ኢትዮጵያ የቀንድ ከብት ሃብቷ በዓለምም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ከፊተኛዎቹ ተርታ ላይ እንድትገኝ አርጓታል። ይህንን ሃብት ለኢኮኖሚ እድገቷ በመጠቀም ረገድ ግን እዚህ ግባ የሚባል ሥራ እንዳልሠራች ይታወቃል። ለዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች ከሚባሉት መካከል በእንስሳት ጤና ላይ አለመሠራቱ፣ በምርምርና በዝርያ ማሻሻል እንዲሁም የድርቅ አደጋ መከላከል ላይም እንዲሁ ብዙ ርቀት መሄድ አለመቻሉ ይጠቀሳሉ።
የእንስሳት መኖን በጥራትና በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አለመቻልም ሌላው አንዱ ምክንያት ስለመሆኑም ይገለጻል። የእንስሳት መኖን ለእንስሳቱ ማቅረብ አለመቻል ከእንስሳት የሚገኘውን ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ድርቅ በሚመላለስባት ሀገር፣ ለእንስሳት መኖ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራት ችግሩን ምን ያህል ውስብስብ ሊያደርገው እንደሚችል መገመት አይከብድም። ያለ እንስሳት መኖ ሥጋ በሚፈለገው ልክና ጥራት ማግኘት አይቻልም፤ ወተትና እንቁላልም እንደዚያው።
ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ለእንስሳት ሀብት ልማት እያከናወነች ካለችው ተግባር በተጓዳኝ በሌማት ትሩፋት እየተሠራ ያለው ሥራ የመኖን አስፈላጊነት አውጥቶ አሳይቶታል። ዜጎች በዚህ መርሐ ግብር በወተት፣ በዶሮና እንቁላል ልማት ላይ መሠማራታቸው እየሰፋ ሲመጣ ትልቁ ችግር ሆኖ የመጣው የመኖ እጥረት ነው።
ይህን ችግር የተመለከተው መንግሥት ውስን የነበሩት የመኖ ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲበራከቱ ወደ ማድረግ እንዲገባ አርጎታል። ለእዚህም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተከናወነው ተግባር በአሁኑ ወቅት በክልል ከተሞች የመኖ ማቀነባበሪያዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። የግል ዘርፉም እንዲሁ ይህንኑ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። ዜጎች በማኅበር እየተደራጁ በእንስሳትና እንስሳት ተዋፅዖ ልማት ከመሠማራታቸው በተጨማሪ በመኖ ልማት እየተሠማሩም ይገኛሉ።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን ወደሸገር ከተማ አስተዳደር በማቅናት ኮዬ ፈጬ እና ገላን ጉዳ ክፍል ከተማ በተለያዩ ወረዳዎች እየተካሔደ የሚገኘውን የተቀናጀ የከተማ ግብርና ልማትን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በጉብኝቱም በዳለቲ ወረዳ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ሙስሊምና ሶፍያ የእንስሳት መኖ አምራች ማኅበርን እንቅስቃሴ ቃኝቷል። የማኅበሩ ሊቀመንበር ወጣት ሙስሊም ናስር እንደሚናገረው፤ ማኅበሩ አምስት አባላትን ያካተተ ነው፤ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው።
በማኅበሩ ከተደራጁት ውስጥ ሦስቱ በቻይና የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው ዲግሪ ይዘዋል። ወደ እንስሳት መኖ ማምረት የመግባታቸው ምስጢርም በቻይና ለአራት ዓመት ያህል ለትምህርት በቆዩበት ወቅት በኢትዮጵያ እና የቻይና መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ማስተዋላቸውና ይህም ቁጭት ያሳደረባቸው መሆኑ ነው።
በቻይና እና በኢትዮጵያ ያለውን የዶሮ ሥጋ አመጋገብ ሲያስተውሉ በጣም የተራራቀ ልዩነት እንዳለው መረዳታቸውን የጠቀሰው ወጣት ሙስሊም፤ ‹‹በቻይና በጣም በትንሽ ገንዘብ የዶሮ ሥጋ በቀን ሦስቴ መብላት ይቻላል፤ የዶሮ ሥጋ በኢትዮጵያ እንደሚታየው እንደ በቀላሉ የማይደረስበት አይነት ትልቅ ምግብ አይታይም›› በማለት ይናገራል። ኢትዮጵያን ሲያስቡ ደግሞ የዶሮ ሥጋ እንኳን በየጊዜው ሊበላ ቀርቶ በበዓል ወቅትም በናፍቆት አሊያም ልዩ ዝግጅት ሲኖር የሚቀርብ የምግብ አይነት መሆኑ ያስገርመው እንደነበር ያነሳል።
ይህን በሁለቱ ሀገሮች በዶሮ ሥጋ ላይ የሚታየውን እጅግ ሰፊ ክፍተት የተመለከቱት እነ ወጣት ሙስሊም ክፍተቱን መሙላት የሚቻለው እንዴት ነው? ሲሉ ብዙ አሰቡ፤ በጉዳዩ ላይ ተወያዩናም ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ዶሮ ማርባት ቀዳሚው ተግባራቸው እንደሆን ደመደሙ። ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በቀጥታ ወደ ዶሮ እርባታው ከመግባታቸው በፊት ሁኔታዎችን ተዘዋውረው ለማቃኘት ሞከሩ። በምልከታቸውም በብዙዎቹ የዶሮ አርቢዎች ዘንድ በተግዳሮትነት የሚነሳው የዶሮ መኖ ጉዳይ እንደሆነ ተገነዘቡ።
ቆም ብሎ ማሰብ የግድ መሆኑን መረዳታቸውን ወጣቱ ጠቅሶ፤ ‹‹ወደ መጀመሪያው የዶሮ እርባታ ሥራቸው ከመግባታቸው በፊትም በትኩረት ተወያይተናል›› ሲል ይገልፃል። ስለዚህም ከመሠረቱ መነሳት ግድ እንደሚል በመገንዘብና እቅድ በማውጣት የመጀመሪያ ሥራቸው መሆን ያለበት የዶሮ መኖ ማምረት እንደሆነ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ያስታውሳል።
‹‹ሦስት ዓመት ያህል አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖችን ከውጭም ከሀገር ውስጥም የምናገኝበት ሁኔታ አጠናን። እንዴትና በምን እንደምንሠራ መዘገጃጀት ጀመርን፤ ተዘዋውረንም ተጨማሪ ጥናት አደረግን›› በማለትም ያስረዳል። ለጥቂት ዓመታት በመኖ ምርት ላይ ተሠማርተን ውጤታማ ከሆንን ጎን ለጎን ዶሮም ማርባት እንጀምራለን ወደሚል ውሳኔ ደርሰው መኖ የሚያለሙበትን መንገድ መያያዝ መጀመራቸውን ያመለክታል።
‹‹ሐሳባችን እና እቅዳችን ሰፋ ያለ ነው፤ ዶሮ እርባታ ብንገባ ምርታችን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ የሚውል ሳይሆን ሥጋው ታሽጎ ወደ ውጭ ሀገር መላክንም የሚጨምር ነው›› የሚለው ወጣት ሙስሊም፤ ይህም የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ከሌላው ሃገር ተሞክሮ መውሰዳቸውን ያስረዳል።
የእንስሳት መኖ አምራች ማኅበር መመሥረታቸውን የሚናገረው የማኅበሩ ሊቀመንበር፣ አሁን የእንስሳቱን መኖ የማምረት ሥራውን ተያይዘውታል። በኢትዮጵያ ያለው ገበያ ሲታይ በጣም ተፈላጊ መሆኑን መረዳታቸውንና በእንስሳት መኖ ማምረት ላይ መንግሥት በእጅጉ ሲያበረታታም እንደሚታይ ይናገራል።
እርሱ እንደሚለው፤ ለየትኛውም ሕይወት ላለው ነገር ምግብ ወሳኝ ነው፤ ሁሉም ነገር የሚነሳው ከምግብ ነው። ሰውን ጨምሮ ዶሮ፣ የወተት ከብትም ሆነ የሚደልብ ሰንጋ ሁሉ ምግብ ያስፈልገዋል። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ እንደመሆኑ ለዚህ ሕዝብ የሚመጥን ምግብ ማቅረብ መቻል ፈታኝ ነው። አሁን ካለው 120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ እንስሳት ለሚያረባው 10ና 20 ሚሊዮን ሕዝብ መኖ ማድረስ ቢቻል ለመኖ አምራቾች ትልቅ ገበያ እንደሚፈጠር አብራርቷል።
‹‹ወደ ምርቱ የገባነውም ይህን ታሳቢ በማድረግ ጭምር ነው፤ ደግሞም ውጤታማ እንሆናለን ብለን አስበናል›› ሲል የሚናገረው ወጣት ሙስሊም፤ ከተለያየ ቦታ ብዙዎች የእንስሳት መኖ ጥያቄን እያቀረቡ መሆኑን ይገልፃል። በመሆኑም በርካታ የመኖ ማምረቻ አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ እንዳልሆነ ይጠቅሳል።
የእንስሳት መኖ ማምረቻ ማኅበራቸውን ለመመሥረት ሲነሱ ሁለት ሚሊዮን ብር ይዘው መሆኑን ይናገራል። በማምረቻ ሼዱ ውስጥ የሚገኙት ማሽኖች ደግሞ ብዙ ብር የወጣባቸው መሆናውን ይገልፃል። ከእነዚህ ማሽኖች መካከል እስከ 12 ሚሊዮን ብር የወጣበት ማሽን እንደሚገኝ ያስረዳል።
‹‹ከእንስሳት ጋር ተያይዞ በተለይ በቀንድ ከብት ከፍተኛውን ቁጥር በአፍሪካ ደረጃ የያዘችው ኢትዮጵያ ናት›› የሚለው የማኅበሩ ሊቀመንበር፤ ‹‹ለዚህ የቀንድ ከብት ሀብታችን ተገቢውን መኖ ካለማቅረባችን የተነሳ በምርቱ በኩል ውጤታማ መሆን አልቻልንም›› ሲል ቁጭቱን ይናገራል። ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምስጋና ይድረሰውና በዚህ ላይ ብድር በማመቻቸት ረገድ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ጠቅሶ፣ ይህም ሥራቸውን ለማቀላጠፍ እንደረዳቸው ያመለክታል።
‹‹በዳለቲ ወረዳ ማምረቻውን ከመክፈታችን በፊት፤ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የተገዛው ማሽን ውጤታማ ይሆን ዘንድ ወሳኝ ቦታ ስንፈልግ ቆይተናል፤ የተለያዩ ቦታዎችን ለማግኘት ጥያቄ አቅርበን ነበር። ጥያቄያችን እስከ ሻሸመኔ ድረስም ዘልቆ ነበር›› በማለት ያስታውሳል። ይሁንና ሳይሳካላቸው መቆየቱን ያስረዳል።
በመጨረሻም በሸገር ከተማ አስተዳደር በገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ በዳለቲ ወረዳ ውሃና መብራት እንደልብ የሚገኝበት የተመቻቸ ሼድ ስለመገኘቱ ሐሳብ ይቀርብላቸዋል። ‹‹እኔ በቦታው ተገኝቼ ባየሁ ጊዜ ሁሉም ጥሩ መሆኑን ስለተረዳሁ ሥራ ጀመርን፤ የመብራት መቆራረጥም አላጋጠመንም›› ሲል በጅማሬያቸው ወቅት የነበረውን ሒደት ያብራራል።
‹‹ሼዶቹ ውስጥ ለውስጥ የተሟላ መንገድ ያላቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ፤ የሚገኙትም ከተማው አካባቢ እንደመሆኑ ወደ ከተማ ለመድረስም የሚወስደው ጊዜ አጭር ነው። ስለሆነም ክፍለ ከተማው ችግር እንዳይኖር ጥሩ ሥራ እየሠራ ነው›› ሲል ያብራራል።
ወጣቱ ሙስሊም እንደሚለው፤ የእንስሳት መኖ የራሱ ይዘት ያለው ነው፤ በተለይ ደግሞ የዶሮ መኖ ዘጠኝ ያህል ግብዓቶችን ይፈልጋል፤ ለመኖነት የሚዘጋጀው እነዚህ ሁሉ ተደበላልቀው ነው። ከዘጠኙ ግብዓቶች ስምንቱን በሃገር ውስጥ ማግኘት ይቻላል፤ ግብዓቶቹን መግዛት አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው የተሟላ ፋይናንስ ሳይኖር ሲቀር ነው።
ከግብዓቶቹ መካከል 50 በመቶ የሚሆነው በቆሎ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም በኢትዮጵያ በስፋት የሚመረት መሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ይገልጻል። ‹‹በቆሎ በስፋት ከሚመረትበት ከትውልድ አካባቢዬ ኢሉባቡር አስመጣለሁ›› ይላል። ቫይታሚን የሚባለው ግብዓት ግን ከውጭ ሀገር የሚመጣ መሆኑን አመልክቶ፣ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ትንሽ አዳጋች እንደሆነባቸው ይገልጻል። ‹‹ግብዓቱን አስመጪዎችም የሚሸጡልን ሦስትና አራት እጥፍ አትርፈው በመሆኑ በዚያ በኩል ችግር አለብን›› ሲልም ጠቁሟል።
‹‹ወደፊት በመኖ ሥራ ላይ ብቻ ተንተርሰን አንቀጥልም፤ ጎን ለጎን ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት አስበናል›› የሚለው ወጣት ሙስሊም፤ እንደጅምር በአሁኑ ሰዓት ከእንስሳት መኖ ጎን ለጎን ፍየል የማደለብ ሥራ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ያመለክታል። ለጊዜ የጀመሩት ጥቂት ፍየሎችን በማደለብ እንደሆነ ገልፆ፤ ይህንንም በማስፋት ወደ ዶሮ እርባታ ለመግባት ማቀዳቸውን ይጠቁማል። ‹‹በተለይም የሥጋ ዶሮን ማርባት ነው ትልቁ ፍላጎታችን ነው›› ሲል ይናገራል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የዶሮ ሥጋ መብላት የቅንጦት ያህል እንደሚቆጠር ጠቅሶ፣ ‹‹በየእለቱ በሚኖረን የምግብ ገበታ ውስጥ ዶሮን ማግኘት ብርቅ ነው፤ እኛ ግን ይህን የመቀየር ሕልም ጭምር እንዳለን መናገር አፈልጋለሁ። ይህን ማድረግ ደግሞ እንችላለን ብለን እናምናለን›› በማለት ይናገራል።
መኖ እስካለ ድረስ ዶሮንም ሌሎች እንስሳትንም ማርባት ብዙ ከባድ እንደማይሆን ጠቅሶ፣ ‹‹የእኛ ሕልም የሥጋ ዶሮ በሰፊው በማርባት የራሳችንን ብራንድ በማድረግ አሸገን የዶሮ ሥጋ መሸጥ ነው። ይህን በአጭር ዓመት ውስጥ እናሳካዋለን ብለን እናስባለን›› ሲል የማኅበሩ ሊቀመንበር ጠቁሟል። በአሁኑ ወቅት እያመረቱ ያሉትን የእንስሳት መኖ የሚሸጡት በተለያዩ አካባቢዎች ባሏቸው ወኪሎች በኩል መሆኑን ጠቅሶ፣ ከእነዚህም መካከል ቱሉ ዲምቱ እና ቢሾፍቱ ያሉት ወኪሎች እንደሚጠቀሱ ተናግሯል። ጅማ ላይም ወኪል እንደሚፈልጉ ጠቁሟል።
በሌላ በኩል ከአዳማ ወደ ጂቡቲ በሚደረገው የቁም እንስሳትን ባቡር የማጓጓዝ አገልግሎት የእንስሳት መኖ ማቅረብ አንደሚያስፈልግ ተናግሮ፣ የማኅበሩ አባላት ይህንንም ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚፈልጉ ጠቅሷል።
‹‹በወኪሎቻችን ዘንድ የምንሸጠው የእንስሳት መኖ በኩንታል 4 ሺ 500 ብር ነው። ለእንቁላል ጣይ ዶሮ ማምረት የምንችለው ስድስትና ሰባት አይነት ነው። ለወተት ከብቶች የሚውል መኖ በአካባቢያችን ላሉ ሼዶች በመሸጥ ላይ እንገኛለን›› ይላል። የአንዱ ኩንታል መኖ ዋጋም እስከ ሦስት ሺ 400 ብር እንደሆነ ያመለክታል።
እሱ እንዳለው፤ እነ ወጣት ሙስሊሙ በመኖ ማምረቻው ለዘጠኝ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፤ ከድርጅቱ ሠራተኞች መካከል የማሽን ኦፕሬተርና የኒውትሪሽን ባለሙያ ይገኙበታል፤ የኒውትሪሽን ባለሙያው መኖው እንዴት ለእንስሳቱ መስጠት እንደሚገባ ግንዛቤ ይሰጣል። በተለይ በመኖ አሰጣጥ ለላይ በትኩረት ይሠራል፤ ደንበኞች ግንዛቤው እስኪኖራቸው ድረስ ማስረዳቱ ላይ ይሠራል። ምክንያቱም ለእንስሳቱ መኖ በገፍ መስጠት አያስፈልግም፤ በየስንት ሰዓቱ፣ እንዴት መሰጠት አለበት? የሚለው ትልቁ ነገር ነው። ለእንስሳቱ መኖ በገፍ መስጠት ለሞት ሊዳርጋቸው ጭምር ይችላል። ለእዚህም ምርታቸው የሚደርስበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወረ ባለሙያው ግንዛቤ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም