የኢትዮጵያ እድገት ሌላኛው አቅም

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነውን የማዕድን ሀብቷን እስካሁን ማወቅ አለመቻሏን ጥናቶች ያመለክታሉ። ለዚህም የሥነ-ምድር መረጃዎች አለመገኘትና ፍለጋው ባህላዊ መንገዶችን ተከትሎ መካሄድ ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

ደካማ መሆን እንዲሁም ፍለጋው በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆን ሀገሪቱ ካላት የማዕድን ሀብት ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ብቻ ማወቅ እንድትችል ያደረጋት ሲሆን ይህም ያላትን ማዕድን ሀብት ባግባቡ እንዳትጠቀም የሚያደርጋት ምክንያት እንደሆነ ይነሳል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ካላት ማዕድን አንጻር ምን ያህል እየተጠቀመች ነው? በዚህ ዘርፍ ያለው ሕገወጥነት ምን ይመስላል? እንዴትስ መከላከል ይቻላል? የሚሉ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ምሁራንና ሃላፊዎች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማይኒንግ መምህር ኤሊያስ ካሳሁን ፤ በሀገራችን ያለው የማዕድን ሀብት በየቦታው ተበታትኖ ያለ ነው። ይህም ጠለቅ ያሉ የአሰሳ ጥናቶች እንዳይካሄዱ ያደርጋል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ብዙ የማዕድን ክምችት ያሉባቸው ቦታዎች አሁን ላይ ግጭቶች አሉባቸው ያሉት መምህሩ ለአብነትም ትግራይ፣ ወለጋ እንዲሁም ጉጂ ማንሳት ይቻላል። በነዚህ አካባቢዎች ግጭቶች ባይኖሩ ጥሩ የማዕድን ሀብት ያሉባቸው ነበሩ ሲሉ ይገልጻሉ።

በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች ነባር የሆነው በጉጂ ዞን የሚገኘው የሚድሮክ ወርቅ ማምረቻ ድርጅት ባሁኑ ጊዜ በዓመት እስከ 3 ነጥብ 5 ቶን እያመረተ ይገኛል ያሉት አቶ ኤልያስ ቀደም ባሉ ዓመታት ግን እስከ 8 ቶን ይመረት ነበር ይላሉ።

ሌላው ዘርፉን እየጎዳ ያለው ሕገወጥነት መሆኑን የሚያነሱት መምህሩ ይህም ማዕድን አውጪዎችን የሚጎዳና ጥራት ያለው የማዕድን ምርት እንዳይገኝ የሚያደርግ ሲሆን በተለይም በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎች በርካታ የወርቅ ማዕድን ቢኖርም በግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ ተይዞ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

በዓለም ላይ ማዕድን በባህላዊ መንገድ እንዲወጣ የፈቀደች ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ይህም ያለውን የማዕድን ሀብት በዘላቂነት እንዳንጠቀም ያደርጋል ሲሉ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ካላት የማዕድን ሀብት 3 በመቶ የሆነውን እንኳን አልተጠቀመችም ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ያለውን ሀብት መጠቀም ብቻም ሳይሆን ማዕድናቱ ያሉበት ቦታዎችን መለየት በራሱ ትልቅ ሥራ የመሚጠይቅ ነው ይላሉ።

አቶ ኤልያስ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀምና በዘርፉ ያሉ ሕገወጥነትን ለመከላከል አዲስ ተግባራዊ የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው እያገዘው እንደሚገኝ አንስተው ዘርፉ ከፍ ያለ የፋይናንስ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ጠለቅ ያሉ ጥናቶችን ማካሄድ እንደሚኖርበት ይጠቁማሉ።

የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ከከበሩ ማዕድናት እስከ ግንባታ በርካታ ማዕድናት ያላት ሀገር ናት። መንግሥትም ባለፉት አምስት ዓመታት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ በማልማት ላይ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም አላገኘችም የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም የሆነው ለበርካታ ዓመታት ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሠራቱ ነው ይላሉ።

ሌላው በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከወርቅ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሕገወጥነት አጋጥሟል ያሉት አቶ ኤልያስ አሁን ላይ ያለው ሕገወጥነት በቅርቡ ተግባራዊ ከተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በኋላ ወርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ባንኮች መግባት ጀምሯል ብለዋል።

አቶ ሚሊዮን፤ ባለፈው በጀት ዓመት 900 ኪሎ ግራም ወርቅ መገኘቱን አንስተው ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በኋላ በነሃሴና መስከረም ወር ብቻ ከሁለት ሺህ 700 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል። ይህም የፖሊሲ ማሻሻው ያመጣው ውጤት መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ ከግብርናው በመቀጠል ክፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው ከማዕድን ዘርፉ ነው።

በቀጣይም በዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ሶስት የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፕጀክቶቹ በአንድ ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ማምረት ይገባሉ ብለዋል።

አቶ ሚሊዮን፤ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎቹ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በዓመት ከ10 ቶን በላይ ተጨማሪ የወርቅ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ወደ ውጭ የሚላከውን የማዕድን ምርት በመጠንም ሆነ በጥራት እንዲጨምር ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በቤኒሻንጉል ፣ ጋምቤላና ትግራይ ክልሎች እንደሚገነቡ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በቤኒሻንጉል ክልል በኮርሙክ ወረዳ የሚገነባው ፕሮጀክት ትልቅና በዓመት እስከ ዘጠኝ ቶን ወርቅ እንደሚያመርት ተናግረዋል።

አቶ ሚሊዮን፤ ከሶስቱ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ጉጂ የሚገኘው ነባር የወርቅ ማምረቻ ኩባንያ የማስፋፊያ ሥራ እየተሠራለት መሆኑን ገልጸው ከወርቅ ባለፈም የፖታሽ ማዕድንን በአግባቡ ማምረት የሚያስችል ፕሮጀክቶች በአፋር ክልል የሚገነቡ ይሆናል ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ማዕድናት 420 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲያለሙ በሀገሪቱ ክፍት የሆነ አሠራር ተዘርግቷል። በዋናነት ከዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማግኘት የካፒታል ምንጭ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረትና ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር በዘርፉ የሚሠሩ ሥራዎች መካከል ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You