የላቀ ዕድገትን የወጠነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ

በኢትዮጵያ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር ሊናቁ የማይችሉ የኢኮኖሚ ዕድገቶች ተመዝግበዋል። የቅርቡን ማለትም ከ2016 ዓ.ም እስከ 2018 ዓ.ም ይተገበራል ተብሎ የታቀደው ሁለተኛው የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ፤ በ2016 ዓ.ም በሁሉም ዘርፎች የኢኮኖሚ መነቃቃት በመፍጠሩ 8 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል።

ይህንን በተመለከተ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በሚፈትኑ ትልልቅ ችግሮች ውስጥም ሆና፤ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመተግበሯ ባለፈው ዓመት ግብርና በ 6 ነጥብ 9 በመቶ ማደግ ችሏል። የዋና ዋና ሰብሎች ዘርፍ ዕድገትም 7 ነጥብ 8 በመቶ የተመዘገበ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ ዕድገትም ዘጠኝ ነጥብ ሁለት በመቶ ማድረስ ተችሏል። የአገልግሎት ዘርፍም እንዲሁ 7 ነጥብ 7 በመቶ ማደግ የቻለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 8 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

ይህ ዕድገት የተመዘገበውም በኢትዮጵያ ከተከሰቱ ግጭቶች፣ ከኮቪድ ወረርሽኝ የከረመ ተፅዕኖ እና ከአየር ንብረት መዛባት ተፅዕኖ አንፃር ሲታይ ትልቅ ነው። በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ያሉ የሀገራት ጦርነቶች በዋናነት ለዓለም ከፍተኛ የስንዴ ምርትን በማቅረብ በተመሰከረላቸው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነትን ተከትሎ በየሀገራቱ የተከሰተውን የዋጋ ንረት በመቋቋም የመጣ ውጤት መሆኑ ሲታይ እጅግ ትልቅ መሆኑን መካድ አይቻልም። እናም ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሲታይ ኢትዮጵያ የቀረፀችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ብልፅግና ተኪ የሌለው ሚናን እየተጫወተ መሆኑ እሙን ነው።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቀጣዩን የኢትዮጵያን የዕድገት ደረጃ ከፍ እንዲል ከማድረግ ባሻገር፤ ገበያን ማረጋጋት፣ የዕዳ ጫናን ማቃለል እና ገቢን ማሳደግ ላይ እያስገኘ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ)ም በባለሙያዎቹ ያካሔደው ጥናት ይህንኑ አረጋግጧል።

ይህን ተከትሎ ከሰሞኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዓመቱ የትኩረት ነጥቦች ዙሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ላይ እንደገለፁት፤ በተያዘው ዓመት በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ያሉትን ችግሮች በማቃለል 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ አስቀምጠዋል። ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የኢንቨስትመንት እና የንግድ ከባቢን ማሻሻል፤ የዘርፎች ምርታማነት እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እና የመንግሥትን የመፈፀም አቅም ማጎልበት ትኩረት የሚሰጣቸው መሆናቸውን ገልፀዋል።

በእርግጥ የኢኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተ ኢትዮጵያ በምታደርገው ብርቱ ጥረት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የገንዘብ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ የተወሰዱ እርምጃዎች የሚያበረታቱ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ናቸው። በተለይ በቅርቡ የተደረገው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለበርካታ ዓመታት ማነቆ ሆኖ የቀጠለውን የውጪ ምንዛሪ ችግር ለመፍታት እና ኢኮኖሚው ወደ ሚፈለግበት ደረጃ ለማሻሻል የሚረዳ መሆኑም በመታየት ላይ ነው።

ቀደም ሲል ውጪ የሚልኩ አምራቾችን የሚጎዳና ሸቀጥ አስገቢዎችን የሚያበረታታው እና ሀገርን የሚጎዳ አካሔድ፤ በተቃራኒው ሀገርን በሚጠቅም የኢኮኖሚ እድገትንም በሚያረጋግጥ መልኩ መስመር እየያዘ ይገኛል። እርምጃው ኢ-መደበኛ የንግድ አሠራሮችን ለማስቀረት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲሆን፤ በተለይ በሕገወጥ መንገድ የሚፈሱ እና የሚተላለፉ የውጪ ምንዛሪ ሒደቶችን በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እያስቻለ ነው።

ይህ ሂደት ራስን ከመቻል ጋር ተያይዞ መንግሥት ከያዘው አቅጣጫ አንፃር የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች የገበያ ድርሻ ከፍ በማድረግ የገጠመንን የንግድ ሚዛን መዛባት እና የዕዳ ጫናን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል። ለውጪ ኢንቨስተሮችም ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ ይህም የሥራ ዕድልን ከመፍጠር በተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት፤ አምራችና ተጠቃሚን የሚያግዝ እና የሚያበረታታ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ይረዳል።

በተጨማሪ የውጪ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታት ተግባራዊ የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ባንኮች ከዲያስፖራ የሚያገኙትን ገቢ ለማሳደግ፤ ኢኮኖሚያችንን ዘመናዊ ከማድረግ ባሻገር ድጋፎችን ለማግኘት እንደሚረዳም ታውቋል። ይህንን በተመለከተ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴም እንዳሳወቁት፤ በቀጣይ ዓመት ከልማት አጋሮች እና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢኮኖሚያችንን የሚደግፍ እና ለዕድገታችን ማስፈንጠሪያ 27 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረውን በሦስት ዓመት የሚተገበረው የስድስት ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ ድጋፍ ለመተግበር የሚያስችል ዕድል መገኘቱንም ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚው ማሻሻያውና ይህንንም ተከትሎ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተለይም የውጪ ምንዛሪውን በተመለከተ የተወሰደው መፍትሔ፤ ኢትዮጵያ ከቀረው የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን እና እያደገ የመጣውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚያስችላት ተጨባጭ ውጤት ማግኘት ተችሏል።

በሀገር ውስጥም የኢኮኖሚው ማሻሻያውን ተከትሎ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መፍጠር የሚገባ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱ እንዳመላከቱት፤ ይበልጥ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ኢንቨስትመትን በሚያበረታታ መልኩ ከባቢ ሁኔታን ማሻሻል ያስፈልጋል። በአገልግሎት ዘርፍ የሚታየውን ሰፊ ኢ-መደበኛነት በመቀነስ እና ወደ መደበኛነት በመቀየር፣ በፋይናንስ ዘርፍ የታየውን መነቃቃት ማስቀጠል ይገባል። እነዚህን በትክክል ማድረግ ከተቻለና ወደ ጠንካራ የዲጂታል አገልግሎት ማምራት ላይ ትኩረት ከተሰጠ፤ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ይበልጥ ማሳደግ የማይቻልበት ሁኔታ አይኖርም።

በአጠቃላይ ያደሩ እና የተወሳሰቡ ችግሮች አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድሩም፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓት በመተግበሩ ኢኮኖሚው 8 ነጥብ 1 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። የተወሳሰቡት ችግሮች ባይኖሩ ምን ያህል ዕድገት ሊመዘገብ እንደሚችል ሲታሰብ አጓጊ ውጤት እንደሚመጣ መተንበይ ከባድ አይሆንም። ይህ አጓጊ ውጤት በትክክል መገኘት እንዲችል፤ የተወሰኑ ተቋማት እና የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆኑ ባለሀብቶች እና መላው ኢትዮጵያውያን የየራሳቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል።

ፌኔት (ከመሳለሚያ)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You