ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን የጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል

አዲስ አበባ:- በዘንድሮ ዓመት ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የመዲናዋ ነዋሪዎች አቀፍ ጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ። የ2017 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የአባልነት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጿል።

የ2017 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የአባልነት የምዝገባ ጊዜ ከጥቅምት 1 እስከ ኅዳር 30 ቀን ድረስ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የነባር እና አዲስ አባላት ምዝገባ መካሄድ መጀመሩን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ የ2017 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ነባር አባላቶች ሙሉ ለሙሉ እድሳታቸውን እንዲያከናውኑ እና በዘንድሮው ዓመት አዲስ አባላቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልፀዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በፀደቀው መዋጮ መጠን መሠረት መደበኛ መዋጮ መጠን አንድ ሺህ 500 ብር ሲሆን የድሀድሃ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

ይህ ማለት ነባር አባል መዋጮ አንድ ሺህ 500 ብር፣ አዲስ አባል መዋጮ አንድ ሺህ 500 ብር እና የመመዝገቢያ 200 ብር በላይ አንድ ሺህ 700 ብር ዓመታዊ መዋጮ ይከፍላል ነው ያሉት።

ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ልጆች እና በአባሉ ጥላ ስር ለሚኖሩ ተጨማሪ ቤተሰብ 750 ብር እንደሚከፍል አመልክተው፤ በኢ-መደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተቀመጠውን መዋጮ በመክፈል ዓመቱን ሙሉ በሁሉም ውል በተገባባቸው የጤና ተቋማቶች አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ዋናው ነገር ጤና ነውና ኅብረተሰቡ ዛሬ ነገ ሳይል የምዝገባ ጊዜው አጭር መሆኑን ተረድቶ በሚኖርበት ወረዳ ጤና ጣቢያ በመሄድ ምዝገባ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ካልታሰበ የድንገተኛ ወጪ ለመጠበቅ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል መሆን እንዳለበት እና አባላት ወደ ምዝገባ ሲሄዱ መሟላት የሚገባውን በሙሉ በሟሟላት ሥራው የተቀላጠፈ እንዲሆን ማገዝ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን መርሕ መደጋገፍ ስለሆነ አባላት ቢታመሙም ባይታመሙም ሕመም ወይም በሽታው መቼ እንደሚገጥም ስለማይታወቅ አባልነታቸውን በወቅቱ ማደስ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ያልተመዘገበ ወይም አባልነቱን ያላደሰ አገልግሎቱን ማግኘት እንደማይችልም ተናግረዋል።

በ2016 ዓ.ም ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች በላይ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል የሆኑ ሲሆን ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ አባላትና ቤተሰቦቻቸው በተመላላሽ እና በተኝቶ ሕክምና ከጤና ጣቢያ ጀምሮ እስከ ፌደራል ሆስፒታሎች ባሉት የጤና ተቋሞች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በ2016 ዓ.ም ከተማ አስተዳደሩ ለማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ድጎማ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You