የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን መጠቀም ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ለማሳደግ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ ቬክናነሰ ኦርቢት ሄልዝ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ትላንት ተፈራርመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በስምምነቱ ላይ እንደገለጹት፤ ለጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሀገር ውስጥ የፈጠራ ውጤቶች ያስፈልጋሉ።

ስምምነቱ የጤና መረጃዎችን ከማዘመን በተጨማሪ የመረጃዎችን ደህንነት መጠበቅ፣ ተደራሽነት መጨመርና ማዘመን ያስችላል ያሉት ዶክተር መቅደስ፣ ቴክኖሎጂን ከጤናው ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር ለኅብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር (ዶ/ር) በለጠ ሞላ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያን በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ፊት ለማራመድ ተቋማት ያላቸውን አቅም በማስተባበር ሊሠሩ ይገባል።

ስምምነቱ በጤና ጥበቃው ዘርፍ የማኅበረሰቡን ችግር በብዙ መልኩ ሊያቃልል፣ ልማትንና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ሊያፋጥን እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ በዘርፉ ወጣቶች ክህሎቱን ታጥቀው ቴክኖሎጂውን ማምረት፣ ወደ ውጪ መላክ የሚቻልበትን አቅም ለመገንባት እንደሚረዳም ገልጸዋል።

ከውጪ እያስመጣን የምንጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች ፋይዳ ቢኖራቸውም ተጋላጭነት አላቸው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ቴክኖሎጂን በሀገር ውስጥ መፍጠር የሚያስችል አቅምን ለማሳካት የተደረገ ጅማሮ ነው ብለዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት፣ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለወጣቶች አዳዲስ እውቀትና ክህሎቶችን ማስታጠቅ ያስፈልጋል።

በአምስት ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት በተቋማት መካከል የትብብር ባሕልን ለመፍጠር ያስችላል ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፣ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ መካከል ያለውን አቅም አስተሳስሮ በመሄድ በፍጥነት ለመልማት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ አምራችነት በሂደት የሚያሸጋግር ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን በማምረት ለሌላውም መትረፍ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ምርትን ለመጠቀም፣ ጥራት ያለው የሥራ ዕድል ከመፍጠር ረገድ የራሱ የሆነ አበርክቶ እንደሚኖረውም በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ራስን የመቻል ጉዞንና በሁሉም መስክ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ትልም እውን ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል።

የኦርቢት ሄልዝ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓዚዮን ቸርነት በበኩላቸው፣ ሀገር በቀል ኢኮኖሚንና እውቀትን እውን ለማድረግ ትብብር አስፈላጊ ነው።

እንደሀገር ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ መድረስ ካልተቻለ ወደኋላ መቅረት እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ የካምፓኒውም ዓላማ ትርፍ ሳይሆን ቴክኖሎጂውን ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You