አካተን ያካሔድነውን ቃለመጠይቅ በዚህ መልኩ አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- የሲዳማ ባንክ እንቅስቃሴ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታው ምን ይመስላል?

አቶ ታደሰ፡– እንቅስቃሴውን እንቃኝ ስንል በጣም ሰፊ ነው። ነገር ግን ጠቅለል ባለ መልኩ በሁለት መንገድ ውስጣዊ እና ውጫዊ በሚል ከፋፍለን ማየት እንችላለን። በሀገር ውስጥ ከደንበኞች በቁጠባ እና በተንቀሳቃሽ መልክ ገንዘብ እንሰበስባለን፤ የደንበኛ አገልግሎት ሥራዎችን እንሠራለን። ከብድር አንፃር ደግሞ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ብድር እየሠጠን እንገኛለን። የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት ላይም እንሰማራለን።

የውጪ ግንኙነትን በተመለከተ ስድስት ከሚሆኑ የውጪ ሀገር ባንኮች ጋር ግንኙነት አለን። አዲስ እንደመሆናችን መጠን ከስድስት አላለፍንም። ከገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋርም ግንኙነት አለን። በሀገር ውስጥ ካሉ 31 ባንኮች ጋር በአር ቲ ጂ ኤ ሲስተም እርስ በእርስ ተገናኝተን እንሠራለን። ሀገራችን ከምትከተለው ዲጂታላይዜሽን ሲስተም አንፃር ባንኩን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ስላሰብን በቶሎ ወደ ቴክኖሎጂ ገብተናል። ስለዚህ ኤቲ ኤም እና ከባንክ ወደ ባንክ ማዘዋወር እንዲሁም ከቴሌ ጋር ግንኙነት ፈጥረን እየሠራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሲዳማ ባንክ በሐዋሳ ለቤት ገንቢዎች ያዘጋጀው ብድር ነበር። ምን ላይ ደረሰ?

አቶ ታደሰ፡- የክልሉ መንግሥት በሁለት መልኩ ቤት እንዲገነባ ፈቅዶ ነበር። አንደኛው በማህበር ተደራጅተው ይመጣሉ። ቆጥበው ያስቀምጣሉ፤በተጨማሪ በጋራ መኖሪያ ቤት መልክ የሚቆጥቡም አሉ። እኛ ለሁለቱም የገንዘብ አቅርቦት እንሠጣለን። የክልሉ የማህበራት ማደራጃ ቢሮ ያደራጅና በባንኩ የሒሳብ ቁጥር እንዲከፈት ያደርጋል። የተጠየቁት 50 በመቶ ሲሞላ የከተማ አስተዳደሩ ለእያንዳንዳቸው መሬት ይሠጣቸዋል። እነሱ ዲዛይን አውጥተው ቤቱን የሚገነቡበትን ሁኔታ በሚመለከት ሂደቱን ጨርሰው ሲያጠናቅቁ ወደ ባንካችን ይመጣሉ። እኛ ደግሞ ግንባታውን ማጠናቀቂያ ብድር እንሰጣቸዋለን።

የጋራ መኖሪያ ቤቱን በተመለከተም ባንኩ ለከተማ አስተዳደሩ ብድር ይሰጣል። የከተማ አስተዳደሩ ብድር ይወስድና የጋራ መኖሪያ ቤት ይገነባል። በዕጣ ለሚያስተላልፍላቸው ሲያስተላልፍ እኛ ደግሞ ብድር ለገዢዎቹ እንሰጣለን። ገዢዎቹ ዕዳውን ሲከፍሉ የከተማ አስተዳደሩ ብድር ይዘጋል ማለት ነው። በሁሉም ሞዳሊቲ ባለፈው ወደ 35 ማህበራት መሬት ወስደው የቤት ዲዛይን እየጨረሱ ነው። እርሱ ብቻ አይደለም፤ ከዋጋ ንረት አንፃር መጀመሪያ የተገመተው እና አሁን ያለው እኩል አይደለም። ስለዚህ መቆጠብ አለባችሁ እየተባሉ ስለሆነ አሁን ላይ መቆጠብ ጀምረዋል። ያንን ጨርሰው ሲመጡ እኛ ደግሞ የብድር ሁኔታን እናመቻቻለን።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ካፒታላችሁ ምን ያህል ነው?

አቶ ታደሰ፡- ካፒታል የሚገለፀው በብዙ መልኩ ነው። መጠባበቂያ ካፒታል‹ ጠቅላላ ካፒታል የሚባሉ አሉ። ጠቅላላ ካፒታል ከተባለ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ነው። ሃብታችን ደግሞ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን አካባቢ ነው። ሃብት የሚባለው የደንበኞች ቁጠባ የተሠሩ ቁጥሮች ይደመራሉ። የባንኩ ቋሚ ሃብቶችም አሉ። እነዛ ሁሉ ተደማምረው ነው። ያበደርነው ደግሞ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ነው። ስለዚህ የሚለካው ሃብታችን ተደርቦ ነው ።

አዲስ ዘመን፡- ተግባራዊ የተደረገው ገበያ መር የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለባንኮች ያለው ጥቅም እና ጉዳትን በተመለከተ ቢያብራሩልን ?

አቶ ታደሰ፡- ገበያ መር የሆነ የውጪ ምንዛሪ ተመን በጣም ትልቅ ዕምርታን ያሳየ ነው። እኛ እንደውም አዲስ ባንክ በመሆናችን ብዙ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት ጠቅሞናል። የውጪ ምንዛሪ ግኝታችን ከ60 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል። ምክንያቱም ወደ ውጪ የሚልኩ ባለሃብቶች ያገኙትን ዶላር መጠቀም እና ማስቀመጥ ይፈልጋሉ። ከዛ አንፃር የተለያዩ ደንበኞች የውጪ ምንዛሪ ባንክ ሲያስቀምጡ በአንድም በሌላም መንገድ ሌሎች ዶላሩን የሚያገኙበት ዕድል ይኖራል።

ሌላው ደንበኞች ያመጡትን የውጪ ምንዛሪ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተስማምተው ለባንክ መሸጥ እና ከባንክ መግዛት ይችላሉ። አንድ ለአንድ መደራደር ባይቻልም፤ የዕለቱን የመግዣ እና የመሸጫ ምንዛሪያችንን ይፋ እናደርጋለን። የውጪ ሀገር ገንዘብ ያላቸው ደንበኞች በመረጡት ባንክ ሔደው ይሸጣሉ። ይህ ለእኛም ጠቅሞናል።

ውጪ ያሉ ዘመዶቻችንም ገንዘብ በዛ መልኩ እያስተላለፉ ነው። የእኛ ገንዘብ አስተላላፊ ወኪሎች (ኤጀንቶች) ግን ውስን ናቸው። ይቀረናል እንጂ የመንግሥት አካሔድ በጣም እየረዳን ነው። ያለንን የውጪ ሀገር ገንዘብ ስልክ እየደወልን ‹‹ከውጪ የምታስገቡት ነገር ካለ መጥታችሁ መውሰድ ትችላላችሁ፡፡›› እያልን እስከ መደወል ደርሰናል። ስለዚህ ለእኛም ለተገልጋዩም ትልቅ ለውጥ አለ።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ አሁን ላይ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ በሙሉ እያገኘ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ታደሰ፡- መንግሥት የውጪ ምንዛሪን ፈሰስ አድርጓል። ይህ የውጪ ምንዛሪው ገበያ መር ሲሆን፤ የተለያዩ ባንኮች እንዲገዙ ለማገዝ የተለቀቀ ነው። ወደ ውጪ የሚላከው እና ከውጪ ሀገር የሚላከውም ገንዘብ ስለጨመረ ማግኘት እየተቻለ ነው። በባንክ በኩል የውጪ ምንዛሪውን ይዞ መቆየት አክሳሪ ነው። ምክንያቱም ባንኩ ራሱ ትርፍ የሚያገኘው ደንበኞች ባለው ገንዘብ ሲጠቀሙ ነው። ለምሳሌ ሊዝ ሲከፈል የሚከፈሉ ክፍያዎች አሉ። የአገልግሎት ክፍያዎች ለባንኩ እንደገቢ ናቸው። አስር ሚሊዮን ዶላር አካውንቴ ውስጥ አለ ከማለት ይልቅ አንድ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ተቀምጦ፤ ሌላው ለገበያ ቢውል ይሻላል።

የሀገር ውስጥ ገንዘብም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። በቢሊዮን ቁጥር የገባ ብር መንቀሳቀስ አለበት። አዲሱ ፖሊሲ ብዙ የውጭ ምንዛሪ እንዲገባ አድርጓል። በተመሳሳይ መልኩ ለደንበኞች ለመስጠትም ጥሩ ዕድል ፈጥሯል። ከዚህ በፊት የውጪ ምንዛሪ እጥረት አለ ስለሚባል አንዳንድ ባንኮች አካባቢ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተፈጠረ ነው ይባል ነበር። አስር ሰው ጠይቆ ለአንዱ ብቻ ሲሰጥ የመልካም አስተዳደር ችግር የመፈጠር ዕድሉ የሰፋ ነው። አሁን ግን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ስለሌለ ችግሩን ማስወገድ ችለናል ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ባንኮች ገንዘብ የሚሰበስቡት ከብዙ ሕዝብ ቢሆንም፤ የሚያበድሩት ለጥቂት ሰዎች ነው። በተለይ ድሃውን እየጠቀሙት አለመሆኑ ይታወቃል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ታደሰ፡- በእርግጥ የቆጣቢ እና የተበዳሪ ቁጥር ሙሉ ለሙሉ አይገናኝም። ምናልባትም አንድ ሰው በአራት እና በአምስት ባንኮች በተለያየ የሒሳብ ቁጥር ሊቆጥብ ይችላል። ያ ሁሉ ሲቆጠር የሁሉም ባንኮች ተደማምሮ የቆጣቢ ቁጥር ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከባንኮች 93 ሺህ አካባቢ ብቻ ተበዳሪ አለ። ያን ያህል ሕዝብ ቆጥቦ ጥቂቱ ይወስዳል። በእርግጥ ገንዘቡ ተሰብስቦ የሚሰጠው ለጥቂቶች ነው።

ሲዳማ ባንክ አነሳሱ አነስተኛ የቁጠባ እና ብድር ተቋም ሆኖ የተቋቋመ ነው። ስለዚህ የቀረፅነው መንገድም ያንኑ ተከትሎ የሚሄድ ነው። ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው መሠረት አንድ ባንክ የካፒታሉን 25 በመቶ ድረስ ማበደር ይችላል። እኛ ግን ያደረግነው ጥቂቶች ብቻ ወስደው እንዳይጨርሱ የምናበድረው አስራ አምስት በመቶ ብቻ ነው። ያ ያለችውን ሃብት ለብዙዎች እንድትከፋፈል ይጠቅመናል። ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተር ፕራይዞች ራሱን የቻለ የባንኩ ዲፓርትመንት አለ። በዚህ ዲፓርትመንት ወደ አምስት መቶ ሚሊዮን ብር ትንንሽ ብድሮች ይሰጣል። ባለፈው ዓመት ለጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ስናበድር ነበር፡፡

እንግዲህ ድህነት በንፅፅር ነው። አንድ ሚሊዮንም፤ አምስት ሚሊዮንም የሚበደር አለ። እኛ ከአንድ ሚሊዮን ብር በታችም እናበድራለን። የትኛውም ባንክ ሃምሳ ሺህ እና መቶ ሺህ አያበድርም። እኛ ግን እናበድራለን። ነገር ግን ባንኮች አነስተኛ ብድር የማይሰጡት ለምንድን ነው? የሚለውንም ማወቅ ያስፈልጋል። ምናልባት የአሁኑን ዲጂታል ሥራ ላይ በማዋል ለብዙሃን ብድር መስጠት ይቻላል። ነገር ግን አሁንም ማግኘት የሚችሉት ዘመናዊዎቹ ዲጂታሉን የሚጠቀሙት ብቻ ናቸው፡፡

ባንኮች ብድር የማይሰጡት ለምንድን ነው ተብሎ ሲጠየቅ፤ መልሱ ተበዳሪው አንድ ጊዜ ብድር ከወሰደ፤ የታወቀ እና መገኘት የሚችል መሆን አለበት። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን አንድ ጊዜ ከተበደረ በኋላ ማግኘት አይቻልም። እኛ እያበደርን ያለነው የሕዝብን ገንዘብ ነው። አንዱ ያስቀመጠውን ለሌላ ስናበድር፤ የግድ በሌላ ጊዜ ብር ያስቀመጠው ሰው ገንዘቡን ሲጠይቅ ማግኘት አለበት። ተበድሮ የሚጠፋ ከሆነ ያንን መመለስ አይቻልም። ስለዚህ ብድር ስንሰጥ ብሩ እንደሚመለስ እርግጠኛ መሆን አለብን።

መንግሥት በቅርቡ እየዘረጋ ያለው የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት ለባንኮች በጣም ትልቅ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሥርዓት ነው። ምክንያቱም ዲጂታል መታወቂያ ከተለመደ የትም ቦታ ቁጥር ሲገባ ግለሰቡ ማን እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በኋላ ሕግ ሆኖ ሲወጣ ዲጂታል መታወቂያ የሌለው ሰው መበደር አይችልም ይባላል። የትም ቦታ ሔዶ መታወቂያ ማውጣት አይችልም። ስም ቀይሬ መታወቂያ አወጣለሁ ቢል አሻራ ይይዘዋል። በዛ ጊዜ ተበዳሪን ማግኘት ይቻላል።

እስከዛም ቢሆን እኛ የድሃውን ማህበረሰብ ለማገዝ ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብረን እንሰራለን። ሴቶችን የምንደግፍበት ሁኔታ አለ። ከድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች ጋር እንሰራለን። ለድሃው ማህበረሰብ ተመጣጣኝ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የተቻለንን እናደርጋለን። 100 ሚሊዮን ብር ለአንድ ግለሰብ አናበድርም፤ የምናበድረው አነስተኛ ብድሮችን ነው። ይህ የብድር አቅርቦትን ለማዳረስ በሚል የመጣ ሃሳብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተስ ምን ይላሉ?

አቶ ታደሰ፡- ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በማየት እኛ ደግሞ ከዛ ላይ ቆርሰን የምንፈልገው ምንድን ነው? በሚል እያየን ነው። እያንዳንዱ ዘርፍ የየራሱን ቆርሶ ይወስዳል። የፋይናንስ ዘርፉ የሌማት ትሩፋቶች ላይ ለምሳሌ የአሳ ሃብት፣ የዶሮ እርባታ ላይ በቡድን እየተደራጁ አንዱ ለሌላው ዋስ እንዲሆን በማድረግ ብድር እየሰጠን ነው። ሌላኛው ደግሞ ወጣቶችን የሚያደራጁ ፅህፈት ቤቶች አሉ። እነርሱ ለተደራጁት ኃላፊነት ይሰጡዋቸዋል፤ ይከታተሉዋቸዋል። ሙያዊ ድጋፍ ይሰጧቸዋል። ለእነርሱ የፋይናንሺያል አቅርቦት አለን።

በባንኩ በኩል ለወጣቶች የማማከር ሥራም ይሠራል። ለምሳሌ የፋይናንስ ኦፕሬሽን ዲፓርትመንት ውስጥ ያሉ ባለሙያዎቻችን ሙያዊ ድጋፍ ይሰጧቸዋል። ሀገር በቀል ኢኮኖሚው የሚያበረታታው የፈጠራ ባለሙያዎችን ነው። ጥገኛ ሆነን ብቻ ሳይሆን ራሳችን ፈጥረን መስራት እንችላለን። ስለዚህ በዚህ መልኩ ድጋፍ እያደረግን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ወደፊት የውጪ ባንኮች እንደሚገቡ እየተነገረ ነው። የሀገር ውስጥ ባንኮች ምን ያህል አቅም አላችሁ? ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል?

አቶ ታደሰ፡- ለረዥም ጊዜ ኢትዮጵያ ለውጪ ባንኮች በሯን ዝግ አድርጋ ኖራለች። በዓለም ደረጃ ተገዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከተፈለገ የግድ የዓለም ማህበረሰብን ሳያቅፉ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ተዘጋጅቻለሁ እያለ ነው። ደግሞም ብዙ የማሻሻያ ሥራዎች ተሠርተዋል። ባንኮች እንዲጠናከሩ ተደርጓል። ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ሥራዎች ተሠርተዋል። ነገር ግን ከደርግ መንግሥት በኋላ የመጀመሪያው የግል ባንክ አዋሽ ባንክ መነሻው 25 ሚሊዮን ብቻ ነበር። አሁን ግን ካፒታሉ በቢሊዮን የሚቆጠር ነው። ልክ እንደአዋሽ ሁሉ መንግሥት በተቻለው መንገድ የግል ባንኮችን እያጠናከረ ነው።

አንድ ባንክ ተወዳዳሪ መሆን የሚችለው በካፒታሉ እና በቴክኖሎጂ ነው። የእኛን ጨምሮ ባንኮች ቴክኖሎጂ መር ሥራ እየሠሩ ነው። ይህ ማለት ግን ሲመጡ መቋቋም ይችላሉ ማለት አይደለም። ስለዚህ መጣመር ያስፈልጋል። መጣመር ሲባል መተባበር ነው። ከሌላው ጋር ተባብሮ መሥራት ማለት ነው። ምናልባት አንዳንዴ በተቃራኒው የሚወራው የእኔነት ስሜት የሚባል ነገር አለ። ነገር ግን እውነታውን ማወቅ ያስፈልጋል። ምንጊዜም ቢሆን ባለገንዘቡ የሚፈልገው ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበትን ባንክ ነው። ከዛ ውጪ የሚወራውን ወሬ አይፈልግም።

ባለድርሻው የኔ ባንክ የሚለው ለእርሱ ጥሩ ትርፍ የሚያመጣለትን ነው። ሲዳማ ባንክ ትልቅ ትርፍ ማግኘት ባይችልና ከሌላ ባንክ ጋር ተባብሮ ከፍተኛ ገንዘብ ቢያገኝ የአክሲኦን ድርሻ ባለቤቱ ከፍተኛ ትርፉ ያስደስተዋል። ደንበኛ 100 ሺህ ድርሻ ገዝቶ ምን ያህል ትርፍ እንደሚያገኝ ያስባል እንጂ ሌላ ምንም አያስብም። አንዳንድ ሰዎች ግን ጉዳዩን በግድ ፖለቲካ ለማድረግ ይሞክራሉ።

ባንኩን ማጠናከር እና ተወዳዳሪ ማድረግን በተመለከተ በእኛ በኩል የአምስት እና የአስር ዓመት ስትራቴጂ ቀርፀን ጨርሰናል። አማራጮችን አስቀምጠናል። አንደኛው ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ካፒታላችንን ከአምስት ቢሊዮን በላይ ማድረስ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አምስት ቢሊዮን ብቻ ሆኖም ላንቀጥል እንችላለን፤ ምክንያቱም ትሬዠሪው አምስት ቢሊዮን ብር ወደ ዶላር ሲቀየር በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህ የውጪ ባንኮች እንዳያሸንፉን ከሌላ ባንክ ጋር ልንተባበርም እንችላለን። የግድ ከሌላው ጋር መተባበር ሊገባ ይችላል። ከእኛም ያነሰ ሊመጣ ይችላል። በራሳችን ውስጥ እናካትተዋለን።

እኛ እንደሙያተኛ ለባለድርሻው ጥቅም የሚያመጡ ነገሮች ላይ ጠንክረን እንሠራለን። የባንኩን ካፒታል እና ትርፍ በማሳደግ የሰለጠነ የሰው ኃይልን በመጠቀም በጣም ምርጥ ቴክኖሎጂን ሥራ ላይ በማዋል ባንኩን ለማሳደግ ጥረት እያደረግን ነው። ቴክኖጂውን የበለጠ በጥራት እና በስፋት ለመጠቀም በቅርብ ጊዜም ጨረታ ወጥቷል። ስለዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል በመጠቀም ለውጡን ለመቀበል ጥረት እያደረግን ነው። መንግሥት ደግሞ በቻለው አቅም ባንኮችን መደገፉ የሚካድ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ባንኮች አካባቢ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ታደሰ፡– መንግሥት በቻለው ሁሉ በተለያየ መልኩ የኢትዮጵያ ባንኮችን ለማጠናከር ጥረት እያደረገ ነው። ለምሳሌ የውጪ ምንዛሪን ለባንኮቹ ሰጥቷል። ይህ ራሱ ቀላል ድጋፍ አይደለም። ሌላው የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ነው። ለምሳሌ ውልና ማስረጃ የሰጠውን ውክልና በቀላሉ በቴክኖሎጂ ማረጋገጥ የምንችልበት ሲስተም ተዘርግቷል። ይሔ ቀላል አይደለም። የእኛ ደንበኛ የመንግሥትን ግብር በቀጥታ በእኛ ባንክ በኩል ይከፍላል። ይህ ለእኛ ትልቅ ድጋፍ ነው። ነገር ግን እንደተግዳሮት ሆነው የሚነሱት አንዳንድ ጊዜ መንግሥት ሳይፈልግ ፈተና ሆነው የሚመጡ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ የፀጥታ ችግር መንግሥት ፈልጎት የሚመጣ አይደለም። ባንክ በራሱ በጣም ጥንቃቄ እና ጥበቃን የሚሻ ተቋም ነው። ያገኘውን ገንዘብ እንዴት ላስጠብቅ ማለት ብቻ ሳይሆን እንዴት ላሳድግ እያለ ሲያስብ፤ የፀጥታ ችግሮች ከባድ ፈተና ይፈጥራሉ።

ሌላው የውጪ ዜጋ የሲዳማ ባንክን ድርሻ (ሼር) መግዛት እንዲችል ተፈቅዶለታል። ነገር ግን የፀጥታ ችግር ካለ አይተማመንም። መንግሥት የሚሰራው በተለይ የሀገር ግንባታ ላይ ማተኮሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ፀጥታው ላይ ያለው ችግር መፈታት አለበት። ሌላው የውጭ ምንዛሪ ላይ ሰዎች እያመጡ ያሉበት ሁኔታን የበለጠ ማሳደግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ትንንሽ አንድ መቶ ወይም ሁለት መቶ ዶላር ሊልኩ ይችላሉ። ያ ወደ ሆነ የኢንቨስትመንት ደረጃ እንዲመጣ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራት አለበት። ለምሳሌ አሁን ይፋ የተደረገው ዩናይትድ ኦፍ ኢቲ የሚለው ብዙ ዳያስፖራዎች እዛው ሆነው የአካውንት ቁጥር ከፍተዋል። በቪዲዮ በፎቶ እዛው ሆነው መረጃቸውን ይልካሉ። በኤሌክትሮኒክስ ይፈርማሉ። ስለዚህ ስርዓቱ ስለተዘረጋ ወዲያውን ብር መላክ ይችላሉ። ገንዘብ ማስቀመጥም ይችላሉ፤ እዚህ ላይ ከፍተኛ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራት አለበት።

አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ንረት ባንኮች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?

አቶ ታደሰ፡– ፈተና ተብለው ከሚጠሩ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የዋጋ ንረት ነው። የገንዘብ የመግዛት አቅም ማነስ ነው። የዋጋ ንረት ሲኖር ቆጣቢዎች ያስቀመጡትን ገንዘብ በብዛት የሚያወጡበት ሁኔታ አለ። ዛሬ በስንት መከራ የተቀመጠ ገንዘብ ይወጣል። ምክንያቱም ደንበኛው ለሚያወጣው ወጪ ገንዘቡ አይበቃም። በእኔ እምነት ለዚህ ትልቁ መፍትሔ አቅርቦትን ማስፋት ነው። የሚፈለገው ነገር በገፍ ከተገኘ ዋጋ መቀነሱ አይቀርም። ለምሳሌ የቻይና ኢኮኖሚ በምዕራቡ ዓለም ሳይቀር ፈተና የሆነው አቅርቦት ስላበዙ ነው። በቻይና በጣም ብዙ ፋብሪካዎች ያመርታ። ቻይናዎች በጣም አቅርቦት ላይ በስፋት ይሠራሉ። አውሮፓዎች ደግሞ በጥራት ጥቂት ምርት ያመርታሉ። ስለዚህ እኛም በግብርና በኢንዱስትሪው አቅርቦቱን ማብዛት ያስፈልገናል። አቅርቦት ከበዛ ባንኮችም ገንዘብ መሰብሰብ ይችላሉ።

በእርግጥ የዋጋ ንረትም ቢኖር ገንዘቡም ወጥቶ ወደ ባንክ ሊገባ ይችላል። ነገር ግን አንዳንዴ አይገባም። ብሔራዊ ባንክ የሚያውቀው ገንዘብ እና በአጠቃላይ ያለው ገንዘብ የተለያየ ነው። ማለትም ብሔራዊ ባንክ አትሞ ያወጣው ብር ባንኮች ውስጥ የለም። አንዳንዴ ባንኮች አካባቢ ያለው እጥረት ባንክ ሔጄ ላላገኝ እችላለሁ በሚል ስጋት ሰዎች ብራቸውን ወደ ባንክ ላያስገቡ ይችላሉ። ከዚህ በላይ ማውጣት አይቻልም ሲባል ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ ማስቀመጥ ይቀንሳሉ። ስለዚህ የሚሻለው መልቀቅ ነው። ሰዎች ባንኮች ላይ እንዲተማመኑ መሥራት ያስፈልጋል። አንድ ሚሊዮን ሁለት ሚሊዮን ማውጣት ከቻሉ ለማስገባት አይጨነቅም።

በሌላ በኩል ምርታማነት ላይ በደንብ ከተሠራ አቅርቦቱ ሲጨምር የዋጋ ግሽበትን መቀጣጠር ይቻላል። በዛ ላይ መንግሥት አሁን ጥሩ እየሔደ ነው። አሁን እየተቀመጠ ያለው ፖሊሲ ጥሩ እየተሠራበት ጥሩ ውጤት እያስገኘ ነው። አንዳንዴ ባንኮች ቢዝነሱ ከሚያስፈልገው በላይ ገንዘብ የመልቀቅ ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ዋስትና በማየት ብቻ ሲለቁ፤ ችግር ነው። ስለዚህ የሚለቁት ብድር እንዲወሰን በማድረግ ራሱ የራሱ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል። እንዲህ ሲወሰን ትንንሽ ብሮች ይወጣሉ። ትልልቅ ብድሮች ሲሰጡ ተጠቃሚዎቹ የተወሰኑ ብቻ ናቸው። አነስተኛ ብድሮች ሲሰጡ ግን ብዙ ሰው ጋር ይዳረሳል። ብዙዎች ያመርታሉ። የማምረት አቅም ሲጨምር ደግሞ ምርታማነት ይጨምራል።

አዲስ ዘመን፡- ባንኮች በጨረታ ላይ ተስማምተው የሚገቡበት እና አሻጥር የሚሰራበት ሁኔታ ስለመኖሩ ይነገራል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ታደሰ፡– በፊት ነበር አሁን ግን ጨረታ የለም። አሁን ባንኮች በጠዋት የውጪ ምንዛሪ ባንኩ የሚሸጥበትን እና የሚገዛበትን መጠን ወስነው በየራሳቸው ይፋ ያደርጋል። እያንዳንዱን የማነጋገር ሁኔታ የለም። ነገር ግን አንድ ዶላር ያለው ሰው ለመሸጥ ብዙ ዶላር ይዞ ከመጣ መስማማት እንዲቻል ዕድሉ አለ። ይህ ሌላ ቦታ እንዳይሔድ ነው፤ ሌላ ነገር የለውም። 100 ዶላር ከሚያመጣ ሰው ጋር ግን ድርድር ውስጥ አይገባም። ነገር ግን አንድ እና ሁለት ሚሊዮን የውጪ ምንዛሪ አመጣለሁ ወስንልኝ የሚል ከመጣ በመወሰን እዚሁ እንዲመነዝር ይደረጋል። ከዛ ውጪ ባንኮች አሁን ላይ ደፍረው እርስ በእርስ የሚደራደሩበት ሁኔታ የለም። ነገር ግን አንዱ ባንክ ለሌላው ባንክ የሚሸጥበት ዕድል ተፈቅዷል።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ዕድሉን እንስጥዎት?

አቶ ታደሰ፡- አዎ! በመንግሥት ደረጃ እየተቀረፁ እና እየተተገበሩ ያሉ የልማት ፕሮግራሞች ለእኛ ትልቅ መነቃቂያ የፈጠሩ ናቸው። በተለይ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ውስጥ ራሳችንን ጠለቅ አድርገን ስናይ የተደረገው የለውጥ አካሔድ ብዙ አቅሞችን እያወጣ የመጣ ከመሆኑ አንፃር በጣም ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ ነው። ሌላው ተቋማት የማስፈፀም አቅማቸው በቴክኖሎጂም ሆነ በሰው ኃይል እንዲያድግ እየተደረገ መሆኑ፤ ለእኛ ትልቅ አቅም ሆኖናል። ምክንያቱም አገልግሎቶች ግልፅ እና ውጤታማ እየሆኑ ነው። አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች ከተሞች ላይ የሚገጥሙን ችግሮች እየተቃለሉ ናቸው። ነገር ግን ይኸው በጣም በተሻሻለ መልኩ መቀጠል አለበት፡፡

ሌላው ከውጪ ምንዛሪ ጋር ያለው ሁኔታ መንግሥት አጠናክሮ ቢቀጥል የበለጠ አደጋ እንዳይመጣ ቶሎ ለመከላከል ያግዛል። አደጋ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ቀድሞ መከላከል ግድ ይላል። ምናልባት ኑሮ ውድነቱን የውጪ ምንዛሪው ገበያ መር መሆኑን ተከትሎ የመጣ ለማስመሰል የሚደረገው ሙከራ ሐሰት ነው። እንደውም አቅርቦቱ እየጨመረ ስላለ ለምሳሌ ፒኤልሲ ሲከፈቱ የነበሩ ክፍያዎች በመግዣና በመሸጫ ልዩነት እንድንወስድ ስለተደረገ ባንኮች የሚጭኑት የአገልግሎት ክፍያ በጣም ትንሽ ሆኗል። እየመጡ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የውጪ ባንኮች መግባትን ጨምሮ የምናየው በመልካም ነው። አቅምን ያጠናክራል። እንቅልፍ እንቅልፍ ያለንን እንድንነቃ ያደርገናል። ስለዚህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ባይ ነኝ። በተረፈ ፈጣሪ ሀገራችንን ይባርክ።

አዲስ ዘመን፡- አሜን ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ እናመሰግናለን፡፡

አቶ ታደሰ፡- እኔም በጣም አመሠግናለሁ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You