አዲስ ዘመን ድሮ

የዛሬው “አዲስ ዘመን ድሮ” በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ከመጽሐፍት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ “አዲስ ዘመን” ልክ እንደ ዛሬው ሁሉ፣ ድሮም ለንባብና ጽሕፈት፤ እንዲሁም ለድርሰትና ደራሲ፤ በአጠቃላይም ስለ መጽሐፍት፣ ስለ ሥነእውቀትና ፋይዳው ልዩ ትኩረትን ሰጥቶ እንደ ነበር እንመለከታለን። በተለይም የመጀመሪያው ጸሐፊ (ታኅሣሥ 27 ቀን 1952 ዓ•ም) ምን ያህል ያኔ ላይ ሆነው የእኛን ዛሬ እንደተመለከቱ ለተገነዘበ ልባም ጉዳዩ ተዓምር ቢያሰኝ የሚገርም ሊሆን አይችልም። መልካም ንባብ።

“መጽሐፍ የተጻፈው እኛ ልንጠቀምበት ነው”

ተመልካችነት ያለው ሰው ሁሉንም ማስተዋልና መመልከት እንደሚጠቅመው ይገነዘበዋል። ይልቁንም መጽሐፉ መመልከትን ከሁሉ ያበልጠዋል።

አንድ ታላቅ ደራሲ ጥሩ አስተያየት ያለበት መጽሐፍ አዘወትሮ የተመለከተ እንደ ሆነ ከኔ በላይ ሌላ አዋቂ የለም የሚል ሃሳቡን ያሻሽልበታል። ከሰው በላይ ሰው እንዳለ የሚታወቀው ከድርሰት ወይም ከመጽሐፍ በላይ የሆነውን የድርሰት መጽሐፍ በመመልከት ነው።

የዓይን ምሳ፣ የመንፈስ ምግብ፣ የልብ ስቴ ወይን፤ የጥሩ ድርሰት ምንጭ ከሆነ መጽሐፍ በቀር ሌላ ምን ይገኛል? ቅዱስ ጳውሎስ “የተፃፈው ሁሉ እኛ ልንመክርበትና ልንገሠፅበት ተፅፏል” እንዳለው መጽሐፍት ባይኖሩ ምክርና ተግሳፅ የሚሆኑ፤ ጥበብና እውቀትን የሚገልፁ፤ የሰው ልጆችን የሚያጨዋውቱ የተሻሉ ነገሮች ባልተገኙም ነበር።

አዲሶቹም የጥበብ መጽሐፍት፣ የድሮዎቹም የቅዱስ መጽሐፍና የታሪክ ዜናዎች የሰውን አዕምሮ ለመክፈት ሃሳብን በማትባት ምን ያህል እንዳገለገሉ የመጽሐፍት ወዳጆች ሁሉ አይዘነጉትም።

“ሰው በሕይወቱ ሳለ ደስ ከሚያሰኘውና ከሚያደርገው መልካም ነገር በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ” ሲል ቃሉ መጽሐፍ ሆኖ የቀረበለትና መጽሐፉ በስሙ ሲጠራለት የሚኖረው ብልሁ ሰለሞን የተናገረው፤ ከመልካም ነገር የበለጠ ሌላ የመልካም መልካም የሆነ ምን መልካም ነገር ኖሮ ነው? በፍቺው አንባቢዎች ይደርሱበታል።

ከዚህም ዝቅ ብሎ “እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘለአለም እንዲኖር አወቅሁ” ካለ በኋላ በዚሁም ላይ “ይጨመርበትም፣ ይጎድልበትም ዘንድ አይችልም” ሲል ይኸው ፈላስፋ ንጉሥ የተናገረው የሰውን ሃሳብ በምን ግምት ላይ ለመጣል አስቦ ነው?። የዚህም ፍጆታ ለአንባቢው ተለቆለታል።

ይልቁንም ይኸው ፈላስፋ ንጉሥ “እንጀራህን በውሃ ላይ ስደድ (ጣል)። ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህና” ያለው ከመቸውም ይልቅ ፍቺውን ያገኘው ዛሬ እንደ ሆነ መረጃው ተገኝቷል።

በአሁኑ ክፍለ ዘመን ወንዞችን እየገደቡና ወራጆችን እያገዱ፣ ባሕሮችን በአስተላላፊ መዘውር እየጠለፉ በመስኖ ተግባር የሀብት እንጀራን ማግኘትና የመብራት ኃይሎችን መብራት መዘርጋት የሚመለከተው” እንጀራህን በውሃ ላይ ስደድ፣ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህና” የተባለውን የድሮውን የሳይንስ ሊቅ አሳብ ነው።

የሚያስታርቃቸው እያጡ ነው እንጂ የሃይማኖትና የሳይንስ መጽሐፍት ምንም አይጣሉም። ዙረው ተመልሰው የሚያስረዱት የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ ለጥበበኞች ጥበብን ገላጭ ነው።

“ነፋስ የሚጠብቅ አይዘራም፤ ደመናም የሚመለከት አያጭድም” እንደሚባለው፣ የሳይንስን መጽሐፍ የሚጠራጠር፣ ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተባብል ከሁለት ዛፍ የወደቀ ይሆንና ባንዱም ሳይጠቀም ይቀራል።

የመጨረሻው የሀሳብ ውሳኔ “ከማለዳ ጀምረህ ዘርህን ዝራ፣ በማታም ጊዜ እጅህን አትኮርኩም” የተባለውን በመገንዘብ አሳብን ከምርመራ፣ እጆችን ከሥራ መሰብሰብ እንኳን ለአሁኑ ጊዜና ለመቸውም ትውልድ ተገቢ አይደለም።

ከመጽሐፍ ወዳጆች አንዱ

(አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 27 ቀን 1952 ዓ•ም)

* * * *

በመጽሐፍ ያለው እየታሰበ ሲሄድ በመጽሐፍ የሌለ እየተዘነጋ በመሄዱ ምክንያት ለታሪክ አወራረስና ለቃላት ጥናት ያለ መጽሐፍት ምንም ሊደረግ አይቻልም።

“ዘጻሐፍኩ ጾሐፍኩ” እንደ ተባለው ያለፉት ሊቃውንቶች የጻፉትን ጽፈዋል። የዛሬዎቹም የሚጽፉትን ይጽፋሉ።

ነገር ግን በስመ ሰው በእውቀትና በሊቅነት ወይም በጀግንነትና በሌላም ስመ ጥሩነት ሁሉ እኩል እንዳይደለ በስመ መጽሐፍም ሁሉ እኩል አይደለም።

እንደ እውነቱ የሆነ እንደ ሆነ የመጽሐፍ መጽሐፍ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ያለጥርጥርና ያለውልውል መጽሐፍ ነው ሊባል ይችላል።

ሰው አዲስ እየመሰለው በአሁኑ ዘመን ሁናቴ ሲደነቅና ሲገረም ይታያል። ባነጋገር እየተለያየና ባመራመር እየተሳሳተ ነው እንጂ። ሳይንስ ለሚባለው ዘመናዊ የጥበብ ምንጭ መሠረቱ ይኸው መሆኑ የታወቀ ነው። ሌላውም ዘመናዊ ፖለቲካና የእርስ በእርስ አለመስማማት ቀደም ብሎ የተነገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው።

“ምናሴ ኤፍሬምን፣ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላዋል” የተባለው ቃል የሰጠው ትርጉም ተሠርቶበት በቅቷልን? ወይስ ሲሠራበት ይኖራል?

መጽሐፉ ምናሴና ኤፍሬም በማለት የመላውን ዓለም ሕዝቦች በሁለት መድቦ በሁለት ስም እንደ ተናገራቸው ሲታሰብ ከመቼውም ይልቅ ይህ ሁናቴ በአሁኑ ጊዜ የዓለም መረጃ ሳይሆን እንደማይቀር ይታወቃል።

ይኸውም ምሥራቅና ምዕራብ የተባለው የሁለት ፖለቲካ ክበብ መሆኑ አይጠረጠርም። ጦርነትም ይደረጋል እየተባለ የሚጠረጠረውና እርስ በእርሳቸው ይበላላሉ እየተባሉ የሚታሙት ወገኖች ያሉበት ወዲህና ወዲያ የብረት መጋረጃ ክልል ነው።

“ቀንድህን ብረት፣ ጥፍርህን ነሐስ አደርግልህና ብዙ አሕዛብን ትሰብራለህ” ተብሎ ሚኪያስ በተባለው ነቢይ እንደ ተነገረው፤ የአሁኑ ዘመን ሕዝቦች ቅድድማቸው መሣሪያዎቻቸውን ሁሉ ኃይለኞችና አጥፊዎች ለማድረግ ስለሆነ ከላይ የተነገረውና ከዚህ የተገለፁት ሁለቱ ትንቢቶች በአሁኑ ጊዜ የጉዳት አስከታይ ተግባር መፈፀሚያ እንዳይሆኑ በተለይ የፀሎት መጽሐፍቶች የእግዚአብሔርን የምሕረት ደጅ ይጠባበቃሉ።

(አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 28 ቀን 1952 ዓ•ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You