ሰንደቅ ዓላማ ሀገር ወካይ፣ ሕዝብ ገላጭ የማንነት መልክ እንደሆነ የሚጠፋው አይኖርም:: በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የተቀለመው ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሶስት ገላጭ እሳቤዎችን ይዞ ከትላንት ወደዛሬ መጥቷል ወደ ነገም ያዘግማል:: ቀይ የጀግንነት፣ የብርታት ተምሳሌት ሆኖ፣ ቢጫ የሰላም፣ የፍቅር ምልክት ሆኖ አረንጓዴን በአረንጓዴና በልምላሜ ከትበን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሶስት ዘመን ተሻጋሪ ቀለሞች ስር አሳርፈን ብዙ ተጉዘን እነሆ ዛሬ ላይ ደረሰናል::
በየዓመቱ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮም ‹‹ ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ከፍታ!›› በሚል መሪ ቃል እና መሃላ ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ ተከብሯል:: አዲስ ዓመት በገባ ሰሞን የሚከበረው ይህ በዓል ዓመቱን በኢትዮጵያዊ ስሜት፣ በአብሮነትና፣ በወንድማማችነት እንድናሳልፍ እድል የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር የቀድሞ አባቶቻችን ለሀገርና ሕዝብ የከፈሉትን መስዋዕት የምናስብበትም ጭምር ነው::
በመሪ ቃልና በመሀላ መከበሩ ልዩ ድባብን ከማስገኘቱ ጎን ለጎን ለባንዲራ ያለንን ክብር ከፍ እንድናደርግ፣ የተከፈለልንን ዋጋ እንድናውቅ፣ በአብሮነት እንድንጓዝ፣ ቃል ወደተግባር ተቀይሮ ሀገራችንን በልማትና በሰላማዊ መንገድ እንድንመራ እድል የሚሰጥ ነው:: እኛ ኢትዮጵያውያን ብሎ የሚጀምረው የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን መሀላ በይዘቱና በቁም ነገሩ ፍሬ ያለው፣ በአንድነት ስለአንድነት እንድንተጋ አጽንኦት የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያና ከፍታዋ ላይ ያተኮረ መሆኑ ከቃለ መሃላው መረዳት ይቻላል::
‹እኛ ኢትዮጵያውያን…ድህነትና ኋላቀርነትን አስወግደን፣ ኢትዮጵያችን በልማትና በዲሞክራሲ ጎዳና ውስጥ የሕዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ትሰለፍ ዘንድ፣ የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ወደማይቀለበስ ደረጃ ለማድረስ፣ በየጊዜው እያጋጠሙን ያሉ ችግሮችን በማስወገድ፣ በአንድነትና በጋራ ስሜት፣ አብሮ በመቆም በየዓመቱ በመንግሥት ትኩረት አግኝተው የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶቻችንን ለማሳካት፣ በሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃል እንገባለን› የሚል ነው::
መሀላ እንደ ቃል የእምነት እዳ ነው:: ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ እንደሚባለው ሀገርኛ ሥነ-ቃል ዋጋው ከፍ ያለ ነው:: ስለሀገር ሲሆን ደግሞ ትርጉሙ ከዚህም በላይ ይገዝፋል:: እኛ ኢትዮጵያውያን ለቃል የተለየ ቦታ የምንሰጥ መሆናችን በብዙ አጋጣሚዎች የታየ እውነታ መሆኑ የሚያጠራጥር እንዳይደለ ብዙ ማረጋገጫዎች አሉ:: ከሁሉም በላቀውና የሁላችንም የክብርና የሉዓላዊነት ቀለም በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ፊት ቆመን የገባነው መሀላ ጥልን በፍቅር፣ ክርክርን በውይይት የሚሽር የአብሮነት ስሜትን ከመጫሩ እኩል ለሀገራችን ያለ ነው እኛ እንደሆንን፣ ከእኛ ብርቱ ትስስርና ጉርብትና ሌላ ነፃ አውጪ እንደሌላት የሚጠቁምም ነው::
እንዲህ ባለው ሕዝባዊ መሃላ በመታገዙ እስከ ዛሬ ከተከበሩት የሰንደቅ ዓላማ ቀኖች የዘንድሮው ለየት እንደሚል አምናለሁ:: ለተግባር በሚያተጉ አንቂና አብቂ መሀላዎች ችግሮቻችንን ካልተጋፈጥናቸው አስቸጋሪ የመሆናቸው ነገር ሳይታለም የተፈታ ነው:: በአንድ ዓመታዊ ክብረ-በዓል ወይም ወደፊት ለምንተገብራቸው ሀገራዊ ጉዳዮች አበባ ስናስቀምጥ፣ ሻማ ስናበራ፣ ሪቫን ስንቆርጥ አብረን እንዲህ ያሉ የትጋትና የንቃት መሃላዎችን መጨመራችን አዋጪነቱን የገዘፈ ያደርገዋል::
የቃል ትንሽ፣ የመሃላ መናኛ የለውም:: ሁሉም ቃሎች ከአንደበታችን እስከ ወጡ ድረስ ባለመከበራቸው በፈጣሪና በህሊናችን በኩል ተጠያቂ ሊያደርጉን ኃይል አላቸው:: ቃል ስንገባና መሀላ ስንፈጽም ለዛ ቃልና መሀላ ተገዢ በመሆን ነው:: በዛሬው እለትም የገባንው የመሃላ ቃል የመላው ኢትዮጵያውያን የእምነት እዳ ሆኖ የሚጠራ ነው:: ቃላችንን በማክበር፣ ለሀገራችን በመልፋት፣ ስለአብሮነት ዋጋ በመክፈል፣ ድህነትና ኋላቀርነትን በመፋለም፣ ልማትና ዲሞክራሲ፣ ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ጠጠር በማዋጣት መሀላችንን በተግባር ማረጋገጥ አለብን::
የባንዲራ ቀንን ብቻ አይደለም በሀገርና በማህበረሰብ ስም የሚከበሩ እንደ ዓድዋ፣ እንደ አርበኞች ቀን፣ እንደ ሰማእታት ቀን ያሉ የድል ቀኖችን እንዲህ ባለው መንፈስ በቃልና በመሃላ፣ በብሔራዊ መዝሙርና አንድነትን በሚያጠነክሩ የእርስ በርስ የበጎ እሴት ልውውጥ ብናከብራቸው ጥሩ ውጤት እንደምናመጣ ባለተስፋ ነኝ::
የተለማመድነው በአበባና በሻማ ማብራት ዘክሮ ማለፍ ነው:: ትርጉሙ እንዲገባን፣ ዓላማውን እንድንረዳ፣ ለትውልዱ ያለው ፋይዳ እስከ የት እንደሆነ ለማወቅ ቀለል ብለው ለየት ያሉ የአከባበር ሥነ ሥርዓቶች ዋጋቸው ብዙ እንደሆነ አምናለሁ:: ጥሩ የሆኑና በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ መንፈስን የሚፈጥሩ እንዲህ ያሉ የትስስር ገመዶች ለመቼም እንዳይበጠሱና እንዳይላሉ የጠበቁ ናቸው::
አንዳንድ የልጅነት ጥበቦች አሉ በምንም የማይከለሉ፣ ዘመን ደፍሮ የማይሽራቸው፣ ጊዜ ችሎ የማይደፍራቸው ሁነቶች:: ልጅነት እንደክታብ ነው በሕይወት በፈር ላይ የሚውል:: አፍላነት እንደ ዶቃ ነው ቅጭልጭልታው እስከ እድሜ ጥግ የሚከተል:: ዛሬም ድረስ አልረሳ ብለው ከወጣትነትና ከጉልምስና ከእርጅናም አፋፍ ያልጠፉ፣ ትናንትናዎችንን ያጣፈጡ የብዙ ትዝታዎች ባለቤቶች ነን:: ከነዚህ ትዝታዎች መሀል አንዱ ደግሞ የሰንደቅ አላማ የአከባበር ትዝታ ነው::
በልጅነቴም ሆነ በአሁኑ የወጣትነት እድሜዬ እንደ ባንዲራ ክብር የተገባው ነገር አይቼ አላውቅም:: ለምን የሚለው ጥያቄ እስከሆነ ልጅነቴ ድረስ መልስ አልባ ነበር:: እየሰነበትኩ ስሄድ ነው እኔን፣ ከመልክና ወዜ ጋር ቀልሞ የያዘ ገጸሰቤ እንደሆነ የተረዳሁት:: በትምህርት ቤት የባንዲራ ደፍ ስር በክብር፣ በሥርዓት፣ በጨዋነት የቆምነው፣ ድምጻችንን አዝልገን ለመቼም ከሆድ በማይጠፋ ህብረ ዝማሬ የተቀኘነው የክብር ወግ ዛሬም መታወሻዬ ነው::
ባልተንሻፈፈ አቋቋም ቀጥ ብለን ቆመን፣ እጃችንን በትከሻችን አቅጣጫ ያለውልጋዴ ዘርግተን፣ በሥርዓትና በግብረገብነት ስንታይ ያ ዘመን የት ሄደ እንድል ያደርገኛል:: በትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ፊታውራሪነት ሰልፋችንን አስተካክለን፣ እጆቻችንን ከፊትና ከኋላ በቆሙ ወዳጆቻችን ትከሻ ላጥ ጥለን፣ ስለኢትዮጵያዊነት ያዜምነው፣ ስለ ሀገር ፍቅር የዘመርነው ዝማሬ የሁልጊዜ ናፍቆቴ ነው::
የዜግነት ክብር ስንል በጽኑ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ አንዳንዴም በእንባ ታጅበን የተቀኘነው ፊተኛ ጥበባችን፣ በአንድ ስም፣ ለአንድ አላማ ‹‹ኢትዮጵያችን ኩሪ እኛም ባንቺ እንኩራ›› ስንል ያስተጋባነው የመንፈስ ከፍታ በዚህ ትውልድ ላይ እንዲያቆጠቁጥ እመኛለሁ:: ልብን ሰቅዞ በሚይዘው ብሔራዊ መዝሙር ታጅበን ባንዲራ ሲወጣና ሲወርድ ከምንሆነው መሆን በላይ ፊታችን ላይ ያለው የስሜት ልህቀት ነበር እጅጉን የሚያስገርመው:: ትላንትን ወደ ዛሬ አምጥቶ ወደ ነገም ማራመድ ቢቻል ያን መንፈስ፣ ያን ማንነት፣ ያን ህብረ ብሔራዊነት፣ ያን ሀገር ፍቅር ስሜት፣ ያን ኢትዮጵያዊነት፣ ያን ወንድማማችነት፣ ያን ትቅቅፍ እመልሰው ነበር:: ርግጥ እንደ በፊቱ አይሁን እንጂ ያን መሳይ መልክ አሁንም አለ::
አንዳንድ ስጦታዎች የሕይወት ዘመን ሀብቶች ያህል ናቸው:: ሀገር ለሕዝብ፣ ሕዝብ ለትውልድ ሊሰጡት የሚገባ ትልቁ ስጦታ ወንድማማችነትን ነው:: አባቶቻችን በሀገር ፍቅር ስሜት ለባንዲራቸው ሞተው አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን ከነፃነትና ከሉዓላዊነት ጋር ሰጥተነዋል:: ይሄ በምንም የማይመነዘር፣ ከፊተኞቻችን የተቀበልነው፣ ለውድድር ሚዛን ላይ የማይወጣ ለእያንዳንዳችን ድንቅ ስጦታችን ነው:: እኛም እንደ ፊተኞቻችን ሁሉ ለኋለኞቻችን ልንሰጠው የሚገባ እንደ ፍቅርና፣ ይቅርታን የመሰሉ ነፃ አውጪ መርሆች ሊኖሩን ግድ ይላል::
ተሰጥቶን ሀገርና ሕዝብ ሆነናል:: ተሰጥቶን ባለታሪክና ፊተኞች ተብለናል:: እንደተቀበልነው ሁሉ ለሚመጣው የምንሰጠው የመልካም እሴት ዋጋ ሊኖረን ይገባል:: መጪው ትውልድ ባለፈው እንዳይጠራ የራሳችንን ጀብድ ልናስቀምጥለት እንደ ዜጋ ግዴታ አለብን:: የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበር ትርጉሙም ይሄ ነው:: የተቀበልነውን በመስጠት እና ተንከባክቦ በማኖር ትውልድ መፍጠር፣ ሀገር ማስቀጠል ላይ ያተኮረ ነው::
ሀገር ማለት ባንዲራ ናት:: ሕዝብ፣ ትውልድ፣ ታሪክ፣ ቅርስና ማንነት በዚህ ሰንደቅ ዓላማ በኩል ነፍስ የዘሩ ናቸው:: ትላንት ዛሬና ነገ ሳይቀሩ የነበር ትውስታቸውን ሽረው ውዳዴን የሚያሳዩት እንዲህ ባለው ክብረ በዓል እለት ነው:: መቶ ሃያ ሚለዮን ሕዝብ፣ ከበዛና ከገዘፈ ህብረ ብሔራዊነቱ ጋር፣ ከወግና ልማዱ እንዲሁም ከማንነቱ ጋር በዓለም አደባባይ የሚታየው በወከለው ሰንደቅ ዓላማው በኩል ነው:: ራስን በኳለ ሁኔታ ብዙኀነት ከነሙሉ ክብሩ ማንነቱን የሚገልጥበት ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙርን የመሳሰሉ ከሕዝብ መንጭተው ሕዝብን የሚያረሰርሱ የጋራ ታሪኮች እንደ በጎ ማህበራዊ እሴቶች የሚወሰዱ ናቸው::
በፖለቲካው ምህዳር ትልቁ የሥልጣን እርከን ባንዲራ ነው:: ቀላል ይመስላል አይደል? ቀላል ግን አይደለም:: ባንዲራ ስላችሁ ጨርቁን እያልኩ አይደለም:: ከጨርቁና ከቀለሙ ባሻገር ስላለው ታላቅ እውነታ መናገሬ ነው:: ስለወከለው ሕዝብና ስለቆመለት ዓላማ፣ በሞትና ሕይወት ኑባሬ ስር ስለቆመ የቃል ኪዳን አደራ ማውራቴ ነው:: ኢትዮጵያዊነትን ስለሳለው፣ ብዙኀነትን ስላቀፈው፣ ትናንትን ከዛሬና ከነገ ጋር ስላስተሳሰረው ገድሉ መናገሬ ነው:: የሶስት ሺ ዘመንን የታሪክና የሥልጣኔ፣ የክብርና የሉዓላዊነት፣ የፍትህና የነፃነት ብኩርናን ማለቴ ነው::
በአጭር ቃል የባንዲራን ግዝፈት ለመረዳት ሀገርና ሕዝብ ያሉበትን ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነት መመልከት ብቻ በቂ ነው:: በትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ ክብርና ማንነት በሚንጸባረቅባቸው በየትኞቹም ሁነቶች ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚውለበለበው ሰንደቅ ዓላማችን ነው:: በፖለቲካው ዓለም በሹም ሽረት ወቅት የሚደረግ የሥልጣን ርክክብ እንኳን ባንዲራ ሰጥቶ በመቀበል ይሁንታ የሚያገኝ ነው:: ታላቅ ትርጉም ባላቸው የፖለቲካ ጫፎች ላይ በከፍታና በዝቅታ ተሰቅሎ የሕዝብን ስሜት ከመግለጽ አኳያም ሚናው የላቀ ነው::
በእውነቱ ከያዘው የሶስት ቀለም ንድፍና ከገባን ውስን ትርጉሙ በቀር ስለ ሰንደቅ ዓላማ የገባን አይመስለኝም:: ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያዊነት ሌላኛ ስሙ ነው:: እኔን ከሌላው፣ ሌላውንም ከኔ ጋር አመሳስሎ ኢትዮጵያዊ የሚል የጋራ ስም ያገኘንበት የክብር ጌጣችን ነው:: ባንዲራን ማወቅ ሀገርን ማወቅ ነው:: ሰንደቅ ዓላማን መረዳት ኢትዮጵያዊነትን መረዳት ነው:: አባቶቻችን ለባንዲራ ተዋደቁ ስንል ለሀገርና ሕዝብ ተዋደቁ እያልን መሆኑ የሚያሻማ ባይሆንም የመጨረሻው የእውነት ጥግ ግን ለህብረ ብሔራዊነት ዋጋ መስጠት የሚለው ነው::
ንቁ ትውልድ በሌሎች ሀገራት ተጽዕኖ ሳይሆን አባቶቹ ባስቀመጡለት በራሱ እሴት በኩል የሚፈጠር ነው:: የተሰጠንና አባቶቻችን ያስቀመጡልን ደግሞ ከጥላቻና ከዘረኝነት የራቀ፣ ስለሌላው ግድ የሚለውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው:: ባንዲራ በሚለው ስም በኩል ከፊተኞቻችን የተሰጠን የክብርና የታላቅነት ቀለም አለ:: የተሰጠንን ከዚህም ከዚያም ከምንሰማው አሉባልታ ጋር እያመዛዘንን ውለታ በል እየሆንን ያለን ጥቂቶች አይደለንም:: ከሁሉም የሚበልጥ እውነት ቢኖረን በሰንደቅ ዓላማ በኩል የሚገለጥ ሀገራችን እና ሕዝባችን ነው::
ሰንደቅ ዓላማችን ህብረ ብሔራዊ ድላችን ሆኖ ብዙ ሰንብቷል:: ነፃነትና እኩልነት፣ ጀግንነትና ሉዓላዊነት መልካቸውን የተዋበች፣ የቆራጥ ስም ማንነት ቀለም ነው:: ኢትዮጵያዊ ስንሆንና ስንባል በዚህ የሶስትዮሽ ቀለም በኩል ተንጸባርቀን ነው:: ቃላችንን ወደተግባር፣ መሀላችንን ወደእውነታ በመቀየር እንደ መንግሥትና እንደ ዜጋ ኃላፊነታችንን በመወጣት አጋርነታችንን ማሳየት ከሁላችን ይጠበቃል::
የሀገር ፍቅር መገለጫ ከሆኑት ውስጥ ቃልን ማክበር እና መሀላን መፈጸም ዋነኞቹ ናቸው:: ምናልባት እንደ ሀገር የከሰርንባቸውንና አልመን ያልደረስንባቸውን አንዳንድ ትልሞቻችንን መለስ ብለን ካስተዋልን ከቃል የዘለለ ምንም ነገር አለማድረጋችን በቀዳሚነት የሚነሳ እውነታ ይሆናል:: ካለፈው ተምረን ሰንደቅ ዓላማችን ፊት፣ ስለሀገራችን፣ ስለነጋችን የገባንውን መሀላ በመፈጸም የተሻለ እምርታ ማሳየት እንዳለብን በመጠቆም ላብቃ:: ቸር ሰንብቱ::
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም