የቱሪዝም ዘርፍ በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ድርሻ ለማሳደግ ነባርና አዳዲስ የመዳረሻ ልማቶችን ማካሄድ፣ የመስህብ ሀብቶችን ማስተዋወቅ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚመጥን መዋቅራዊ አደረጃጀትና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሠራር መዘርጋትም ሌላው ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበትም ይጠቁማሉ። ነባራዊ ሁኔታን ያማከሉ ፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎች ማድረግም እንዲሁ ለውጤታማነቱ ቀዳሚውን ድርሻ ከሚወጡ ተግባራት መካከል መሆናቸውንም ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
ከላይ ከተጠቀሱት መሠረታውያን ባሻገር ቱሪዝም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ሚና ተኪ እንደሌለውም ይገለጻል። በተለይ የሆስፒታሊቲ፣ የትራንስፖርትና የአስጎብኚ ባለሙያዎችና ቱር ኦፕሬተሮች ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም ይጠቁማል። መንግሥት የመስህብ ሥፍራዎችን የመለየት፣ የማልማት፣ የመጠበቅና የጎብኚዎችን ደህንነት የማረጋገጥ ድርሻን ይውሰድ አንጂ፤ ከግል ዘርፉ ጋር ካልተቀናጀ የሚፈለገው ውጤት ሊመጣ አይችልም።
በዘርፉ የዓለም አቀፍ ቱሪስት ፍሰት ከፍተኛ እንዲሆን አስጎብኚ ድርጅቶችና ባለሙያዎች (tour operators and professionals) ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይገለፃል። አስጎብኚ ድርጅቶች የኢትዮጵያን የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና ሌሎች የቱሪዝም መስህቦችን ለጎብኚዎች በማስተዋወቅ ከፍተኛ የቱሪስት ቁጥር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ፤ ቆይታቸውንም በማራዘም፣ የሀገሪቱን ገፅታና ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲያሳድግ የማድረግ ኃላፊነትን እንደሚወጡ ይገለፃል።
አስጎብኚ ድርጅቶችና ባለሙያዎች በተለይ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች ለመጎብኘት በሚመጡበት ወቅት የጉዞ እቅድ በማውጣት፣ የሚያርፉበትን ሆቴል፣ የሚጎበኟቸውን መስህቦች በማመቻቸት፣ በቆይታቸው የተሻለ ልምድና ተዝናኖትን አግኝተው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥት የግል ባለሀብቶችና ተቋማት በሆቴል (በቱሪዝም ኢንቨስትመንት)፣ በገልግሎት ዘርፍ፣ በአስጎብኚ ድርጅቶች፣ በሌሎችም ንኡስ የቱሪዝም ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ እያበረታታ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ አስጎብኚ ድርጅቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ይህም ድርጅቶቹና በጉብኝት መሪነት የሚያገለግሉት ባለሙያዎች ውጤታማነት ለዘርፉ ዘላቂ እድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ይታመናል።
ንብረት አደም መሀመድ የሀመር ላንድ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነው። የዝግጅት ክፍላችን በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ በተካሄደው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ላይ በተገኘበት ወቅት በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ድርጅቱ እየሠራ ስላለው ሥራ አነጋግሮት ነበር። እርሱ እንደሚለው፤ ሀመር ላንድ ላለፉት 11 ዓመታት የመስህብ ሀብቶቹን ለዓለም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ሲያስጎበኝ ቆይቷል። በዋናነትም በደቡባዊው ኢትዮጵያ በጅንካና በኦሞ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ መዳረሻዎችን ሲያስተዋውቅ ቆይቷል። በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ ለመሆን እየሠራ ይገኛል።
‹‹በውጭ ሀገር ቱሪስቶች ላይ ዋና ትኩረታችንን አድርገን እየሠራን ነው›› የሚለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ ቱሪስቶቹን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በድርጅቱ ዌብ ሳይት፣ በቱሪስት አድቫይዘር፣ በአውደርዕይ እንዲሁም በአጋርነት ከሚሰሩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ድርጅቱ ያደረገውን ስምምነት እንደሚጠቀም ያስረዳል።
ማህበራዊ ሚዲያ (በኢንስታግራም፣ በቲውተር፣ ፌስቡክና በመሳሰሉት ገጾች) የኢትዮጵያን የመስህብ ሥፍራዎች በማስተዋወቅ እንዲሁም ድርጅቱ ልዩ ጥቅሎችን በማዘጋጀት ቱሪስቶቹ ሀገሪቱን እንዲጎበኙና ቆይታቸውን አራዝመው እንዲሄዱ እንደሚያመቻች ይገልፃል። ይህ መሆኑ የሀገሪቱን ኢኮኖሚን ከማሳደጉም ባሻገር መዳረሻው አካባቢ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የሥራ እድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልፃል።
ከ 14 ዓመቱ ጀምሮ በጅንካ የአካባቢውን ሀብቶች በማስተዋወቅ ከቱሪስቶች ጋር የመሥራት ልምድ እንዳዳበረ የሚናገረው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ንብረት፤ የተወለደበት አካባቢ በባህል የበለፀገና የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ መሆኑ በይበልጥ ከሙያው ጋር እንዳስተዋወቀው ይናገራል። በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢ መሰል የባህል፣ የተፈጥሮ፣ የቅርስ እና አርኪዮሎጂካል መንደሮች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ከቻሉና ዘርፉ እንዲያድግ በቅንጅት ከተሠራ የቱሪስት ፍሰቱን ማሳደግ እንደሚቻል አስታውቋል።
‹‹ለቱሪዝም እድገት እንዲሁም ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር በዋናነት ሰላም አስፈላጊ ነው›› የሚለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ ዓለም አቀፍ ቱሪስቱን ለመሳብ የቱሪዝም ሀብቶቹን ማስተዋወቅና ተወዳዳሪ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ቀዳሚው ጉዳይ ግን ሰላምና ደህንነትን ማስፈን ነው›› ሲል ያስገንዝባል፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ ኢትዮጵያን በቀዳሚነት ማሰለፍ የሚያስችል አቅም እንዳለ ገልጿል።
እንደ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች (እንደ ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ) ካሉት አንዱ መሆን የቻለና በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ መፍጠርም የሚችል ኢንዱስትሪ ነው። ይህንን በሚገባ ለመጠቀም የቱሪዝም መሠረተ ልማት ማሟላት፣ ሰላምና ደህንነት ማስፈን እንዲሁም በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ የተማሩ ባለሙያዎችን ማሠማራት እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮቪድ ወረርሽኝን እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ ጥቂት የማይባሉ የአስጎብኚ ደርጅቶች ዘርፍ አየቀየሩ እንደሚገኙ የሚገልፀው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ ሀመር ላንድ እና ሌሎች መሰል የአስጎብኚ ድርጅቶች ግን የቱሪዝም ዘርፉ ያለውን መልካም አድል እና በመንግሥት የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት በመመልከት አሁንም ድረስ ድርጅቶቻቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ይገልፃሉ።
ደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል ባህላዊ ሀብቶች በስፋት የሚገኙበት እንደመሆኑ መጠን የሀመር ላንድ አስጎብኚ ድርጅትም ዋናው ትኩረቱን በባህል ቱሪዝም ላይ አድርጓል ሲል የሚናገረው ንብረት ፤ በሌሎችም የተፈጥሮና የታሪክ መዳረሻዎች ላይ ቱሪስቶችን በመውሰድ የኢትዮጵያን ሀብቶች እንደሚያስተዋውቅ ያስረዳል።
ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ከአስጎብኚነት ባሻገርም የፎቶግራፍ ባለሙያ መሆኑን ጠቅሶ፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ከታዋቂው የፎቶግራፍ ባለሙያ ጆዊ ላውረንስ ጋር በመተባበር ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል ስያሜ ያለው የፎቶግራፍ መፅሀፍ ማሳተሙን ይገልጻል። ይህ መፅሀፍ በአማዞን ከፍተኛ ሽያጭ እያስመዘገቡ ካሉ የፎቶ መፅሀፎች ውስጥ አንዱ መሆኑንም ጠቅሶ፣ ይህ ሥራቸውን የቱሪዝም ዘርፉ ያለውን አቅም፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ውበትና መስህብ ለማሳየት እንደተጠቀሙበትና፤ ተጨማሪ አቅም አንደሚሆን ሙሉ እምነት የጣለበት መሆኑን ተናግሯል።
‹‹የኢትዮጵያን ቱሪዝም አሁን ካለው በተሻለ ማሳደግ ይገባል›› የሚል እምነት ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በኮቪድ ወረርሽኝና በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ባለው አለመረጋጋት እየተፈጠረ ያለውን ጫና ለመቀነስ መንግሥትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አመልክቷል። እንደ አስጎብኚ ድርጅትም ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች በማስተዋወቅ ከቱሪስት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መጠቀም እንዲቻል የግል ድርሻውን እንደሚወጣም አስረድቷል።
ሃይማኖት ዘርዓይ የሰሜን ኢኮ ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅት የማርኬቲንግ ባለሙያ ነች። ሰሜን ኢኮ ቱሪስት በዋናነት ተፈጥሮን መሠረት በማድረግ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ለቱሪስቶች በማስጎብኘት ይታወቃል። የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ በመሆንም የተፈጥሮ ቱሪዝም በኢትዮጵያ ሰፊ ድርሻ እንዲኖረው እየሠራ መሆኑን የማርኬቲንግ ባለሙያዋ ሃይማኖት ትናገራለች።
ዓለም አቀፍ ቱሪስቱ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች እና መልከዓ ምድር ለመጎብኘት ፍላጎት እንዲኖረው ሰሜን ኢኮ ቱሪዝም እየሠራ መሆኑን የምትናገረው የማርኬቲንግ ባለሙያዋ፤ ጎብኚዎች በተፈጥሮ አካባቢዎች ሲገኙ ምንም አይነት ተፈጥሯዊ ያልሆኑ በአድ ነገሮች እንዲጠቀሙ ድርጅታቸው እንደማይፈቅድ አስታውቃለች።
‹‹በኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ላይ በጎ ተፅእኖ ለመፍጠር እየሠራን ነው›› የምትለው የሰሜን ኦኮ ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅት ማርኬቲንግ ባለሙያዋ ሃይማኖት፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረትና ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት የምትሰጥ ሀገር ስለመሆኗ ድርጅቷ አጉልቶ ለማሳየት እና ገፅታዋን ለመገንባት እየሠራ መሆኑንም ጠቅሳለች። በዚህም ተፈጥሮ የሚወዱና የሚንከባከቡ ቱሪስቶች ላይ ልዩ ተኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ትገልፃለች።
እሷ እንደምትለው፤ በሰሜን ኢኮ ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅት አማካኝነት በርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፤ አስጎብኚ ድርጅቱ እነዚህ ቱሪስተቶች በጉዞ ላይም ይሁን በማረፊያ ቦታቸው የፕላስቲክ ኮዳ ባለመጠቀም፣ ተፈጥሯዊ ምርቶችን በማበረታታት፣ ለአየር ብክለት ምክንያት ሊሆኑ የማይችሉ ቁሳቁስን በመያዝ መስህብ ሥፍራዎችን እንዲጎበኙ ያደርጋል፡፡ ጎብኚዎች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባሻገር ለመዳረሻ ሥፍራዎች ጥበቃ የሚኖራቸውን ደርሻ ማሳደግ ይገባል ስትል ገልጻ፣ ይህን ማድረግ ከተቻለ ዘላቂና ጠንካራ የቱሪዝም ዘርፍ መገንባት እንደሚቻል አስታውቃለች፡፡
እንደ ማርኬቲንግ ባለሙያዋ ገለፃ፤ አስጎብኚ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በብዛት እንዲገቡ፣ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ እንዲያገኙና በብቁ ባለሙያ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ የድርጅቶቹ አቅም ማደግ ይገባዋል። ለዚህም መንግሥት ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን በማድረግና በቅንጅት በመሥራት ሊደግፋቸው ይገባል። ይህንን በዘላቂነት ማድረግ ከተቻለ በቱሪዝም ዘርፉ እንዲመጣ ለሚታሰበው ለውጥ የአስጎብኚ ደርጅቶች የጀርባ አጥንት መሆን ይችላሉ።
ሰሜን ኢኮ ቱሪስት አስጎብኚ ደርጅት ከተመሠረተ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ጨምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለቱሪስቶች ሲያስጎበኝ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የኮሮና ወረርሺኝና፣ በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሯል፤ ይህን ተከትሎም የቱሪስቱ ቁጥር ቀንሷል።
ደርጅቱ እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ኢትዮጵያን ማስተዋወቁን መቀጠሉን ተናግራ፣ አሁንም ድረስ የቀጠለው አለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ መፍትሄ ሲያገኝ አሁን ካለውም በተሻለ መሥራት እንደሚችሉ አስታውቃለች።
በኢትዮጵያ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተገነቡ ስለመሆናቸውም ሃይማኖት ጠቅሳ፣ መስህቦቹ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በብዛት እንዲመጡ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ትገልፃለች። ድርጅታቸው ለቱሪስቶች የሚያዘጋጀውን የጉብኝት እቅድ ለማስፋት የተገነቡትና እየተገነቡ የሚገኙ መዳረሻዎች ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸውም ታስረዳለች።
ቱሪዝም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ልዩ ድርሻ እንዲኖረው መዳረሻዎችን ማልማት፣ ማስተዋወቅና ነባሮቹን ከጉዳት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አመልክታ፣ ከሁሉም በላይ ግን ሰላም ለቱሪስቶች ደህንነት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁማለች። በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሁን ያለው አለመረጋጋት እንዲሰክንና ሰላም እንዲፈጠር መሥራት እንደሚገባው አስገንዝባለች።
ይህንን ማድረግ ከተቻለ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶች ከበቂ በላይ መሆናቸውን ጠቅሳለች። እንደ አስጎብኚ ድርጅት የኢትዮጵያ ሰላም እንዲመለስ፣ መልካም ገፅታዋ ተጠብቆ እንዲቆይ ለማስቻል ድርጅቱ ከመንግሥትና ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሠራም አረጋግጣለች።
እንደ መውጫ
አስጎብኚ ድርጅቶችና የጉብኝት መሪዎች የቱሪዝም ዘርፉ የጀርባ አጥንት መሆናቸው ይነገራል። ድርጅቶቹ የአንድ ሀገር ባህል፣ ተፈጥሮ፣ ታሪክና ቅርስ በቱሪስቶች አይን ውስጥ እንዲገባ ዋናውን ድርሻ ይወስዳሉ። የጉብኝት እቅድ መንደፍ፣ ማረፊያ ቦታዎችን ማዘጋጀት፣ ጎብኚው ስለ መስህቦቹ በቂና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ፣ ቱሪስቱ ምቾት ተሰምቶት ቆይታውን እንዲያራዝም ተፅእኖ መፍጠር የእነዚህ አስጎብኚ ድርጅቶችና የጉብኝት መሪዎች (Tour Guide) ሃላፊነት ነው።
ለዚህም ነው መንግሥት መዳረሻዎችን ከማልማት፣ ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቦታዎችን ከመጠበቅ ባሻገር ኢንዱስትሪውን ከሚያንቀሳቅሱ መሰል ድርጅቶች ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለበት የሚታመነው። መንግሥት በተለይ አቅማቸው እንዲጎለብት፣ መዋቅራዊ አደረጃጀታቸው ጠንካራ እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት የዘርፉ ምሁራን ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም