አዲስ አበባ:- የሀገርን ክብር ከፍ ለማድረግ ቀን ሳይወስኑ ሁሌም መትጋት ይገባል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ትናንትና ተከብሯል።
በወቅቱ አቶ አደም ፋራህ እንደተናገሩት፤ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችንን ከማክበር ባለፈ እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት ሙያ በየዕለቱ የሀገሩን ክብር ከፍ ለማድረግ መጣር ይኖርበታል። በተገቢው ቦታና ጊዜ ሁሉ የሀገርን ሰንደቅ ከፍ ለማድረግ ጠንክሮ መሥራት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብሔራዊ ሰንደቃችንን ማክበር ማለት ለሀገር ሲሉ ለተዋደቁት ክብር መስጠት ነው ያሉት አቶ አደም፤ የሃገርን ክብር ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ማንኛውም ዜጋ በተሠማራበት ሙያ ሁሉ መትጋት ይጠበቅበታል ብለዋል። ኢትዮጵያ ወርቃማ ክብሯን እንደጠበቀች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሻገር ማድረግ ከእኛ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እልፍ አዕላፍ ጀግኖች መስዋዕት የሆኑላትን የሉዓላዊነትና የነፃነት ምልክት የሆነችውን ሰንደቅ ዓላማችንን፣ በብሔራዊ የአርበኝነት መንፈስ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም አስረድተዋል።
ድላችን፣ ክብራችን፣ አይበገሬነታችን እና በፈተናዎች መካከል ፀንተን መቆማችን በሰንደቅ ዓላማችን ላይ ታትሞ ይኖራል ያሉት አቶ አደም፤ እስከ ፍጻሜው ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብና ደም አምራ፣ ደምቃ፣ ፈክታና በልፅጋ ትኖራለች ብለዋል።
ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ክብረ በዓል ማለት የኢትዮጵያን ክብር በዓለም አቀፍ አደባባይ ከፍ ላደረጉ ተገቢውን ክብር መስጠት መሆኑን ተናግረዋል። ቀኑን የኢትዮጵያን ጀግኖች፣ አንድነታችንን እና ኅብረ ብሔራዊ እሴቶቻችንን በማሰብ በተገቢው መንገድ መከበሩ አግባብ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በዓሉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚከበሩበት ነው ያሉት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት፤ ቀኑን አክብሮ ከማለፍ በተጨማሪ በማንኛውም ጊዜ በተሠማራንበት ሙያ ውጤታማ በመሆን በዓለም አደባባይ ሰንደቃችንን ከፍ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል ብለዋል።
በተጨማሪ የሰንደቅ ዓላማ ክብርን፣ ቀለማቱና ምልክቱ ያላቸውን ትርጉም ለትውልድ ማሳወቅ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው፤ ሀገር ተረካቢው ወጣት የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀምና ሥርዓትን ጠንቅቆ እንዲያውቅ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ለሀገራቸው መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎችን በማሰብ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተከፈለውን ውድ ዋጋ በማስተማር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የአ ብሮነታችን ምልክት በመሆኑ፤ አሰባሳቢ መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ማክበር ግዴታ መሆኑን አንስ ተዋል።
ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር መስጠት የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ ውድ ዋጋ ለሚከፍሉ ቀደምት ጀግኖች አርበኞችን እና የፀጥታ አካላትን ዕውቅና መስጠት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና እውን ለማድረግ የሚተጉ ብርቱ ክንዶችን ማክበርም የሀገር ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማን የማክበር መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም