አዲስ አበባ፡- የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ባለሁለት ፎቅ ሕንጻ ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት አስገንብቶ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር እንደሚውል ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ፡፡
በቤተ መፅሐፉ በምርቃ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንደገለጹት፤ ከዚህ በፊት የነበረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የቦታ ጥበት ነበረበት።አሁን የተገነባው ዘመናዊ ሕንጻ በቂ የምርምር መሳሪያዎችን ለማስቀመጥና ለመጠቀም ያስችላል።
ለትምህርት ጥራት መጠበቅ የምርምር ግብዓቶች ወሳኝ ሚና አላቸው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለትምህርት ግብዓት መሟላት መንግሥት የአቅም ውስንነት ስለሚኖርበት በባለሀብቶች መደገፉ አቅሙን ያጠናክረዋል ብለዋል።
የተመረቀው የቤተ መጻሕፍት ሕንጻ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ወግና ባህል ምርምር የሚደረግበት ይሆናል ካሉ በኋላ፤ ሌሎች ባለሀብቶችም በእንዲህ አይነት አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ በቅርቡ የድምጽ ሲስተም እንደሚደረግለት ገልፀው፤ በአገሪቱ ውስጥ የሚታተሙ የህትመት ውጤቶች በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ እንደታሪክ ተሰንደው ይቀመጣሉ ብለዋል። ለምርምር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድርሻ መሆኑን አመልክተው፤ የበፊቱን በማስቀመጥ ከመስራት ባሻገር እስካሁን ሲያገለግል የነበረው የጥናትና ምርምር ተቋም ሙሉ በሙሉ ሙዚየም እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ባለቤት በሼህ አላህ ሙህዲን ስም የተሰየመው ሕንጻ 116 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ በስድስት ሺህ 260 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የተገነባ ነው።ሕንጻው 250 መቀመጫዎችን የያዘ የስብሰባ አዳራሽ እና 365 የመጻሕፍት መደርደሪያዎች ያሉት ሲሆን፤ የእሳት ማጥፊያን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች ተገጥመውለታል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
ዋለልኝ አየለ