የንግድ ማጭበርበርን ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎች ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል

አዲስ አበባ፡የሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥና የንግድ ማጭበርበርን ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎች 50 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን እንደተቻለ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ 88 ቢሊዮን 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ባለፉት ሦስት ወራት በተከናወነ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ሀገር ልታጣ የነበረውን 50 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ78 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ተቋሙ የሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥና የንግድ ማጭበርበር የመከላከል ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢንተለጀንስ ቁጥጥር፣ በድንገተኛ ፍተሻ፣ በኦዲት፣ በመደበኛ ፍተሻና ሰነድ ምርመራ እንዲሁም የቀረጥ ነፃ መብትን አላግባብ በመጠቀም የንግድ ማጭበርበርን ለመከላከል ቁጥጥር እንደሚደረግ አመላክተዋል።

ተቋሙ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አንስተው፤ በሩብ ዓመቱ ሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ገቢ እቃዎች እና 842 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ወጪ እቃዎች ተይዘዋል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ 87 ቢሊዮን 270 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 88 ቢሊዮን 100 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

አፈጻጸሙ የእቅዱን 100 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ38 ቢሊዮን 450 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ካሉት ኃላፊነቶች ሌላኛው የተሳለጠ የንግድ አገልግሎት መስጠት ነው ያሉት ኮሚሽር ደበሌ፤ በሩብ ዓመቱ 34 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ግምት ላላቸው እቃዎች የቀረጥ ነፃ መብት አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ወጪ ንግድን ለማሳለጥና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትም የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የተቋሙ የሩብ ዓመት አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት መሆኑን አመላክተው፤ ለውጤቱ መገኘት በየደረጃው ያሉ ሠራተኞች፣ ግብር ከፋዮች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎችና አመራሮች ጠንካራ ቅንጅት ወሳኝ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል። አፈጻጸሙም ለቀጣይ ሥራ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ኮሚሽሩ ጨምረው ገልጸ ዋል፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You