አዳማ፦ እንደሀገር ያለውን የደም ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት ለማጣጣም ትምህርት ቤቶች ደም ልገሳን በባለቤትነት መንፈስ በማስተባበር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት “ደም በመለገስና ሌሎችም እንዲለግሱ በማሳሰብ ሕይወትን እናስቀጥል” በሚል መሪ ሀሳብ የበጋ ወቅት የደም አሰባሰብ ሁኔታ ላይ ከትምህርት ተቋማት ፎረም ጋር በአዳማ ከተማ ከትናንት በስቲያ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር በ2016 ዓ.ም 349 ሺህ ዩኒት ደም የተሰበሰበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 51 በመቶ የሚሆነው ደም የተሰበሰበው ትምህርት ቤቶች ላይ ነው።
ስለዚህ እንደሀገር ያለውን የደም ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት ለማጣጣም የትምህርት ቤቶች ሚና አይተኬ መሆኑን በመረዳት፤ ትምህርት ቤቶች ደም ልገሳን በባለቤትነት መንፈስ እንዲያስተባብሩ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ሆኖም ክረምት ላይ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ ከፍተኛ የደም እጥረት እንደሚገጥም የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ ትምህርት ቤቶች በቀጣይ የክረምት ልገሳ መርሐ ግብር በቋሚነት በማዘጋጀት በክረምት ወራት የደም እጥረት እንዳይከሰት እና ዜጎች በደም እጦት ሕይወታቸውን እንዳያጡ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
የደም ልገሳ ባሕሉ እያደገ ቢመጣም የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት አኳያ ገና ብዙ የቤት ሥራ ይቀራል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ከአንድ ሀገር ሕዝብ ውስጥ አንድ በመቶው ቋሚ ደም ለጋሽ መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ።
ነገር ግን ለአብነት በ2016 ዓ.ም እንደሀገር ከተሰበሰበው 349 ሺህ ዩኒት ደም አኳያ በቋሚነት እየለገሰ ያለው ማኅበረሰብ 0.3 በመቶ እንደሆነ ይናገራሉ።
ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙበት ዋና ዓላማ በማኅበረሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ማስተማርና ማኅበረሰቡን መጥቀም ነው የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት አኳያ ያለውን የደም ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ለማቀራረብ ደም በመለገስና ሌሎችም እንዲለግሱ በማስተማር ሕይወትን በማስቀጠል የበጎ ፍቃድ ሥራ ላይ ትምህርት ቤቶችና መምህራን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በዓመታዊው የትምህርት ተቋማት ፎረም የበጋ ወቅት የደም ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ ላይ የአገልግሎቱ፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን ተሳትፈዋል።
በመድረኩም ስለ ደምና አይን ብሌን ልገሳ የመድረኩ ተሳታፊዎችን ግንዛቤ ከፍ የሚያደርጉ ጽሑፎችን ባለሙያዎች አቅርበዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም