የጥራት ደረጃን ከማውጣት በተጓዳኝ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግም ያስፈልጋል!

ጥራት ሰፊ እና ጥልቅ የሆነ ሃሳብ አለው። ለቃሉ ግልጽ ያለ ትርጉም ለመስጠት የማይቻልበት ሁኔታ የሚታይ ሲሆን፣ ለእዚህ ምክንያቱ በሁሉም ተግባር ውስጥ የማይገኝና በአንድ ነገር የማይወከል መሆኑ ላይ ነው። በምርት ብንለው፣ በአገልግሎት፣ በሰው ለሰው ግንኙነት ብንል በማኅበራዊ ትስስር በሁሉም ነገር ውስጥ ያለ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ለዚህ ነው “quality is in everything you do in life” እየተባለ የሚገለጸውም።

እኔ ግን ከሰፊው ጽንሰ ሃሳብ አንዱን መዝዤ ላወጋችሁ ነው። ይህም የንግድ ዘርፉን ይመለከታል። በዚህ እሳቤ ጥራት መለኪያና መመዘኛ (standards) ይቀመጥለታል። መለኪያዎቹ የብሔራዊ ደረጃዎች ድርጅት /international organization for standards (ISO)/ ሊሆኑ ይችላሉ። በኩባንያ ደረጃ በሚቀመጡ መለኪያዎችም (company standards) ሊመዘንም ይችላል።

እነዚህ መለኪያዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው ይዘቱ ምን ላይ ነው የሚለውን ያመላክታሉ፤ እንደ ሀገር ከዘመኑ ጋር አብሮ እየዘመኑ መሄድን ያላምዳሉ፤ ዜጎችን ጠቅመው አካባቢን ይጠብቃሉ፤ ጊዜውን የዋጀ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣም የበኩላቸውን ይወጣሉ። በጥራት አስቦ፣ በጥራት አምርቶ፣ ምርትን በጥራት ሥራ ላይ እንዲያውሉም እድል ይሰጣሉ። ከምንም በላይ ብክነትን በመቀነስ ተወዳዳሪነትን በማስፋት የገቢ ምንጭን ከፍ ያደርጋሉ።

ሀገራችን ከዚህ አንጻር ምን ሠራች ካልን ሁለት ነገሮችን መሥራቷን በዋናነት መጥቀስ እንችላለን። የመጀመሪያው እንደ ሀገር ጥራት የምትፈትሽባቸው ሁኔታዎቹ ተዘጋጅተዋል፤ እነዚህም የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን ያወጣቸውና በብሔራዊ ምክርቤት የጸደቃቸው 285 የሚደርሱ ብሔራዊ ደረጃዎች ናቸው።

እነዚህ ደረጃዎች በስድስት ዘርፎች የተዘጋጁም ሲሆኑ፤ በግብርናና በምግብ ዝግጅት 18፣ በመሠረታዊና አጠቃላይ የደረጃ ዝግጅት 28፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች 72፣ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ 79፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል 69፣ እንዲሁም በአካባቢና ጤና ደህንነት 19 ደረጃዎች እንደሆኑም የደረጃዎች ኢጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል። በእነዚህ ደረጃዎች በመጠቀም ሀገራት በዓለምአቀፍ ደረጃ ምዘና ምርቶችን ሲያሰራጩ ኢትዮጵያም የራሷ በሆኑ ብሔራዊ መመዘኛዎች ምርቶችን ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ታደርግባቸዋለች። ወደውጪ የሚላኩትንም ምርቶች የቅድመ ጭነት ኢንስፔክሽን ሥራዎችን ታከናውንባቸዋለች።

ሌላው ኢትዮጵያ ገና በማደግ ላይ ያለች ሀገር በመሆኗ በብሔራዊ ደረጃዎቿ ብቻ የገቢና ወጪ እቃዎች (ምርቶች)ን ጥራት ማረጋገጥ ስለሚያዳግታት የጥራት ቁጥጥርን በአማራጭ የምትሠራበትን መንገድም አመቻችታለች። ይህም በዓለምአቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን የቅድመ ጭነት ኢንስፔክሽን (Pre-Export Verification of Conformty) አድራጊ ኩባንያዎችን በመጠቀም ጥራትን የምታረጋግጥበት ነው። እነዚህ ኩባንያዎች Cotecna እና Bureau Veritas የሚባሉ ሲሆኑ፤ ሥራቸውን የጀመሩት ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ በሶላር ቴክኖሎጂ እና በውሃ ፓምፕ ምርቶች ላይ ነው። ምርቶቹ ሲገቡ የቅድመ ጭነት ኢንስፔክሽን ሥራዎችን በማከናወን የማረጋገጫ ሰርተፍኬት ይሰጣሉ። በቅርቡ በወጣ መረጃ ደግሞ ተጨማሪ 11 ምርቶችን የሚያረጋግጡና የጥራት ሰርተፍኬት የሚሰጡ ይሆናል።

ጥራት ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪውና ለንግድ ተወዳዳሪነት አቅም መጎልበት ሁነኛ መፍትሄ ነው። ከኅብረተሰቡ ጤናና ደህንነት አንጻርም ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። አቅራቢዎች ወይም ተቀባዮች በበቂ ሁኔታ አቅማቸው እንዲያድግ፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር ከማድረግ አኳያ ሚናው ቀላል የሚባል አይደለም። ምክንያቱም ወጪዎቻቸውን በመቀነስና የሚያቀርቧቸውን ምርቶች ጥራት በመጨመር ገቢያቸውን ያሳድጋሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ ሀገርም በከፍተኛ ሁኔታ እድገቷን ታፋጥናለች።

ለአብነት ከደረጃ አንጻር ብናነሳ የግብርና መሣሪያዎችን የተመለከቱ 51 ደረጃዎች መዘጋጀታቸው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፤ ከማዘመን አልፎ የግብርና ምርትን ወደ ውጭ እስከመላክና ገቢን ከፍ እስከማድረግ ድረስ የሚዘልቅ ጥቅም ያስገኛሉ።

ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ የተዘጋጁ ስድስት ደረጃዎችም እንዲሁ የሚሰጡት ጥቅም በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ከቆሻሻ መለየት፣ ማስወገድና መልሶ መጠቀም ጋር የተቆራኙ ጥቅሞችን እንድናገኝ ያስችላሉ። በአጠቃላይ ጥራት የምርቶችን፣ የአገልግሎቶችንና ተያያዥ ጉዳዮችን ጥራት ከማሻሻልና ከማረጋገጥ አንፃር ፋይዳው የጎላ ነው።

ይህ ግን እውን የሚሆነው ሕግ ወይም ደረጃ ብቻ ስለወጣ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። መሬት ላይ በተግባር በሚገባ የሚተረጎምበት ሁኔታ ይወስነዋል። ከዚያ የላቁ ደጋፊ ሥራዎችም አብረውት ሊከናወኑ ይገባል። ለአብነት ተግባራዊነቱ ታችኛው ማህበረሰብ ክፍል ድረስ መውረዱንና እየተሠራበት መሆኑንን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ድንገተኛ ፍተሻዎች እንደ ተጨማሪ ግብዓትነት ታይተው ሊሠራባቸውም ይገባል። ምክንያቱም ዛሬ ላይ በሀቅ ከሚሠራው ይልቅ በውሸት የሚሠራው ተቀባይነትን እያገኘ ያለበት ሁኔታ ይታያል። በገቢም እየተሻለ የሚሄደው አመሳስሎ በመሥራት ሕዝቡን የሚያጭበረብረው ነው። ገበያውን የሚያጨናንቀውም ይሄው አካል ነው።

ለዚህ ችግር መፈጠር ምክንያቱ ደግሞ ተጠያቂነት አለመስፈኑ ነው። የተወሰኑ ርምጃዎች ቢኖሩም ሕዝቡ ከተበዘበዘና ነገሮች ከተጠናቀቁ በኋላ ነው። ለዚህ አብነት የሚሆነን በቅርቡ የታገደው የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ቁስ ሲሆን፤ ማከፋፈያው ማህበረሰቡ ዘንድ ደርሶ ካለቀና ተጠቃሚው በገንዘብም ሆነ በሌሎች አገልግሎቶች ጉዳቶች ከተሰቃየ በኋላ ነው። ይህ ደግሞ ሌቦችን ያበረታታል እንጂ ሀገርንም ሆነ ዜጋውን ሊጠቅም አይችልም፤ እንዲያም ጉዳት ነው የሚያደርሰው።

እናም ደረጃዎች ከማውጣት ጎን ለጎን ፍተሻው፤ ክትትሉ ከስር መሠረቱ ሊሠራበት ይገባል። ወቅቱን የዋጀ ክትትል በተቆጣጣሪው አካል መደረግ ይኖርበታል። በተለይም ድንገተኛ ፍተሻዎችን መጠቀም ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ሕግ ሲጣስም ተገቢውን ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። በእርግጥ ተቆጣጣሪው አካል ብቻ ይህንን ያስፈጽም አይባልም። ማህበረሰቡ ይህን ሕገወጥ ተግባር ለማስወገድ የበኩሉን ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።

ጊዜውን የጠበቀ ቁጥጥርና ሕግን የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የዚሁ የማህበረሰቡ ተባባሪነት ወሳኝነት አለው። ተቆጣጣሪው ተቋም የእያንዳንዱን ችግር ለይቶ ለማወቅ የሚችልበት አጋጣሚ አይኖርምና የችግሩ ሰለባ እየሆነ ያለው የዚሁ ማህበረሰብ ሃላፊነት ወሳኝ ነው። በተለይ ግለሰቦች ነገሮችን አብጠርጥሮ ማውጣት ስለሚችሉ የጥራት አምባሳደር ሆነው ሕግ እንዲከበር መሥራት ይገባቸዋል በማለት ሃሳቤን ቋጨሁ። ሰላም!!

ክብረ መንግሥት

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You