
ልዩ የሀገር ፍቅር፤ ከውስጥ የማይወጣ ቁጭት፣ በየትኛውም መልኩ በየትኛውም ጊዜ ሀገርን የማገልገል ፍላጎት፤ በሀገራቸው አሻራቸውን የማኖር ሕልም አላቸው። ሀገርን የሚቀይረው ሳይንስ ነው፤ ሳይንስን በሚገባው ልክ ማስተማር፣ ሳይንቲስቶችን ማብቃት ጊዜው የሚጠይቀው ነው። ስለዚህ የሳይንስ ትምህርት መሬት መንካት አለበት የሚል ጽኑ እምነት አላቸው። ስለሳይንስ አንስተው አይጠግቡም። ተናግረው አያቆሙም ብቻ የሳይንስን አስፈላጊነቱንና ውጤት እየዘረዘሩ ያስረዳሉ።
ዓለምን የቀየረው ሳይንስ ነው። አንድ ሀገር ወደ ቴክኖሎጂ ማማ የሚወጣው እውነተኛ ሳይንስ በሀገር ውስጥ እውቀት ሲሰፋ ብቻ ነው። አሁን ለሀገራችን እድገት የሚያስፈልጋት ሳይንስ እና ምርምር ነው። ስለዚህ ለሳይንስ ትምህርት ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት የሚል የጸና አቋም አላቸው። የሳይንስ እውቀትን ወደ መሬት ማውረድ በሀገራችን ብዙ ሳይንቲስቶችን ማፍራት ጊዜው የሚጠይቀው ነው። ሳይንቲስቶችን ማፍራት የሚቻለው ዘርፉን በደንብ ማወቅና መማር እና መመራመር የሚችል ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው የሚሉት የልጅ ኤልያስ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ (አሳኮ) መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ልጅ ኤልያስ ጥላሁን ደበላ ናቸው።
ልጅ ኤልያስ በአሜሪካ ሀገር «ልጅ ኤልያስ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ» (አሳኮ) መስርተዋል። በኢትዮጵያ በተመሳሳይ ቅርንጫፍ ኮሌጅ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ናቸው። «ሀገራችንን መቀየር ያለብን እኛ ነን፤ እኛ ደግሞ የእውቀታችንን መስራት አለብን» ይላሉ። ልጅ ኤልያስ ያላቸው የትምህርት ዝግጅት፤ የሥራ ልምድ እንዲሁም ለሀገራቸው ያላቸው ትጋት እና በቀጣይ ሊሰሩ ያሰቡት ዕቅድ የዛሬው «የሕይወት ገጽታ» ዓምድ እንግዳችን እንዲሆኑ አብቅቷቸዋል።
ቃለመጠይቁን አቶ ኤልያስ እያልኩ ልቀጥል ወይስ ልጅ ኤልያስ ልበል የሚለው የመጀመሪያ የመግቢያና የመግባቢያ ጥያቄዬ ነበር። ልጅ ኤልያስ ፈገግ ኮራ የሚል ስሜት ይታይባቸዋል። «ልጅ » ማለት የክብር ስም ነው ሲሉ ቀጠሉ። «በኢትዮጵያ ከነበሩንና ከተወሰዱብን አንዱ የክብር መጠሪያዎቻችን ናቸው። ይሄንን ማስመለስ አለብን ብዬ አምናለሁ። ‹‹ልጅ›› የሚለው ‹‹አቶ›› ከሚለው ማሕበራዊ ማዕረግ በላይ ክብር ያለው ነው። ስለዚህ ራሴን ልጅ ኤልያስ ብዬ ነው የምጠራው። ሰዎችም አቶ ኤልያስ ከሚሉኝ ይልቅ ልጅ ኤልያስ ብለው በኢትዮጵያ የክብር ማዕረግ ሲጠሩኝ እንዳከበሩኝ ይሰማኛል» አሉ በዚሁ ሀሳብ ተስማምቼ ቆይታችንን ልጅ ኤልያስ በሚለው አስቀጥያለሁ። መልካም ንባብ።
ትውልድና እድገት
ልጅ ኤልያስ ጥላሁን ተወልደው ያደጉት ብዙዎች ሀብት ባፈሩበት ‹‹አንተ ማነህ? ከየት ነህ?›› በማይባልበት፤ ሥራ ክቡር በሆነበት፤ ደሀ ጦሙን በማያድርበት አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ነው። ‹‹መርካቶ ገብቶ ምን ጠፍቶ›› ከሰው ነፍስ በስተቀር ይፈበረካል፤ ይሸጣል፤ ይለወጣል። እርሳቸውም ጎተራው ገበያው በእህል ጢም ባለበት፤ ሰርግና ሰርገኛ በሚደራበት ጥር ወር 1963 ዓ.ም ነው ይህችን ዓለም የተቀላቀሉት።
የቤተሰባቸው ድምቀት የሆኑት ልጅ ኤልያስ ለአቅመ ትምህርት ሲደርሱም ቅድመ መደበኛ ትምህርት የጀመሩት መሳለሚያ ኳስ ሜዳ ማዞሪያ አካባቢ ነበር። እንደማንኛውም የከተማ ልጅ ትምህርታቸውን ሀሁ.. ያሉት የቄስ ትምህርት በሚያስተምሩት የኔታ ጋር ነው። ፊደል ቆጥረው አቡጊዳን ዘልቀው መልዕክተን አንብንበው ብቻ አላበቁም፤ ይሉቁንም ሁለት ጊዜ ዳዊትን ደግመዋል። የቄስ ትምህርቱን አጠናቀው ፊታቸውን ያዞሩት ወደ ዘመናዊ ትምህርት ነበር። እዛም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ቢትወደድ ወልደ ገብርኤል በሻህ ትምህርት ቤት ተማሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት አቃቂ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ነበር። አቃቂ አድቬንቲስት የአዳሪ ትምህር ቤት «ልጅነቴን የቀረጸ፣ ስብዕናዬን ሙሉ ያደረገ ልዩ ትዝታን ያተረፍኩበት ነው» ይላሉ። የልጅነታቸው ስነ-ምግባር መቅረጫ በእውቀት ተስለው የወጡበት ነውና ስሙን ደግመው ደጋግመው ይጠሩታል።
በአቃቂ አድቬንቲስት አዳሪ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲማሩ ወደቤተሰብ መሄድ የሚቻለው በወር አንድ ቀን ነው። እዛ ከሁሉም ኢትዮጵያ ክፍል የመጣን ተማሪዎች ነን፤ ብዙ ሙስሊም ወንድም እህት ጓደኞችም ነበሩኝ፤ ትንሿ ኢትዮጵያ እዛ አለች። በጣም ደስ የሚል የሕይወት ልምድ ነው ያገኘሁት። ትልቁ በመጽሀፍ ቅዱስ ስነ-ምግባር እና ግብረ ገብ የተማርኩበት ነው። መጽሀፍ ቅዱስ ራሱን የቻለ ትምህርት ሆኖ ይሰጣል። የመጽሀፍ ቅዱስ ፈተና የወደቀ ወደ ቀጣዩ ክፍል አያልፍም። ይህን ያክል ጥብቅ ነበር። የማደሪያ ክፍላችን በጾታ የተለየ ይሁን እንጂ በክፍል ውስጥ፣ በቤተ-መጽሀፍ ከሴቶቹም ጋር አብረን ነበር የምናሳልፈው። የራሴን ማንነት እንዳገኝ ያደረገኝ ትምህት ቤት ነው ማለት እችላለሁ። አሁን ያለሁበትን ገጽታ የሰጠኝ ያ ዘመን ነው። ከሁሉም ሰው ጋር አብረን ተባብረን ነው የሚኖረው። ያደኩትም በብዙ ጓደኞች መካከል ነው ይላሉ።
ሕልምን ፈልጎ የማግኘት ትጋት
ልጅ ኤልያስ በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ የሚባሉ ባይሆኑም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 3 ነጥብ በማምጣት አልፈዋል። በውጤታቸውም በቀድሞ የንግድ ሥራ ኮሌጅ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በዲፕሎማ ተመድበዋል፤ እዛ አንድ ዓመት ያህል ተማሩ፤ ይሁን እንጂ የነበራቸው ቆይታ ብዙም አይደለም። የተመደቡበት ትምህርት የፍላጎታቸው አልነበረም፤ ቤተሰቦቻቸው ብዙም በትምህርቱ የገፉ አይደሉምና ኑሯቸውም የተመሰረተው በየግል ሥራ በመሆኑ በትምህርቱ «በርታ» የሚል ጉልበት አልሆኗቸውም።
የተመደቡበትን ትምህርት ተምረው ቢጨርሱም ተቀጥረው የሚከፈላቸው የዲፕሎማ የወር ደመወዝ በወቅቱ 347 ብር ነው። ይሄ ደግሞ ቤተሰባቸው በቀን ከሚያገኙት ገቢ ያነሰ ነው እናም በትምህርቱ ብዙም እንዲገፉ አላበረታታቸውም። ስለዚህ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ ጋር ተፋቱ። ትምህርትን ያቋርጠት እንጂ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቻቸውን አርአያ መከተልና ነጋዴ መሆንንም አልመጡም። የራሳቸው ሕልም አላቸው እና እሱን ፈልጎ ማግኘት ነበር ግባቸው።
የሥራ ባሕል ውርስ
አባታቸው በእንጨት ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ናቸው። መሳለሚያ አካባቢ ግዙፍ የእንጨት መሰንጠቂያ አላቸው። የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ብዙ ማሽነሪዎችን አሟልተው በርከት ያሉ ሰራተኞችን ቀጥረው ያስተዳድራሉ።
እሳቸውም ያደጉት በዚሁ የሥራ ባሕል ውስጥ ነው። አባታቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ቱታ አስለብሰው በእንጨት መሰንጠቂያው ድርጅቱ ከሌሎች ተቀጣሪ ሰራተኞች ጋር ሥራ እንዲሰሩ ያደርጓቸዋል። በድርጅቱ ውስጥ መግባታቸው ቱታ መልበሳቸው በራሱ ሁለት ነገርን ወደ ውስጣቸው ከቷል። አንድም ሥራን መልመድ የሥራ ክቡርነትን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሙያን ከሌሎች መልመድን አሳውቋቸዋል። በወቅቱ ግን እሳቸው ልጅ ስለነበሩ ትላልቅ ማሽነሪዎች ጋር መጠጋትና መንካት አይፈቀድላቸውም፤ የእሳቸው ሥራ ተዘጋጅተው የተጠናቀቁ መስኮት በር የመሳሰሉትን ቀለም መቀባት ነው። ሆኖም ግን ይሄ የአባታቸው መንገድ እሳቸውን አልነሸጣቸውም፤ የንግዱን ዓለም ልቀላቀል ብለውም አልተነሱም። አሁንም ቀልባቸው ትምህርቱ ላይ ነውና በማታው ክፍለጊዜ መማር አለብኝ ብለው በ1989 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍልን ተቀላቀሉ። ይሄንንም ቢሆን ማሳረጊያው ላይ አላደረሱትም፤ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ስርዓት «ከነበረኝ ርዕዮተ ዓለም ጋር ተፃራሪ ሆኖ ስላገኘሁት» ብለው አቋረጡ።
«ልጅነቴ አጼ ኃይለስላሴ የወረዱበት ደርግ ደግሞ የመጣበት ስለነበር ብዙ የተረጋጋ ነገር አልነበረም። መርካቶ አካባቢ ብዙ ሰዎች ከፖለቲካው ጋር ተያይዞ ይገደሉ ነበር። የተኩስ ድምጽ እየሰማን ነው ያደግነው» ይላሉ።
ሕይወት በባሕር ማዶ
እአአ መስከረም 2006 ጉዞ ወደ አሜሪካን ሆነ። በወቅቱ የሄዱት እርጥብ ልጅ (የ18 ወር) ሴት ልጃቸውና የቀድሞ ባለቤታቸው ጋር ነበር። እዛ ባሕሉ፣ ቋንቋውም፣ የአየር ንብረቱም፣ የሥራው ሁኔታም አዲስ ነው። በዚህ ሁኔታ ራስን አላምዶ፣ ገቢን አሟልቶ ቤተሰብን ማስተዳደር ግር ማለቱ አይቀርም፤ ልጅ ኤልያስም ይሄ አጋጥሟቸዋል። የነበራቸውን ነገር ከውስጣቸው አውጥተው አዲስ ካሉበት ሀገር ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ማስማመት ይጠይቃል፤ ለዚህ የሚሆናቸውን የአእምሮ ዝግጅት አደረጉ።
አሜሪካ የገቡት በወንድማቸው አማካይነት ነው። በራሳቸው አሜሪካ የመሄድ ሀሳቡ አልነበራቸውም። ሆኖ እድሉ ሲገኝ ተጠቀሙባትና ከነቤተሰባቸው አውሮራ ኮሎራዶ ገቡ። የመጀመሪያ ሶስት ወራት በመንገድ ላይ ምንም ሰው አላዩም፤ ሁሉም ባለመኪና ነው። እዛ ቦታ መኪና ማለት የእግር ጫማ እንደማለት ይቆጠራል። እርሳቸው ግን እስከ 20 ደቂቃ በእግር ተጉዘው ቤተ-መጽሀፍት በመሄድ በአንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃ ይሰበስባሉ። ከመርካቶ የሕዝብ ትርምስ መሀል የወጣ ብቸኛ መንገደኛ መሆን ምን ማለት ይሆን?
ከሶስት ወር ድንብርብር በኋላ ማሟላት ያለባቸውን በሙሉ አሟልተው የሥራ ፍቃድ አውጥተው ወደ ሥራ ገቡ። «ያለ መኪና መንቀሳቀስ በጣም ይከብዳል። አውቶብስ መጠበቅ ወይም ተሯሩጦ መሄድ በጣም ያስቸግራል፤ የሥራ ሰዓት ያባክናል። ያም ሆኖ ግን የመጀመሪያ አካባቢ እንቅስቃሴ አደርግ የነበረው በአውቶብስ ነው» ይላሉ ሁኔታውን እያስታወሱ። የአራት ወር ደመወዝ ካገኙ በኋላ አሜሪካ ሀገር መኪና መግዛት ቀላል በመሆኑ ብዙ አልተቸገሩም። በሀገራቸውም ባለመኪና ነበሩና አሜሪካን መኪና መንዳት አልፈተናቸውም፤ ቶሎ ተዋሀዱት፡፡
ቤተሰቦቻቸውን የማስተዳደር ኃላፊነት በጫንቃቸው ነው። ሥራ ሰርቶ ገቢ ማግኘት ግድ ነው። እሱን እየተወጡ ጎን ለጎን ደግሞ መማር፣ ራስን ማሻሻል፣ ወቅቱና ቦታው ለሚጠይቀው በእውቀት ብቁ ሆኖ መገኘት ደግሞ ያስፈልጋል፤ እነዚህን የማሸነፍ ትግል ቀጠሉ።
በአሜሪካን ሀገር በኮሙዩኒቲ ኮሌጅ አውሮራ እና ዴንቨር የተለያዩ የኮሌጅ ኮርሶችን በመውሰድ በኤሌክትሮኒሮዳያግኖስቲክ ቴክኖሎጂ በአሶሺየት ዲግሪ እአአ በግንቦት 2014 በኮሚኒቲ ኮሌጅ ኦፍ ዴንቨር ተመረቁ። ትምህርታቸውን ለማሳደግ ባላቸው ፍላጎትም በኖርዝ ካሮላይና በሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች ቻፕል ሂል እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቻርሎት በኒሮዳያግኖስቲክ እና ስሊፕ ሳይንስ በጥሩ ውጤት በመከታተል ላይ ሳሉ የሁለት ሴሚስተር ኮርስ ሲቀራቸው በሥራ አለመመቸት ምክንያት አቋረጡ። የቀጣዩ እቅዳቸውም በሪአድሚሽን የተቋረጠውን ትምህርት ማጠናቀቅ ነው።
እንግዳችን አሁን በኤሌክትሮ ኢንሴፋሎግራም እና በፖሊሶምኖግራፍ በቦርድ ሬጂስትርድ ቴክኖሎጂስት ናቸው። በዚሁ ሙያ እአአ ከግንቦት 2014 እስከ የካቲት 2025 ድረስ ለ11 ዓመታት ሰርተዋል። አሁን ሙሉ ጊዜያቸውን አዲስ በመሰረቱት እና ዋና ጽህፈት ቤቱን በአሜሪካን ሀገር ባደረገው የልጅ ኤልያስ መካነ አዕምሮ አማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ» (አሳኮ) እየሰሩ ናቸው።
አሳኮ ምስረታ
እንግዳችን የልጅ ኤልያስ መካነ አዕምሮ አማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ» (አሳኮ) ለመመሥረት የተነሱበት ዋና ዓላማ «መስከረም 3 ቀን 1994 ዓ.ም ለማዕድን ሚኒስቴር ማዕድን ሥራዎች መምሪያ ለማስፈተሽ ያቀረቡት የብረትና የአልሙኒየም ይዘት ያለው ናሙና ለግኝቱ ውጤት ለጠየቁት ሰርተፍኬት በደብዳቤ የተሰጣቸው ምላሽ ነው። ይሄ ሁኔታ ለምን የሚል ጥያቄን በአእምሯቸው አሳደረ። «ችግሩ የመነጨው በዘርፉ በቂ እውቀት ስለሌለ ነው የሚለውንም ተረዳሁ» ይላሉ። ምክንያቱም በዘርፉ ያለው እያንዳንዱ መመሪያ፣ ማረጋገጫ፣ መመዝገቢያ ፎርም ሳይቀር የተዘጋጀው በእንግሊዝኛ ነው። ስለዚህ በቂ እውቀት አለ ለማለት ይከብዳል። ሳይንሱን ከመረዳት አንጻርም ክፍተት አለ። ስለዚህ በራሳችን ቋንቋ ሳይንስ መማር ምርምር ማድረግ አለብን። ብዙ ሳይንቲስቶችን ማፍራት ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ ትምህርት መቅደም አለበት ትምህርቱም የሚሰጠው ብዙዎች በሚጠቀሙበት አማርኛ መሆን አለበት በሚል ከዛን ጊዜ ጀምሮ በአማርኛ ሳይንስን ማስተማር የሚችል ኮሌጅ ለመክፈት ወሰኑ፤ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ
አሁን ዋና ጽህፈት ቤቱን አሜሪካን አድርገው ከአሜሪካን መንግሥት ፍቃድና እውቅና አግኝተው ለመክፈት ቻሉ። በአሜሪካን ሀገር የሚገኙ አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን በአማርኛ የሚማሩበት ኮሌጅ ነው። በቀጣይ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ናቸው። የአማርኛ የሳይንስ ኮሌጁ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የሚያስተምር መሆኑን ይናገራሉ።
«አንድ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ በሌሎች ሀገር እንዳሉ ተመራማሪዎች ውጤት ላይ ለመድረስ ዋናው ቁልፉ የሳይንስ ትምህርትን በራስ ቋንቋ መማር፤ ማወቅና መረዳት መቻል ነው። አንድን ሥራ ጀምሮ ለመጨረስ ተያያዥ ትምህርቶችን መማር አለበት። በራስ ቋንቋ መማር ውጤታማ ያደርጋል። በቀላሉ ለመረዳትም ሆነ ለመመርመር በቂ ቋንቋ ያስፈልጋል። ይሄም የራስ ቋንቋ ነው» ይላሉ።
ልጅ ኤልያስ ይህንን ሲያነሱ ምሳሌ አድርገው የጠቀሱት ደግሞ በራሳቸው ቋንቋ የሚጠቀሙ የበለጸጉ ሀገሮችን ነው። ቻይናዎች የሚጠቀሙት የራሳቸውን ቋንቋ ነው። ጣሊያኖች፣ እንግሊዞች፤ ጀርመኖች፣ ጃፓኖች፤ ፈረንሳዮች… ሌሎችም ያደጉት ሀገራት የሚጠቀሙት የሌላውን ሀገር ቋንቋ ሳይሆን የራሳቸውን ነው። በዚህም ውጤታማ ሆነዋል። የማንኛውንም ሀገር ቋንቋ ማወቅ ክፋት የለውም፤ ነገር ግን የዛ ቋንቋ ተገዢ መሆን ግን በቀኝ እንደመገዛት ይቆጠራል። ቀኝ ግዛት ሲባል የሀገር ሉአላዊነት ላይ ብቻ አይደለም የሚሰራው የሌላውን ሀገር ቋንቋ ለመጠቀም መገደድም ቀኝ ግዛት ነው። ኢትዮጵያም ከቀኝ ግዛቱ መውጣት አለባት። በራሳችን ቋንቋ መማርና መመራመር ይጠበቅብናል የሚል አስተሳሰብ አላቸው።
ወጣትነትና ሕልምን መኖር
ወጣትነታቸውን ሲያስታውሱ የማልረሳው ያሉት የወቅቱን የደርግን ስርዓት ነው። ደርግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ጊዜ ብሄራዊ ውትድርና የመሳሰሉትን በሚገባ ያስታውሳሉ። መጥፎ ስሜት ነው ያላቸው። የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ንግግሮች አይረሳቸውም። «እኔ ደጋፊያቸው አልነበርኩም፤ ሀገራችን እስካሁን ድረስ ምስቅልቅል ውስጥ እንድትገባ ካደረጉ መሪዎች አንዱ ናቸው ብዬ ነው የማምነው»በማለት የስርዓቱን አስከፊንተ ይገልጻሉ።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ብዙ ፊልሞችን ማየታቸውን ይናገራሉ። ዓለም አቀፍ ነገሮችን ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። አንድን ነገር የመፍጠር ፍላጎት አላቸው፤ አንድን ነገር አስተውሎ መጀመር ጀምሮ መጨረስ ይፈልጋሉ። «በልጅነቴ በእንጨት መሰንጠቂያው ውስጥ ስቆይ ሰራተኞቹ ከእንጨት ክላሽ እየሰሩ መጫወቻ ይሰጡኝ ነበር። በዛን ጊዜ የወታደር ዘመን ስለሆነ የልጆች መጫወቻ ሽጉጥ ነው። እኔ ግን በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን ያለፍኩት በእንጨት ሥራ ሙያና ማሽኖች ውስጥ ነው፤ ለዚህም ይመስለኛል አሁንም መሥራት የምፈልገው መፍጠር መመራመር ላይ ነው። አሁን እየሠራሁ ያለሁት ሕልሜን ነው።» በማለት ያሰቡት ሁሉ ባይሳካላቸውም የስኬት መንገድ መክፈት መጀመራቸው ግን ያስደስታቸዋል።
ለሀገሬ የምመኝላት
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር ያለው የሳይንስ ትምህርቱ በቀጥታ ተግባራዊ እየተደረገ ባለመሆኑ ነው። ‹‹ትምህርቱ መድረስ ለምንፈልገው ደረጃ ሊያደርሰን ይችላል ወይ›› ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፤ ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ሀገር ናት፤ የብዙ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሀገር ናት። ያ ሁሉ ተባብሮ አንድ ሆኖ ቢሰራባት ጥሩ ደረጃ ላይ ትደርሳለች የሚል እምነት አላቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሳይንስ ትምህርቱ መሬት የወረደ አይደለም። ማለትም በጣም ብዙ ሰዎች በእጃቸው ብዙ ሥራ መሥራት እንዲችሉ ዕድል የሚሰጥ የትምህርት ስርዓት የለውም። አሁን ትውልዱ እንዲቀረጽ የሚፈለገው በሳይንስ ነው። ዓለምን የቀየረ ትልቅ የትምህርት አሰጣጥ ነው። እሳቸውም አሜሪካ ኮሌጅ ውስጥ የኬሚስትሪ ትምህርት ወስደዋል። ብዙ ነገሮችን ማወቅ የሚቻለው በእጅ እየተሞከረ መሆኑን ተገንዝበዋል። በእጅ መስፋት፣ መነካካት፣ መሞከር ያስፈልጋል። በተፈጥሮ የተገኙትን ወደ አገልግሎት የመለወጫ ዘዴ መጠቀም አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል።
ይሄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም የሚቀበለው የትምህርት አሰጣጥ ነው። በኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጡ አንዱ በራሳችን ቋንቋ አይደለም ስለዚህ ቋንቋውን በደንብ አድርጎ ሳይንሱን የመረዳት ችግር አለ። ሳይንስ የራሱ ምናብ አለው፤ ያንን በደንብ ተረድቶ ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባ ይናገራሉ። ለምሳሌ ናይትሮጅን አየር ላይ አለ። ናይትሮጅንን ከአየር ላይ ቀዝፎ ወደ ፈሳሽነት ቀይሮ ወደ ማዳበሪያነት መለወጥ ለጀርመኖች በዛው ክፍለ ዘመን ትልቁ ስኬታቸው ነበር። ይሄ የሆነው በራሱ ቴክኒካል ዘዴ ነው። በኢትዮጵያ ተማሪዎች ይሄንኑ ሳይንስ በቃል ከመሸምደድ ይልቅ በተግባር ሰርተው ውጤቱን በተጨባጭ ማየትና ሀገር እንዲጠቀምበት ማድረግ መቻል አለባቸው።
ዓላማ- በቅርብ ዓመታት
የልጅ ኤልያስ ቀጣዩ ዓላማቸው ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ የሰለጠኑ የዓለም ሀገራት በሳይንስ የምትጠቀም፤ በሳይንሱ የምትታወቅና የምትጠቀስ ሀገር ሆና ማየት ነው። የኢትዮጵያ ትልቁ እድል የራሷ ፌደላት አላት። የሯሷ አሀዝ አላት። ይሄንን ወደ ሳይንስ ብንቀይረው ብዙ ሰዎች ሳይንስን መረዳት ይችላሉ። ከራሷ አልፎ ከአፍሪካ የተጻፉ ሰነዶች ያሉባት ሀገር በመሆኗ፤ ለአፍሪካም ትልቅ ምሳሌ ሀገር ነው የምትሆነው። ይሄንን ለመተግበር እየሰሩ ይገኛሉ።
« አሁን ባለንበት ደረጃ ብዙ የምናውቃቸውን ማየት እንችላለን። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኬሚካል ኢንደስትሪዎች ቴክኖሎጂ ያለባቸውን ችግር እንደምሳሌ አድርገን እናያለን። ሁሉም ሥራዎች የተሰሩት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፤ የኬሚስትሪ፤ የፊዚክስም ሆነ ባዮሎጂ የተጻፉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። እነዚህ ነገሮች ወደ አማርኛ መመለስ ያስፈልጋል።» ይላሉ።
ኢትዮጵያ በስልጣኔ ቀደምት ነበረች። በአርክቴክት በጣም አስደናቂ ኪነሕንጻዎች ተሰርተዋል። አክሱም ሀውልት ከሺ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ነው። እነዚያ ነገሮች ማሽን ሳይኖር እንዴት እርስ በርስ ተጣብቀው በሰው ኃይል የዛን ያህል ርዝመት ተሠራ የሚለውን የዓለም ሳይንስ እያጠናው ነው ያለው። ይሄንን ስልጣኔያችንን መመለስ እንዳለብን ያምናሉ።« ሀገሬ ሆና ማየት የምሻውም በሳይንስ በቴክኖሎጂ በቅታ ነው። » ሲሉ በቁጭት ይገልጻሉ።
የሳይንስ ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዝኛ ነው። ሆኖም የመሥሪያ ቤቶች አገልግሎት መስጫው ቋንቋ አማርኛ ነው። እናም ሁሉም ተማሪ በእንግሊዝኛ ተምሮና ተመርቆ በእንግሊዝኛ አይሰራም፤ ለምንድነው ታዲያ በራሳችን ቋንቋ የማንማረው ? ይህን ለማድረግ የሚያስቸግረን ምንድነው ? ሲሉ ይጠይቃሉ። ለዚህ ምላሽ ማግኘት ከተቻለ ብዙ በሳይንስ በኩል ያሉ ችግሮች ይፈታሉ የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።
ኢትዮጵያ በራሷ ሀገር የራሷን ሳይንስ የምታዳብር ብትሆን ትልቁ የምትሠራው ነገር በመጀመሪያ ደረጃ ቴክኖሎጂ በደንበ ማወቅ፣ አካባቢያዊ ነገሮችን ከኢኮኖሚ አንጻር መጠቀም የሚያስችል ነገር መሆኑን መረዳት ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አልሙኒየም ሰልፌት ፋብሪካን የመሰረቱት ፖላንዶች መሆናቸውን ያስታውሳሉ። ያ ፋብሪካ ብቻ ነው በኢትዮጵያ ጥሬ ሀብት በመጠቀም የሚሠራው፤ ፋብሪካውን የመሰረቱትና ቴክኖሎጂውን ያስቀመጡት ኢትዮጵያውያን አይደሉም። ይሄ ፋብሪካ በራሱ ስትራግል ያደርጋል። ነገር ግን ይሄንን የመሰረቱት የራሳችን ሰዎች ቢሆኑ በራሳችን የመጠገን፣ ፋብሪካውን ማሻሻልና ማሳደግ የመሳሰሉት ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፤ ብዙ ሀገሮች የዚህ እውቀት አላቸው። ነገር ግን እውቀታቸውን አያሻግሩም። ጥገኛ እንድንሆን ነው የሚፈልጉት። እኛም የራሳችን ቴክኖሎጂ እንዲኖረን በራሳችን ነው ማስጠናት ያለብን። ያንን ለማድረግ እንግሊዝኛ ማወቅ ጥሩ ነው።
ገበሬ እስካሁን ድረስ ለምን በበሬ ያርሳል፣ ጋሪዎቻችን ለምንድነው የጋሪ ጎማ የማይኖራቸው፣ ይሄ ተሻሻለ ተብሎ እንኳን ባጃጅ ቢመጣ ይሄም የኢትዮጵያውያን ቴክኖሎጂ ውጤት አይደለም። የእኛ ተማሪዎች ራሳቸው ወደ ምህንድስናው ገብተው በራሳቸው መሥራት መመራመር የሚቻለው እርስ በርሳችን ከሌላው ሀገር እውቀቱን በማምጣት ብዙ ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ እንዲማሩና እንዲሰሩ ማድረግ ሲቻል ነው።
ግሎባላይዜሽን
ግሎባላይዜሽን ጠቃሚ ጎን እንዳለው ሁሉ ጎጃም ጎን አለው። በአንድ በኩል ቀኝ ግዛት ነው። የሰለጠነውን ወጣት የሰው ኃይል የራስ ማድረግ ነው፤ እስካሁን ባለው አካሄድ ተማሪዎቻችን ተምረው ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሌላ ሀገር ሄደው ከፍተኛ ገንዘብ የማግኘት እድል ሊኖራቸው ይችላል እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ሀገርን ለመቀየር የሳይንስና ምርምር ዕድል የላቸውም። «ግሎባላይዜሽን እኛን አዲሱ የባርነት ቀበቶ ውስጥ ይከተናል እንጂ ሀገራችንን የማሳደግ ችሎታ እንዲኖረን አያደርገንም፤ በጣም መጥፎ ጎን ነው ያለው» ሲሉ የተለያዩ ማሳያዎችን በማቅረብ ይሞግታሉ።
የመስታወት፣ የብረት፣ የአልሙኒየም አሠራር እና መዳብ እንዴት እንደሚወጣ በሳይንስ መጽሀፎች ላይ ተጽፈዋል። እነዚህ ነገሮች በዓለም ላይም በሀገራችንም የሚገኙ ናቸው። በኢትዮጵያ የሌላው የዚህን ቴክኖሎጂ ማወቅ ነው፤ ማግኘት ያለብን ቴክኖሎጂውን ነው እንጂ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ሀብታችንን ለውጪ ባለሀብት አሳልፎ መስጠት አይደለም።
የውጪ ባለሀብቶች የሥራውን ሚስጢር አይነግሩም፤ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የራሳቸውን ሰራተኛ ያደርጋሉ፤ እኛ የምንፈልገው ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ተመራማሪ ደርሶ እነዚህን ነገሮች መሥራት እንዲችል ማድረግ ነው፤ለዚህ ትምህርትና እውቀት ያስፈልጋል። ይሄ በአንድ ቀን ከሌሊት አይመጣም። ሳይንስ ዘመናትን ይፈልጋል፤ ተማሪዎች ኮሌጅ ውስጥ ገብተው መሰልጠን አለባቸው። ኤሌክትሪካል ኢንጂነር፣ ኬሚካል፣ መካኒካል እንጂነር እንዲሁም ከማዕድን ጋር የተያያዘ እንዴት መሬት በወረደ መልኩ ማስተማር፤ ከዛም በየአካባቢያቸው ውጤት እንዲያመጣ መሥራት አለብን በሚለው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ያካፍላሉ።
የባለ ራዕዩ መልዕክት
በሳይንስ ራስን ማነጽ የራሱንም ሆነ የማሕበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ያስችላል። ወጣቱ ለእውቀት ራሱን ክፍት ማድረግ፣ በሕብረትና በትብብር መስራት፣ በሀቀኝነት ሀገርን ማገልገል አለበት። ከሱስ የነጻ እና በስነምግባር የታነፀ መሆን፤ ከሁሉም በላይ ሀገርን መውደድና ለሀገር ተቆርቃሪ መሆን ያስፈልጋል። ሀገርን የሚቀይረው የተማረ ወጣት ነው። ውጤት ላይ ለመድረስ የሚጠይቀውም ጉልበትም ሆነ እውቀት እንደሰለጠነው ዘመን ለሀገራችን ማበርከት አለብን። ለዚህ ደግሞ ከወጣቱ ብዙ ይጠበቃል። ሳይንስ ላይ ትኩረት ማድረግ በፈጠራና ምርምር ላይ መረባረብ ሀገርንም ራስንም ይቀይራል። እዚህ ላይ በርቱ! ንቁ! ለማለት እወዳለሁ በማለት መልዕክታቸውን ቋጩ።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም