ኢትዮጵያ ከራሷ ባሻገር ለጎረቤቶቿ የሎጂስቲክስ ማዕከል እንድትሆን እየተሠራ ይገኛል – አቶ አህመድ ሽዴ የገንዘብ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- ‹‹ኢትዮጵያ ከራሷ ባሻገር ለጎረቤቶቿ የሎጂስቲክስ ማዕከል እንድትሆን መንግሥት በቁጠኝነት እየሠራ ይገኛል›› ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሎጂስቲክስ ዘርፍ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አካላት በተዘጋጀው የእውቅና መድረክ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ መንግሥት በሎጂስቲክስ ዘርፍ ሰፊ ኢንቨስትመንት እያከናወነ ሲሆን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል፡፡

ለአብነትም ከኬንያ እንዲሁም በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሎጀስቲክስ ዘርፍ ለመስራት ስምምነት መደረጉን ገልጸው፤ ይህም አትዮጵያ ከራሷ ባሻገር ለጎረቤቶቿ የሎጂስቲክስ ማዕከል ሆና እንድትወጣ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ሎጂስቲክስ ሥርዓቱን ለማሻሻል በቻይና መንግሥት ድጋፍ ከጅቡቲ ጋር የተደረገው በባቡር ኢንቨስትመንት በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ውጤት እያመጣ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን በዋነኝነት በሪፎርሙ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አውስተው፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ በተለያዩ ሴክተሮች እንዳይሳተፉ ማነቆ የነበሩ የተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሪፎርም ሥራዎች ሲሠሩ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘርፉ ላይ በስፋት ኢንቨስት በማድረግ በተለይ በካርጎ ሎጂስቲክስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ጠንካራ ሥራ እየሠራ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

መንግሥት የአየር መንገዱን አቅም ለማሳደግና አዲስ ኤርፖርት ጭምር ለመገንባት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።ለአብነትም አየር መንገዱ የጭነት አገልግሎትን የበለጠ ቀልጣፋ ለማድረግና የሀገሪቱን የገቢና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ለማሳደግ እየገነባ የሚገኘው የካርጎ ተርሚናል ማስፋፊያ ሥራ ጥሩ አፈጻጸም ላይ የደረሰ ሲሆን ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ሎጂስቲክስ እንዲሻሻል ዓላማ አድርጎ ማስቀመጡን ጠቅሰው በዚህም ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ሕዝብ ያላት፤ ኢኮኖሚዋም እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ አህመድ፤ የማሪታይም ሎጀክስቲክስ ሥራዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶች በሀገር ኢኮኖሚው እድገት ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አመላክተዋል።

በተለይም የዘርፋን አሠራሮችን በማዘመን፣ መሠረተ ልማት ማሟላት፣ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራትና ኤክስፖርት ሎጂስቲክስን ከማስፋት አንጻር በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You