‹‹ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ፤
ተዘነጋሽ እንዴ ኢትዮጵያ መሆኑ፤
አንቺም በሀይማኖትሽ እኔም በሀይማኖቴ፤
መኖር እንችላለን አይጠበንም ቤቴ…››
ዘፈኑ ከድምፃዊው ቴዎድሮስ ካሳሁን ተመራጭ ጣዕመ ዜማዎች ውስጥ ጆሮን አልፈው፤ ውስጥን ሰርስረው በመዝለቅ ልዩ ስሜት ከሚፈጥሩት ውስጥ ተጠቃሽ ነው። በተለይ ይህ የግጥም አንጓ የሚፈጥረው ስሜት የአብሮነት ባህላችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን የተዋጣለት መሆኑንም ጭምር ምስል ከሳች ነው። ይህ እሴት ደግሞ አገሬን ከሌላው ዓለም ለየት እንደሚያደርጋት እያሳየ ስሜት እየፈጠረብኝ ዘመን ተሸግሮ ዛሬ ላይ አድርሶናል ብል ማጋነን አይሆንብኝም
እነዚህ እሴቶች ጤናማ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲኖር የሚጫወቱት ሚና ከፍ ያለ ነው። ለማህበረሰባችን በጋራ መኖር፣ መተሳሰብ፣ መከባበርና መተዛዘን ወዘተ ያስተማሩም ናቸው። ግና ዛሬ ዛሬ በየ ዘመኑ በሚጫኑ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ጠንካራው የአብሮነት ባህላችን ክፉኛ እንደተጎዳ የሚናገሩ ብዙ ናቸው።
አቶ ሳሙኤል ተክለአብ ምንም እንኳ ተወልደው ያደጉት ኦሮሚያ ክልል ቢሆንም የሌላ ብሄር ተወላጅ ናቸው። ከአብሯደግ ጓደኞቻቸውና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መልካም ቀረቤታ እንዳላቸው ቢናገሩም አንዳንድ የፖለቲካ አመራሮች በሚሰሩት ጥቅምን ያማከለ ስራ የአብሮነት ባህላችን እየተሸረሸረ፤ በህብረተሰቡ መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር አድርጓል። በሂደትም የተለየ አመል እየተፈጠረ የማትጠበን አገራችን በጠበበ አስተሳሰብ እንድናያት ሆኖ የአብሮ መኖር ባህላችን ፈተና ውስጥ ገብቷል።
‹‹በአሁኑ ወቅት የአብሮነት ባህላችን የተጎዳ ቢሆንም ሀገራችን የገጠማትን ፈተና ከጥፋት የመታደግ አቅሙ ዛሬም አልሞተም›› የሚሉት አቶ ሳሙኤል አንዳንድ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የዜጎችን በነጻነት የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል። በተለይ አንዳንዶች አብሮ የመኖር እሴቶችን በመድፈቅ የሕዝቦች ግንኙነት እንዲሻክር የሚያደርጉ መንገዶችን በማስረጋቸው በሀገራችን ለሚታየው ችግር በመንስኤነት ሊጠቀስ ይገባል ባይ ናቸው ።
ስርዓት ተዘርግቶለት አንዱ ብሄር በሌላው የውሸት ትርክት እየተዘራ ክፉ አመል ኖሮ የዜጎችን ማህበራዊ ህይወት ያመሰቃቀለና ጥርጣሬን የዘራ ነው ሲሉ አቶ ሳሙኤል ይወቅሳሉ። በዚህም ምክንያት የማትጠበው አገር ጠባ መከባበርና በጋራ መኖር አደጋ ውስጥ ገብቷል። ከላይ በመግቢያው ከተገለፀችው ዜማ ውጭ በሌላ ኢትዮጵያ የተሰራ ታሪክ እስኪመስል ድረስ ወንድም ወንድሙን መግደልና ማፈናቀል፣ የማትጠበው አገር ጠባ ታይታለች ሲሉ በሀዘን ስሜት ነው።
አብሮ የመኖር እሴታችን በፖለቲካ አስተሳሰብ እየተሸረሸረ ነው የሚሉት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ዮዲት ብርሀኑ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ለዘመናት ትውልድን እያሸጋገሩ የመጡ አብሮ የመኖር እሴቶቻችን የፖለቲካ ስራው ክንዱን አሳርፎበታል፤ ተጽዕኖ ስር በመውደቁም አንዱ ሌላውን በጎሪጥ የሚያይበትን አስተሳሰብ እያሰፋ ነው ብለዋል።
‹‹ጥንት አባቶቻችን በጥቃቅን ጉዳዮች ሳይለያዩ በጋራ ተከባብረውና ተሳስበው ይኖሩ ነበር፤ አሁን ግን ተምረናል የሚሉ ሰዎች በተለይም ፖለቲከኞች በህብረተሰቡ መካከል የቆየውን አብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችን በማራመዳቸው ሰዎች በሰላም የመኖር ህልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል።›› የወይዘሮ ዮዲት አስተያየት ነው።
የማህበራዊ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ክንዳለም ዳምጤ የአቶ ሳሙኤልን ሀሳብ ይጋራሉ። በየዘመኑ የሚመጡ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ማህበራዊ እሴቶችን ጎድተዋቸዋል ሲሉ ማሳያ በማቅረብ ነው። ‹‹ደርግ በሶሻሊስት ርዕዮቱ ‹እኩልነትና አንድነት› በሚል ማህበረሰብን በአንድ ቋት ውስጥ በማስገባት ሀይማኖትና ባህል የሚሰጡትን ማህበራዊ ቱሩፋቶች ለማጥፋት ሞክሯል። ኢህአዴግም ሰዎችን በብሄር በመከፋፈል በማህበረሰቡ መካከል የነበረው ተከባብሮና ተፋቅሮ የመኖር እሴታችን ተሽመድምዷል።›› ሲሉ ወቅሰዋል።
ትክክል የሚመስሉ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞችን እያመጡ ለአገዛዝ በሚመቻቸው መሰረት ቅርጽ በመሥጠት በማህበረሰቡ መካከል የዳበሩ እሴቶችን ሲሸረሽሩ ይስተዋላል። ዛሬ ላይ ፖለቲካችን አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ የሚለውን አብሮ የመኖር ባህል አደብዝዞታል። ፖለቲካችን ሰውን ወደ ሀይማኖቱ ወደ ዘሩና ወደ ማንነቱ የሚገፋ ጎጠኛ ስርዓትም ሆኗል ይላሉ ዶክተር ክንዳለም።
ለብዙ ችግሮች መፍቻነት የሚውሉ የአብሮነት የመኖር እሴቶች በፖለቲካ አስተሳሰብ ተኮርኩመው ዛሬ ላለንበት ቀውስ ተዳርገናል። ሀይማኖታዊና ባሕላዊ ተቋማትም የፖለቲካ መድረክ እየሆኑ መምጣታቸው ለእሴቶቻችን መኮስመን ቁልፍ ምክንያት ናቸው።
በኮከበ ፅብሐ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ማናየ እንግዳወርቅ እንደገለፁት በየዘመኑ የሚመጡ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እሴቶቻችንን የመሸርሸር ተጽዕኖ እንዳላቸውና በይበልጥም ባለንበት ዘመን ይህ ሁኔታ ጫፍ እንደነካ ያምናሉ። ፖለቲካው በባህርይው አካባቢያዊነትና ዘረኝነትን የሚያበረታታ በመሆኑና ሀገሪቱን የሚመሩት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘር የተደራጁና የተበላሸ አስተሳሰብ በመያዝ እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ድረስ በመውረድ በአብሮነት ባህላችን ያልጠበበችው አገር ጠባ እንድትታይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ይላሉ።
አብሮነትና ተቻችሎ የመኖር ባህላችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መጥቷል። ሰዎች ሀገራዊ አስተሳሰባቸውን ትተው አካባቢያዊ እየሆኑ በመምጣታቸው የነበረንን ጠንካራ ማህበራዊ እሴት አዳክሞታል የሚሉት አቶ ማናየ በሰዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲዳብር ወላጆችና መምህራን የልጆችን ስብዕና በመቅረጽ ረገድ ሚና ሊጫወቱ ይገባል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የአብሮነት ባህላችን በፖለቲካው ስራ ቢደፈቅም አገሪቱን ከከፋ ሁኔታ የታደገ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ አስቀምጠዋል። መንግስት ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት ተሳስሮ የመጣበትን እሴቶቹን ከፖለቲካ ስራ መለየት አለበት። በዚህም ሕዝቡንና ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ ሁኔታ ለማስገባት የሚሰሩ መጥፎ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በተመረጡ ርዕዮቶች በመተካት ለአብሮነት እሴቶቻችን ዋጋ መስጠትና ዳግም መጠንከር ሀይልና ጉልበቱን ማዋል አለበት ሲሉ መክረዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011
ኢያሱ መሰለ