አዲስ አበባ፡– የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ወደ ሕጋዊ ተፈጻሚነት መምጣቱ ኢትዮጵያ ስታራምድ የነበረውን በእኩልና በፍትሐዊነት የመጠቀም መብትን የሚያረጋግጥ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈጻሚነትን አስመልክተው ትላንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሕጋዊ ወደ ሆነ የጋራ ማዕቀፍ ተፈጻሚነት መግባቱን አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ስታራምድ የነበረውን በእኩልና በፍትሐዊነት የመጠቀም መብትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
ማዕቀፉ፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ልማት ማከናወን እያሰበች በተለያዩ ምከንያቶች ስሟን በማጠልሸት ከወንዙ እንዳትጠቀም በማድረግ አሳሪ ሕጎች ነበሩበት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህን ሕግ በመሻር ለኢትዮጵያና ሌሎችም ሀገራት ጭምር ሊጠቅም ወደሚችል ሕጋዊ ተፈጻሚነት መሸጋገሩን አንስተዋል። ይህም ዓባይን የታችኛው ተፋሰሰ ሀገራት በበላይነት እንዲጠቀሙ ያደረገውን ሁኔታ የቀየረና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ ላይ 15 ዋና ዋና መርሆዎች ያሉት ሲሆን፤ እነዚህም ከመጠቀም፤ የውሃ ሀብቱን ከመጠበቅና መንከባከብ ጋር የተገናኙና ተፋሰሱ ላይ ልማት በማከናወን ዘላቂ አገልግሎት ከመስጠት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች የተካተቱበት ነው ብለዋል።
የናይል ወንዝ ትብብር ስምምነት ማዕቀፍ በታችኛው የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ያሉ ግብፅና ሱዳን በነባር ሕጎች እነርሱን ብቻ ተጠቃሚ በሚያደርግ ሥርዓት ውስጥ እንደነበሩ በመጥቀስ፤ የላይኞቹ በተለይም ኢትዮጵያ ለዓባይ ከፍተኛ ውኃ አስተዋፅዖ እያደረገች እንዳትጠቀም ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል። አሁን ላይ ስምምነቱ ወደ ሕጋዊ ተፈጻሚነት መሸጋገሩ የነበረውን ሥርዓት በትልቁ ቀይሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ገልጸዋል።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ እንዲዘጋጅና በተፋሰሱ ሀገራት እንዲፈረም ኢትዮጵያ በርካታ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ጠቅሰው፣ ስምምነቱ አሁን ላይ ብዙ ደረጃዎችን አልፎ ወደ ሕጋዊ ተፈጻሚነት ላይ መድረሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን አስታውቀዋል።
የማዕቀፉ ስምምነት ዓላማ ማንንም ለመጉዳት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተለይ ኢትዮጵያ ስታራምድ የነበረውን በእኩልና በፍትሐዊነት የመጠቀም መብትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል። ሕጋዊ ተፈጻሚነት ላይ መድረሱም በትብብርና በጋራ ለመልማት እንዲሁም የተፋሰሱን ሀገራት ዜጎች እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስምምነቱን ያልፈረሙ ለዜጐቻቸው ተጠቃሚነት ወደ ማዕቀፉ መቀላቀል እንዳለባቸውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ዛሬ ስኬቱ ሲመጣ ትላንት የነበሩት ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የተጀመሩ ሥራዎችን ማስቀጠል ልማዷ መሆኗን ጠቅሰው፤ ስምምነቱ በተጀመረበት ወቅት ትልቅ ሚና የነበራቸውን መሪዎችም አመስግነዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም