ሮያል ማሪን (የእንግሊዙ ባሕር ኃይል ስፔሻል ፎርስ) ከጀብራልታር ፖሊስ በጋራ በመቀናጀት ባካሄዱት ዘመቻ የአውሮፓ ሕብረትን እገዳ በመጣስ የተጠረጠረ ግሬስ 1 ሱፐር ታንከር የተባለ ግዙፍ ነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከብ ከጅብርላታር ምስራቅ በሚገኘው የውሀ መስመር የፓናማ ባንዲራ እያውለበለበ ሲጓዝ ማገታቸውን ፋይናንሽያል ታይምስ ዘግቧል።
87 የእንግሊዝ ኮማንዶዎች የኢራን ነዳጅ ዘይት ወደ ሶርያ እንደሚያጓጉዝ የተጠረጠረውን ግዙፍ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ያገቱት በምሽት ወረራ ነው፡፡ይህ ድርጊት ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማቲክ ውዝግብ በቴህራንና በእንግሊዝ መካከል እንዲከሰት አድርጎአል፡፡ኮማንዶዎቹ ግዳጃቸውን በጅብርላታር ጠረፍ ከጠዋቱ 2 ሰአት ከፈጸሙ ከሰአታት በኋላ ኢራን የነዳጅ መርከቡን በሕገወጥ መንገድ መታገት እንደማትቀበለው በመግለጽ በቴህራን የእንግሊዝን አምባሳደር ጠርታ አነጋግራለች፡፡፣
ሮያል ማሪን ዘ ግሬስ 1 የተባለውን ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ የከበበው በባሕር ኃይል ሄሊኮፕተርና በቅኝት ጀልባዎች በመታገዝ ከጅብርላታር ፖሊስ ጋር ባደረገው ጥምር ዘመቻ ነው።የእንግሊዝ መንግስት የፓናማ ባንዲራ የሚያውለበልበውና 2 ሚሊዮን በርሜል የመያዝ አቅም ያለው የነዳጅ ጫኝ መርከብ የአውሮፓ ሕብረትን እገዳ በመጣስ ድፍድፍ ነዳጅ ሶርያ ወደሚገኘው ባንያስ በማጓጓዝ ላይ እንደሆነ በቂና አሳማኝ ምክንያት ነበረኝ ማለቱን ዘገባው ያስረዳል።
የተፈጠረው አጋጣሚ በቴህራንና በምዕራባውያን መካከል እንግሊዝ ፈረንሳይ እና ጀርመን ኢራን ከአለም ኃያላን ጋር በ2015 (እኤአ) የተፈራረመችውን የኑክሊየር ስምምነት ለማቆየት ትግል እያደረጉ ባሉበት ሰአት መሆኑ ውጥረቱን አባብሶታል።የአሜሪካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ብቻዋን ከስምምነቱ እንድትወጣ ካደረጉና በኢስላሚክ ሪፐብሊኳ ላይ ተጨማሪ ማእቀብ ከጣሉ በኋላ ኢራን ካለፈው አመት ጀምሮ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደምትገኝ ፋይናንሽያል ታይምስ አስነብቧል።
የተወሰደው ከባድ እርምጃ ቴህራን የነዳጅ ዘይት ወደ ውጭ ለመላክ ያላትን አቅም በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል።እንግሊዝ ፈረንሳይና ጀርመን የዋሽንግተንን ውሳኔና እርምጃ አይደግፉትም። እነሱ የኑክሊየር ስምምነቱን መደገፉን ቀጥለዋል።ኢራን ድፍድፍ ነዳጅ መሸጧን አይቃወሙም።በጅብርላታር የተያዘው የነዳጅ ታንከር ነው፡፡እንግሊዝ ግሬስ 1 የተባለውን ግዙፍ ድፍድፍ ነዳጅ የጫነ መርከብ ያገተችው አውሮፓ በሶርያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ስለጣሰ ነው።በሶርያ ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ አመጹን ለመግታት ለ8 አመታት ጭካኔ የተሞላ ጦርነት አካሂደዋል።
ኢራን ዋናዋ የአሳድ ስርአት የውጭ አጋዥ ስትሆን ለረዥም ጊዜ ለሶርያ ነዳጅ ዘይት በመላክ ትታወቃለች።የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቴህራን የሚገኙት የእንግሊዝ አምባሳደር የነዳጅ ጭነቱ የማን ሆነ የማን ትርጉም የለውም፤ዋናው ጉዳይ በኢራን ላይ ሳይሆን በሶርያ ላይ ማዕቀቡን ማጽናት ነው ብለው መግለጻቸውን ጠቅሶአል፡፡ ኢራን የግሬስ 1 ግዙፍ የነዳጅ መጫኛ መርከብን መታገት የተመለከተችው እንግሊዝ የትራምፕ አስተዳደርን ስራ የመስራቷን ያህል ሲሆን ይህም የኑክሊየር ስምምነቱን ለማዳን የሚደረገውን የዲፕሎማቲክ ጥረት ውስብስብ እንደሚያደርገው ትገምታለች።
ኢራን እንግሊዝ ፈረንሳይና ጀርመን ለኢራን ሪፐብሊክ የኢኮኖሚ ችግር ማቃለያ የሚሆን ተጨባጭ እርምጃ በ60 ቀናት ውስጥ ካልወሰዱ የኒውክሊየር እንቅስቃሴዋን እንደምታሳድግ ገልጻለች።ይህ ቀነ ገደብ የሚያልቀው እሁድ ሲሆን ኢ3 ተብሎ የሚጠራው ቡድን ኢራን በስምምነቱ መሰረት እንድትቀጥል ለማሳመን ተስፋ አድርጎአል።የአውሮፓ ሕብረትና እንዲሁም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አሳድ በሶርያ ጸረ መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በኃይል እርምጃ ከወሰዱበት ከ2011 (እኤአ) ጀምሮ በሶርያ ላይ ማዕቀብ የጣሉ ሲሆን ክስተቱ ወደተራዘመ የሲቪል ጦርነት ተሻግሮ እስከአሁንም ፍልሚያው ቀጥሎአል።
በሶርያ ላይ የተጣለው ማእቀብ የጦር መሳሪያ ሽያጭን፤ ከሶርያ ማእከላዊ ባንክ ጋር መገበያየትን፤ የባለስልጣናት የንግድ ሰዎች ፤የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች የሚያሳድጉ ግለሰቦች ንብረት እንዳይንቀሳቀስ መታገድን ያጠቃልላል።
የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩት የነዳጅ ዘይት ጫኚዎች እንደሚገልጹት ግሬስ 1 የተባለችው ግዙፍ የነዳጅ መጫኛ መርከብ ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ይልቅ የተጣራ የነዳጅ ዘይት በመጫን ጥቂቶቹ ወደ ሶርያ እንደሚሄዱ የሚገልጽ ታሪክ እንዳላት ፋይናንሽያል ታይምስ አትቶአል።
ከባሕር ኃይል ዘመቻዎች ጋር ቁርኝት ያለው ግለሰብ መርከቡን የማገትና የመቆጣጠሩ ሙሉ ውሳኔ መሰረት ያደረገው መርከቡ በመጨረሻ ይደርስበታል ተብሎ በተጠረጠረው በሶርያ በሚገኘው ባንያስ የተባለ ቦታ በሚገኝ የነዳጅ ማጣሪያ ምክንያት ሲሆን ስፍራው በአውሮፓ ሕብረት ማዕቀብ ስር የሚገኝ ነው ሲል መግለጹን ዘገባው ያስረዳል።
ኢራን ከሶርያው የአሳድ መንግስት ጋር ቅርብ ትስስር ያላት በመሆኑ የኢራን ነዳጅ ዘይት ከፍተኛ ገዢዎች በሆኑት ቻይና፤ሕንድና ጃፓን ላይ ገደብ የተጣለ ቢሆንም አብዛኛው የቴህራን ሽያጭ የሚሄደው ወደ ሶርያ ነው።ወደ ሶርያ የሚጫኑት ጭነቶች ለሌሎች ምርቶችና ለኃይል ማመንጫዎች የሚውሉ ናቸው።
የሶርያና የኢራን ስትራቴጂክ ሕብረት ከ1980ዎቹ (እኤአ) ይጀምራል።በዚህ አመት ሶርያ ኢራን ወደ ውጭ በምትልከው ነዳጅ ዘይት ላይ አሜሪካ ማዕቀቡን ማጥበቋ ሀገሪቷን ግጭቱ ከተጀመረ ጀምሮ ወደከፋ ቀውስ እንደሚከታት በመግለጽ አውግዛለች።
የነዳጅ መጫኛ ታንከሮቹ (ሱፐር ታንከርስ) በጠባቡ የስዊስ ካናል ለመጓዝ በጣም ግዙፍ ናቸው ።ይህም ግሬስ 1 ግዙፍ የመጫኛ መርከብ ረዥሙን ጉዞውን በደቡብ አፍሪካ በጅብርላታር በሜድትራንያን ባሕር ውስጥ እንዲያደርግ ያደርገዋል።የመርከብ ደላሎች ግሬስ 1 የኢራንን ቀላል ደረጃ ያለው የነዳጅ ዘይት ድፍድፍ ከገልፉ የካህራግ ደሴት በአፕሪል 7 መጫኑን ከዚያ በኋላ ፉጃኢራህ በተባለ በዩናይትድ አረብ ኢምሬት ምስራቃዊ ጠረፍ እንደቆየ ገልጸዋል።ከቦታው የለቀቀው በእኩለ ቀን ሲሆን በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ አካባቢ በመቅዘፍ ወደ ጅብሪላታር እንደሚያመራ ተስፋ ተደርጎአል፡፡ላለፉት ስድስት ሳምንታት መርከቧ በጣም በዝግታ ነበር የምትጓዘው ሲል አንድ የመርከብ ደላላ ገልጾአል።
አንድ መሰረቱን በጅብሪላታር ያደረገ የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ እንደገለጸው ከሆነ መርከቡ ከረዥም ጉዞው በኋላ መለዋወጫዎችን ለመውሰድ ከወደቡ ውጭ በመቆሙ ተጠርጥሮአል።የታይምስ ዘገባ በበኩሉ የኢራንን ዘይት ወደ ሶርያ ጭኖ ሲወስድ የነበረ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት መጫኛ መርከብ በእንግሊዝ ማሪኖች መያዙ የዲፕሎማሲ ውጥረት ፈጥሮአል ሲል ዘግቦአል።
የብሉምበርጎቹ ቬሪቲ ራትክሊፍ፤ ጁሊያን ሊ እና አርሳላን ሻህላ ያቀረቡት ዘገባ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ተመሳሳይ ነው።የእንግሊዝ ስፔሻል ፎርስ ከጅብራላታር ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ዘመቻ አድርጎ መርከቡን ማገቱን ገልጸዋል።ሶርያውያን ወደ ሀገራቸው ሲጓዝ የነበረው የነዳጅ መርከብ በመታገቱ የሚያደርስባቸው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑ ተሰምቶአቸዋል።
የመርከቡ መታገት ኢራን የደረሰባትን ከፍተኛ ችግር ያሳያል። የኢራን የነዳጅ ዘይት ምርት ባለፉት አመታት በቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በርሜል ያህል ወርዶአል። በአሁኑ ሰአት የታገተው መርከብ የሚገኘው ለጅብርላታር ቅርብ በሆነ በደቡብ ስፔን ጫፍ በቀጥታ ከሜድትራንያን ባሕርና ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ትይዩ በሆነ ቦታ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 4/2011
ወንድወሰን መኮንን