“የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለሉዓላዊነት የተከፈለ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ምልክት ነው” -ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለሉዓላዊነት የተከፈለ፣ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ፣ የነፃነት፣ የእኩልነት ምልክት እና ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት በትውልድ ቅብብሎሽ ጸንቶ የቆየ ዓርማ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በተከበረው የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር ሊሠጡና እንደብሔራዊ በዓል ሊያከብሩት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ብቻ ታትሞ የቆየ ብሔራዊ መለያ ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በአፍሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦችም ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄ ዓርማ ምልክት መሆኑንም ተናግረዋል።

የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን ትርጉም ባለው መልኩ ማክበር ለብሔራዊ መግባባት፣ ለአብሮነት ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት መጽናት እጅግ አስፈላጊና መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዓሉ ሲከበር ኅብረብሔራዊ አንድነትና ሉዓላዊነትን ለሕልውና ዋስትና መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው። ኢትዮጵያ የመልከ ብዙ ባሕሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ፍላጎቶች፣ አስተሳሰቦች፣ በርካታ ሀብቶችና ልዩ ልዩ መልክዓ ምድር ያላት ሃገር መሆኗን በውል በመገንዘብ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ስር በጋራ መሰባሰብ አስፈላጊ መሆኑን በውል በማመላከት ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ሆና አንድ፤ አንድ ሆና ደግሞ ብዙ ነች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የዚህ መገለጫው ደግሞ ሰንደቅ ዓላማ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ጠንካራ ሃገረ መንግሥት ለመገንባት እና የኢትዮጵያን ከፍታ አስተማማኝ መሠረት ላይ ለማኖር የሚቻለው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ በማድረግ፣ በተሠማራንበት ጠንክረን በመሥራት ነው ብለዋል።

ከትናንት እስከዛሬ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በደማቸው ሉዓላዊነቷንና ነፃነቷን አስጠብቀው ያኖሯትን ሀገር ዛሬ በእውቀታችን፣ በጉልበታችንና በላባችን ማልማት አለብን ብለዋል።

ያሉብንን የዘመናት ዕዳዎች ወደሀብት በመቀየር በታላቅ ተስፋና ነገን በማለም በአብሮነት ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ በማድረግ ለኢትዮጵያ ከፍታ ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ቆርጦ መነሳት ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል።

ሉዓላዊነቷን በዘላቂነት ማስከበር የሚቻለው ከልመና ነፃ ማውጣት ሲቻል በመሆኑም ትውልዱ በተሰማራበት ዘርፍ በእውቀትና በላቡ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ መረባረብ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።

ትውልዱ የራሱ ሀገራዊ ዐሻራ የሆነውን የህዳሴ ግድብን በአንድ ልብ፣ በአንድ ሃሳብ በራሱ እውቀት፣ ጥረትና ላብ ገንብቶ በማጠናቀቅ ኃላፊነቱን እንደተወጣ ሁሉ የሀገርን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ የትውልዱ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሠላም፣ ልማትና ሕልውና ለማስከበር መስዋዕት የሚከፍሉትን የመከላከያ፣ የፀጥታ አካላት፣ የእድገትና የልማት ኃይሎች በሙሉ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

የሃገርን ሠላም የሚያውኩ ከኋላቀር አስተሳሰባቸው በማምከን ለሰንደቅ ዓላማ ክብር በመቆም ታሪካዊ ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ትውልዱ የተጀመሩ ሃገራዊ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሪፎርሞችን በተሟላ መልክ በመፈጸም ከአባቶች የወረሰውን የሃገርና የነፃነት ሰንደቅ ዓላማን ጠብቆ በማቆየት ታሪካዊ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ ኅብረታችንና አንድነታችን ማሳያ፣ የዜጎች ሃገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት መገለጫ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ ትስስር እና የሥነልቦናዊ አንድነት የሚንፀባረቅበት ምልክት መሆኑንም ነው አምባሳደር ታዬ የተናገሩት።

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ሰንደቅ ዓላማ የመስዋዕትነት፣ የነፃነት፣ የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ዓርማ ነው። የነፃነት፣ የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መገለጫ እሴት የአብሮነት ዓርማ ምልክት ነው።

ሰንደቅ ዓላማ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ውድ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው በክብር አስጠብቀው በክብር ያስረከቡን በልባችን ታትሞ የቆየ የአሸናፊነት እና የነፃነት ዓርማችን ነው።

ኢትዮጵያ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ታፍራና ተከብራ የቆየች ታላቅ አፍሪካዊ ሀገር ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በመንግሥታዊ አስተዳደር ሥርዓትም ረጅም ዓመታት ካስቆጠሩ ሀገራት ተርታ የምትጠቀስ መሆኗንና የሰንደቅ ዓላማ ታሪኳም ከሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ጋር የተቆራኘና የተሳሰረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ነፃነታችንና ሉዓላዊነታችንን ለመንጠቅ በየዘመናቱ በተደጋጋሚ የውጭ ወራሪ ኃይሎችን እናት አባቶች በተባበረ ክንድ ባንድነት ቆመው መክተውና አሳፍረው የመለሱት ለሃገራቸውና የነፃነታቸው መገለጫ ለሆነው ሰንደቅ ዓላማ ከሚሰጡት ክብር፣ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት በመነሳት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የሀገር ሉዓላዊነት እንዲከበር የሕዝቦች ነፃነትና ክብር ለማጽናት ለሰንደቅ ዓላማቸውና ለሀገራቸው ፍቅርና ክብር ሲሉ በአንድነት መስዋዕትነትን መክፈላቸውንም አስታውሰዋል።

በእለቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት የቃለመሐላ ሥነሥርዓት ያስፈጸሙ ሲሆን፤ እለቱ በየዓመቱ እየተከበረ የሚገኘውም የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 በደነገገው መሠረት መሆኑ ይታወቃል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You