ዕጩ ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ጤናቸው “በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ” ለመራጮች ለማረጋገጥ የሕክምና ማስረጃዎቻቸውን ይፋ ሲያደርጉ፤ ተፎካካሪያቸውን ዶናልድ ትራምፕም ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ ግፊት እየበረታባቸው ነው።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዋ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ የሕክምና ማስረጃዎቻቸውን ይፋ ባለማድረጋቸው “ግልጽነት ይጎድላቸዋል” ሲሉ ከሰዋቸዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ አክለውም የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጪ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ለፕሬዚዳንትነት ብቁ ይሁኑ አይሁኑ የአሜሪካ ሕዝብ እንዲያውቅ አይፈልጉም” ብለዋል።
ነገር ግን የትራምፕ ረዳቶች የሕክምና መዛግብቶቻቸውን ይፋ ሳያደርጉ የግል ዶክተራቸው ጤናቸው “ያለምንም እክል በጥሩ ሁኔታ ላይ” እንደሚገኝ በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላት ዕጩው ፕሬዚዳንት “በጣሙን የተጨናነቀ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻን በብቃት እያካሄዱ” መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሃሪስ የዚያን ያህል “ጥንካሬን የሚጠይቅ ብቃት የላቸውም” ሲሉ ተችተዋል።
በሁለቱ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች መካከል የትችት ቃላት ልውውጥ የተጀመረው የምክትል ፕሬዚዳንቷ ጽህፈት ቤት ካማላ ሃሪስ ፕሬዚዳንት ሆነው አሜሪካንን ለማገልገል የሚያስፈልገው “አካላዊ እና አእምሯዊ ጥንካሬ” እንዳለቸው ያሳያል ያሉትን የሕክምና ምርመራ ውጤት ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።
ለሦስት ዓመታት የሃሪስ ሐኪም ሆነው እያገለገሉ ያሉት የአሜሪካ ሠራዊት ኮሎኔል ዶ/ር ጆሽዋ ሳይመንስ በሕክምና ማስረጃው ላይ ምክትል ፕሬዚዳንቷ የተለያዩ ምርመራዎችን በማድግ ጤናማ እና ንቁ የሕይወት ዘይቤ እንዳላቸው አረጋግጠዋል።
የሃሪስ የሕክምና ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ የምርጫ ዘመቻ ቃል አቀባያቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ዶናልድ ትራምፕ፤ አሁን የእርሶ ተራ ነው” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዲሞክራቶች፤ ሪፐብሊካኖችን በመወከል የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪያቸው የሆኑት የ 78 ዓመቱን ትራምፕ በዕድሜ መግፋት እና በአእምሮ ብቃታቸው ሲተቿቸው ቆይተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በሚካሄደው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የሚያሸንፉ ከሆነ ከአራት ዓመት በኋላ የመሪነት ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ፣ በመጪው ጥር ሥልጣን ከሚያስረክቡት ጆ ባይደን ጋር በአሜሪካ ታሪክ በዕድሜ የገፉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ታሪክን ይጋራሉ።
ከተቀናቃኛቸው በኩል የሕክምና ማስረጃዎቻቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ግፊት የበረታባቸው ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ኃላፊ በሰጡት ምላሽ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የግል ዶክተራቸው እና በግድያ ሙከራ ከተካሄደባቸው በኋላ ሕክምና ያደረጉላቸው ሐኪሞች የጤንነታቸው ሁኔታ ተገልጿል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
“የሁለቱም ሐኪሞች ውጤት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እና የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ለመሆን በሚያስችል እጅግ በጣም ጥሩ በሚባል የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ደምድመዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የወቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በዕጩነት ቀርበዋል።
እስካሁን ያለውን የመራጮች ፍላጎትን በተመለከተ የተደረጉ ሀገር አቀፍ የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች ሃሪስ በጠባብ ነጥብ ትራምፕን እየመሩ መሆናቸውን ሲያመለክቱ፣ ከባድ ፉክክር በሚደረግባቸው ግዛቶች ውስጥ ሁለቱ ዕጩዎች በጣም ተቀራራቢ ውጤት አግኝተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም