የመልሶ ግንባታው ሌላኛው ገፅ

ግጭት በዜጎች ላይ ጥሎ ከሚያልፋቸው አያሌ ጠባሳዎች መካከል አንዱ የሥነ ልቦና ቀውስ ነው።ግጭት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ከሚያደርሰው ውድመት ባለፈ የዜጎችን የረጅም ጊዜ ማህበራዊ መስተጋብር እና የሥነልቦና ደህንነት የማዳከሙ ጉዳይ የአደባባይ እውነታ ነው።

በሀገራችን በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች የሥነልቦና ቀውስ እንዳጋጠማቸው ይነሳል።ተጎጂዎች ከሚፈጠርባችው የማህበራዊ ሥነልቦና ጉዳት ለማገገም በተናጠል ወይም በጋራ የሚደረግ የሥነልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም በባለሙያዎች ይነገራል።

የሥነ ልቦና ህክምና ባለሙያዋ ትግስት ዋልተንጉሥ፤ ከግጭት በኋላ ትኩረት የሚሰጠው ለምግብ፣ አልባሳትና ቁሳቁስ ነው።ነገር ግን ግጭቱ በዜጎች ላይ ጥሎት ያለፈው የሥነልቦና ጠባሳ ይዘነጋል ይላሉ።

ከግጭት ጋር የተያያዙ ጉዳቶችን በአእምሯዊ ጤና እና በሥነ ልቦና ድጋፍ መርሃ ግብር አማካኝነት ወደትግራይ ክልል በመጓዝ የሥነልቦና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ ማድረጋቸውን የሚጠቅሱት ባለሙያዋ፤ በወቅቱ ዜጎች ወደቀደመው ሕይወታቸው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም እንኳን የሥነልቦና ችግር ትልቅ እንቅፋት እንደሆነባቸው መመልከት መቻላቸውን ይገልፃሉ።

እንቅልፍ ማጣት፣ የበቀል ስሜት፣ ድባቴ፣ ጭንቀት፣ ተስፋ ማጣትና ሌሎች አላስፈላጊ ስሜቶች እንደሚስተዋልባቸው አመላክተው፣ እነኚህ ስሜቶች ካልታከሙ ከዜጎቹ ጋር አብሮ የመቆየት እድላቸው ሰፊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ትግስት በዚሁ ፕሮግራም አማካኝት ከትግራይ በተጨማሪ በአፋርና አማራ ክልሎች ተንቀሳቅሰው ሠርተዋል።በሁለቱ ክልሎች ዜጎች በማህበር፣ እድር፣ እቁብና በሌሎችም ማህበራዊ መስተጋብሮች ተሳስረው ረጅም ዓመታትን ቢያሳልፉም፣ ከግጭቱ በኋላ እነኚህን መስተጋብሮች እያቆሙ እንደሆነና እንዲሁም ከትዳር አጋሮቻቸውም ጋር ግንኙነት ማድረግን ያቋረጡ መኖራቸውን እንደተረዱ ይገልፃሉ፡፡

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ፤ የበቀልና መከፋት ስሜቶች መታከም አለባቸው፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ዜጎች ተመልሰው ወደግጭት መግባታቸው የማይቀር ነው።የፈረሰ ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ የእምነት ተቋማትና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የዜጎች ስሜትም መታደስ አለበት።ይህ የማይሆን ከሆነ ከትውልድ ወደትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ግጭቱ በዜጎች ላይ ያስከተለውን የአዕምሮ ቁስል ጠባሳ (Trauma) ለማጥፋት እንደሀገር ፕሮግራም ያስፈልጋል፤ ሥለሥነልቦና ጤና ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌላውም ዜጋ ሊያውቅ ይገባል።ችግሩን ለመፍታትም መንግሥትን ጨምሮ የእምነት ተቋማት፣ እድሮችና ሌሎችም ማህበራዊ ተቋማት በጋራ ሊሠሩበት ይገባል ሲሉ ባለሙያዋ ያስገነዝባሉ፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀዶ ጥገና ባለሙያውና የሀቂ ፋውንዴሽን ሃላፊ ዶክተር ፋሲካ አምደሥላሴ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ድህነት ባለበት ሀገር ግጭት በመስፋፋቱ ዜጎች ለችግር መዳረጋቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል።ግጭቱ ከቁሳዊና አካላዊ ጉዳት በተጨማሪ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ እንዲገጥም ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም ሞት፣ ረሃብ፣ ጉስቁልናና የተለያዩ በሽታዎች በየዜጎች ቤት ደርሰዋል፡፡

ጦርነት ከሚያመጣቸው ጉዳቶች አንደኛውና ዋነኛው የሥነልቦና ቀውስ ሲሆን ይህም በትግራይ ክልል በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል የሚሉት ዶክተር ፋሲካ፤ ከእርስ በእርስ ግጭቱ በኋላ በመምህራንና በጤና ባለሙያዎች ላይ ብቻ በተደረገ ጥናት እስከ 90 በመቶ በሚደርሱ ዜጎች ላይ ጭንቀት፣ ፍርሀት፣ ተስፋ መቁረጥና ሌሎች ተመሳሳይ የሥነ ልቦና ቀውሶች እንደተጋረጠባቸው ይጠቁማሉ፡፡

ዶክተር ፋሲካ እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያም ሆነ በክልሉ ያሉ የሥነልቦና ባለሙያዎች ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ እያንዳንዱን ዜጋ ለማከም አስቸጋሪ ነው።ለዚህም በትንሽ ባለሙያ በርካታ ዜጎች ጋር መድረስ የሚቻልበትን አዲስ የፈጠራ ሃሳብ በማመንጨት ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የነጻ ስልክ መስመር በማቋቋም ዜጎች ለሥነልቦና ባለሙያዎች እየደወሉ ችግሮቻቸውን እንዲያማክሩ በማድረግ እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማትም ተማሪዎችና ታካሚዎችን በማሠልጠን ስለሥነልቦና ጤና የሚሰጠው ትኩረት እንዲያድግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

የሥነልቦና ችግር በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያደርስ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ የሚናገሩት ዶክተር ፋሲካ፤ በሚዲያዎች ላይ የሥነ ልቦና ህክምና ባለሙያዎች ስለአዕምሮ ጤና ጉዳዮች በደንብ ሃሳብ እንዲሰጡ ማድረግና ተከታታይ የቴሌቪዥንና ራዲዮ ድራማዎችን በማሰራጨት ከዚህ ቀደም ልክ ኤች አይቪ ላይ በስፋት በመስራት መቀነስ እንደተቻለው ሁሉ በሥነልቦና ጤናም ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You