የኢትዮጵያን እድገትም ሆነ ውድቀት የሚወስኑ ሁለት ዋነኛ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ገድቦ ኃይል ማመንጨት አንዱ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የባህር በር ጉዳይ ነው፡፡ሁለቱን በተናጥል እንመልከታቸው፡፡
በዓለም ላይ ወደ 276 የሚጠጉ ድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አሉ። እነዚህን ወንዞች 145 የሚሆኑ ሀገራት ይጋራሉ። አንዳንድ ሀገራት ወንዞቹን የሚመለከት ሕግ አላቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የጋራ የውሃ አጠቃቀም ሕግ የላቸውም። ነገር ግን ሕጉ ያላቸው ሀገራት ውሃን ዘላቂና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ።
ወደ እኛ ጉዳይ ስንመጣ ግን በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ በርካታ መሰናክሎች እና እልህ አስጨራሽ ክርክሮች ሲደረጉበት ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከ86 በመቶ በላይ የናይል ወንዝ ምንጭ ብትሆንም በቅኝ ግዛት ውሎች የተነሳ መብቷ ለዘመናት ተጥሶ ኖሯል፡፡ ከ86 በመቶ በላይ የውሃ ባለቤት እየሆነች 1 በመቶ እንኳን የመጠቀም መብት አልነበራትም፡፡
ግብጽ እና ሱዳን የ1929 እና የ1959 የቅኝ ግዛት ውሎችን ምክንያት በማድረግ ከቀሪዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ግብፅና ሱዳን የፈረሙት የቅኝ ግዛት ውሎች የዓባይን ውሃ ሀብት ከአሥር የተፈሰሱ ተጋሪ ሀገሮች ለሁለቱ ብቻ የሚያከፋፍል በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ ስምምነት ሆኖ ሌሎቹን ተጋሪ ሀገሮች ለማስገደድ እንደማይችል የሕግ ሊቃውንቱ እና ጸሐፍት ሲወተውቱ ኖረዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ጨምሮ በሁሉም ዘንድ የሚነሳ ነው፡፡
ኢትዮጵያም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር ተከታታይነት ያላቸውን ድርድሮች በማድረግና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አካሄድን በመከተል ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ እግረ መንገዷንም የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ወደ ማገባደዱ በማድረስ መጪውን ብሩህ ተስፋ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይም የናይል የትብብር ማሕቀፍ ወደ ኮሚሽን ደረጃ መሸጋገሩ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ መስሎ የቆየው ውዝግብ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በእኔነት ስሜት እንዲሟገቱበት እና እንዲከራከሩበት እድል የሚሰጥ ነው፡፡
አንዱ ሕጋዊ ማሕቀፍ ሆኖ በቀጣይ የናይልን የውሃ አጠቃቀም ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጠው የናይል የትብብር ማሕቀፍ ነው፡፡
የናይል የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት የዓባይን ውሃ በጋራ፣ በእኩልነትና ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ውሃውን መጠቀምና አብሮ መንከባከብ የሚያካትትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩባቸውን መርሖችን ጭምር ያካተተ ማሕቀፍ ነው። ይህም በአሥራ አንድ ሀገራት መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው።
ጉዳዩን የኢትዮጵያ መንግሥት የቅርብ ክትትል ያደረገበት በመሆኑ የተሳካ እየሆነ መጥቷል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን በሚያገኙበት አጋጣሚ የውሃ ሀብትን በጋራ ማልማትና መጠቀም የሚቻልባቸውን መንገዶች ያነሳሉ። ይህም የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ ሥራ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ ቀድማ ማሕቀፉን ያጸደቀች ሲሆን ከዛ በኋላ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋዳንዳ ገብተውበት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ የመጣውም በጋራ ለመልማት ካለ ፍላጎት አንፃር ነው። በቅርቡ ደግሞ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን በምክር ቤቶቻቸው አጽድቀውታል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ለዘመናት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የላይኛው ተፋስስ ሀገሮች ከውሃው በፍትሃዊነት የመጠቀም መብታቸውን ከማረጋገጡም ባሻገር ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ስታደርገው የነበረውን ፍጥጫ ሌሎች ሀገራት እንዲቀላቀሉና ክርክሮችንም የሚያካሂዱት ሀገራት ሳይሆኑ ኮሚሽኑ እንዲሆን ያስችላል፡፡ ይህ ማለት ጉዳዩ የኢትዮጵያ እና የግብጽ ብቻ ሳይሆን የ11ዱም ሀገራት ጉዳይ እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ በአጠቃላይ የናይል ትብብር ማሕቀፍ ወደ ኮሚሽን ማደጉ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይዞ ይመጣል፡፡
የመጀመሪያው እና ዋናው ነገር የናይልን ውሃ በትብብር ለመጠቀምና ለማልማት ያስችላል፡፡ በቅኝ ግዛት ውሎች ውሃውን ከመጠቀም ተገለው የነበሩ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ውሃውን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት ይጎናጸፋሉ፡፡
የናይል የትብብር ማሕቀፍ ወደ ኮሚሽን ደረጃ ማደጉ በአጠቃላይ በተፋሰሱ ሀገራት ዘንድ የሚታየውን አለመግባባት እና ውዝግብ የሚያረግብ ይሆናል፡፡ የዓባይ ግድብ ጉዳይ ከሶስቱ ሀገራት እና አህጉር አልፎ ዓለም አቀፍ መወያያ አጀንዳ እስከ መሆን ደርሷል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም በጸጥታው ምክር ቤት የታየ አነጋጋሪ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡
ይህ ጉዳይ ከባህሪው በላይ ተለጥጦ ዓለም አቀፋዊ የጸጥታ ችግር ጭምር ተደርጎ ከመወሰዱም በላይ የአንዳንድ ሀገራት መሪዎች ጭምር በቦንብ እንዲመታ ምክር እስከ መስጠት ደርሰዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ውዝግቡ የደረሰበትን ጡዘት የሚያሳይ ነው፡፡
ሆኖም የተፋሰሱ ሀገራት አሁን በደረሱበት ደረጃ ችግራቸውን ሁሉ በኮሚሽኑ በኩል የሚፈቱ በመሆኑ ወደ ሰላምና ትብብር የሚመጡበት አጋጣሚን ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ከዚህም በዘለለ የሚቋቋመው ኮሚሽን የናይልን ውሃ ከብክነት በጸዳ መልኩ በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ስትራቴጂ ያወጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የናይል ወንዝ የአፍሪካን 1/10 የቦታ ስፋት የሚሸፍን ነው፡፡ አስራ አንድ ሀገራትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተፋሰሱ ሀገራት ተብለው ይጠራሉ፡፡ አጠቃላይ በዚህ ቤዚን ውስጥ እስከ 300 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን የዚህ ወንዝ ልማት በቀጥታ ከነዋሪዎች ሕይወት መሻሻል ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
በአጠቃላይ የናይል የትበብር ማሕቀፍ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ኢትዮጵያ በፍትሃዊነት መርህ የዓባይን ውሃ መጠቀም ብቻ ሳይሆን የማልማትም ሥራ እያከናወነች ነው። ከዚህም ባሻገር የወንዙን ጤናማ የፍሰት ሂደት ለመጠበቅና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለሁሉም ሀገራት በቂ ውሃ እንዲኖር በማሰብ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ላይ ትገኛለች፡፡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለውሃ መጠን መጨመር ጉልህ ሚና አለው። ችግኞች በተተከሉ ቁጥር አካባቢ ላይ የሚደርሰውን የመሬት መራቆት ይቀንሳል። የደን ሽፋንን ያሻሽላል። የግድቦችንም እድሜ ያረዝማል። የተፋሰሱ ሀገራትም በቂ ውሃ በዘላቂነት ማግኘት ይችላሉ፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ በተከለቻቸው ከ40ቢሊዮን በላይ ችግኞች ውስጥ ወደ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የሚሆነው የተተከለው በዓባይ ተፋሰስ ነው። የዓባይን ውሃ በማልማት የሚመጣው ጠቀሜታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮችም ጭምር ጠቀሜታው የጎላ ነው። ይህም ጉልህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የናይልን ውሃ በፍትሃዊነት የመጠቀም ፍላጎቷን የሚያመላክት ነው፡፡
ሁለተኛው የኢፍትሃዊነት መገለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ ከባህር በር የራቀችበት ሁኔታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባህርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች፡፡ 1ሺ800 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባህር ይዞታ በቁጥጥሯ ሥራ ያኖረችና ለወጪና ገቢ እቃዎች ሁለት ወደቦች የምታስተዳደር ሀገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ውጭ ቀይ ባህርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ አይቻልም ነበር፡፡
ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትወገድ ተደርጓል፡፡ ለዘመናትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ምንም ድርሻ እንዳልነበራት ሆን ተብሎ በተሰራጨው ትርክት ኢትዮጵያና ቀይ ባህር ተቆራርጠው ኖረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከሥነ ልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ለበርካታ መሠረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትዮጵያ ሚና አሽቆልቁሏል፡፡
በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሰራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባህር በር ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባህር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ለ27 ዓመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባህር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ እንደገና የባህር ኃይል እንዲኖራት አድርጓል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባህር በር የምታገኝበት አማራጭ ተገኝቷል፡፡ ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ከሶማሊ ላንድ ጋር የባህር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ተፈራርሟል፡፡
ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው፡፡ ቀጠናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ለጎረቤት ሀገሮች ነው፡፡ በተለይም ለቀጠናዊ ግንኙነት የመጀመሪያውን ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት በአስተማማኝ መሠረት የሚቆመው የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ እንደሆነ እና ይኸው ሰላምና መረጋጋት የሚጸናው ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን በማዳበርና የሀገራቱ ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በወዳጅነት፣ በትብብርና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በሚያመጣ መልኩ የተቃኘ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ በመከተል ላይ ትገኛለች፡፡
ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግና መበልጸግ የማይፈልጉ ሀገራት ዘወትር የያዘቻቸው የልማት ዕቅዶች እንዲሰናከሉ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያን ወደኋላ ለመጎተት በርካታ ሴራዎች ሲሸርቡ ማየትም የተለመደ ነው፡፡ ሰሞኑንም የሆነው የዚሁ ሴራ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
የግብጽ፤ የሶማሊያ እና የኤርትራ መሪዎች በአስመራ ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቱ በምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ነው ቢባልም በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን ጉዳይ መንካቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ እንኳን ባይሆን ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ ስለምስራቅ አፍሪካ እና ቀይ ባህር ጉዳይ መወያየቱ የማያስገኘው ፋይዳ የለም፡፡
ይልቁንም ለምስራቅ አፍሪካ መረጋጋት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተች ያለችውን ኢትዮጵያን አግልሎ ሰላምና ልማት አመጣለሁ ማለት ከንቱ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያላት፤ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች እና አስተማማኝ የጸጥታ ኃይል ያላት ሀገር ነች፡፡ ስለዚህም በየትኛውም መስፈርት ይህችን ሀገር ገለል አድርጎ የሚከወኑ የልማትም ሆነ የጸጥታ ጉዳዮች ሁሉ ውጤት አልባ ናቸው፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም