ዲላ፦ በጌዴኦ ዞን በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ197 ሺህ በላይ መማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፎች መሰራጨታቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዞኑ የመማሪያ መጽሐፍ ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍ በክልልና በዞን የጋራ ትብብር የሚታተም ነው።
ለዚህም እንደጌዲዮ ዞን አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ በሚል እንቅስቃሴ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል። በዚህም የመማሪያ መጽሐፍት እየታተሙ ይገኛል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍ በትምህርት ሚኒስቴር የሚታተም ሲሆን ይህንንም በፍጥነት የማሰራጨት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
በዞኑ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ197 ሺህ በላይ መማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፎች ተሠራጭተዋል ያሉት አቶ ዘማች፤ በዘንድሮ ዓመት ከ197 ሺህ በላይ መማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፎችን ከክልል ትምህርት ቢሮና ከትምህርት ሚኒስቴር ተረክበን ማሰራጨት ችለናል ፡፡ በዚህም ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያሉ መጽሐፎች ተሰራጭተዋል ነው ያሉት።
ከቅድመ አንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል ያሉ መጽሐፎች ወደ ማተሚያ ቤት ለህትመት እንደገቡ የገለጹት አቶ ዘማች፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍ መሰራጨቱንም ገልጸዋል። ዘንድሮ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ከአንድ ለአንድ እስከ አንድ ለአምስት መጽሐፎች በሁሉም የትምህርት አይነት ለማዳረስ የሚያስችል ሥርዓት መፈጠሩን ተናግረዋል።
በዚህ ደረጃ የትምህርት ቤቶች ትልቅ ተግዳሮት የሆነውን የመጽሐፍ እጥረት ከሞላ ጎደል እየተፈታ ነው ያሉት አቶ ዘማች፤ እንደዞን የግብዓት አቅርቦት ለትምህርት ስኬት በሚል መሪ ሃሳብ ሁሉም ትምህርት ቤት ወጥ በመሆነ መንገድ ያላቸውን መጽሐፍ ለተማሪዎች እንዲያስተላልፉ ተደርጓል ብለዋል።
አሁን ላይ በዞኑ የመጽሐፍ ማከማቻ ቦታ ላይ የተቀመጠ መጽሐፍ አለመኖሩን ተናግረው፤ አሁን ላይ የታተሙ መጽሐፎች በእጃችን አለመኖሩን እና ከትምህርት ሚኒስቴርና ከክልል ትምህርት ቢሮ በኩል ታትመው የሚሰጡንን መጽሐፎች በፍጥነት ለማዳረስ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ 327 ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ አምና ወደ 295 ሺህ መጽሐፎችን ለትምህርት ቤቶች ማዳረስ ተችሏል ብለዋል። የትምህርት ሥርዓቱ በቅርቡ የተሻሻለ መሆኑ፣ የኢኮኖሚያዊ አቅም ዝቅተኛ መሆን የመጽሐፍ ተደራሽነት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም